ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ የድሬዳዋ ቆይታቸውን በድል ጨርሰዋል

በድሬዳዋ ስታዲየም በተደረገው የመጨረሻ ጨዋታ ባህርዳር ከተማ አርባምንጭ ከተማን በኦሴይ ማውሊ ግቦች 2-0 ረቷል።

የድሬዳዋ ስታዲየም የመጨረሻ ጨዋታ ምሽት 01፡00 ላይ በአርባምንጭ ከተማ እና በባህር ዳር ከተማ መካከል ሲደረግ አዞዎቹ ሲዳማ ቡናን 3-0 ሲመሩ ቆይተው 3-3 በተለያዩበት ጨዋታ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል በዚህም ይስሃቅ ተገኝ ፣ በርናንድ ኦቼንግ እና መላኩ ኤልያስ በአቤል ማሞ ፣ አዩብ በቀታ እና ሱራፌል ዳንኤል ተተክተው ገብተዋል። 

የጣና ሞገዶቹ በበኩላቸው በመቻል 3-2 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ታፔ አልዛየር ፣ መሳይ አገኘሁ ፣ ተስፋዬ ታምራት እና በረከት ጥጋቡ በፋሲል ገብረሚካኤል ፣ ሳለአምላክ ተገኘ ፣ ያሬድ ባዬህ እና ቻርልስ ሪባኑ ቦታ ተተክተው ጀምረዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመሩት የጣና ሞገዶቹ በዱሬሳ ሹቢሳና ፍጹም ጥላሁን የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ 4ኛው ደቂቃ ላይ ፉዐድ ፈረጃ ከቅጣት ምት በመታው እና ግብጠባቂው በመለሰው ኳስ የጨዋታውን የመጀመሪያ ፈታኝ ሙከራ አድርገዋል። 8ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ አገኘሁ ከረጅም ርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ የአዞዎቹ ተከላካዮች ተደርበው አውጥተውበታል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ኦሴይ ማውሊ በግሩም አጨራረስ ባስቆጠራት ጎል ባህርዳር ከተማ ቀዳሚ መሆን ችሏል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረጋቸውን የቀጠሉት አዞዎቹ የተሻለ እንቅስቃሴ ወደ ማድረጉ ቢመጡም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። ይባስ ብሎም በመልሶ ማጥቃት 18ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። ፈቱዲን ጀማል ከረጅም ርቀት ባሻገረው ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘው ዱሬሳ ሹቢሳ ሳይጠቀምበት የቀረው ለጣና ሞገዶቹ ሌላ የመከነ ትልቅ የግብ ዕድል ነበር።

በተጨማሪም 22ኛው ደቂቃ ላይ ፈቱዲን ጀማል ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው ኦሴይ ማውሊ ተረጋግቶ ወደ ጎልነት መቀየር የሚችልበት አጋጣሚ ቢያገኝም ያባከነው ለባህር ዳር ሌላኛው አስቆጪ አጋጣሚ ነበር። ከዚህ ሙከራ በኋላ ግን ጨዋታው ተቀዛቅዞ የቀጠለ ቢሆንም 35ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን ኳሱን ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ተገልብጦ ለማስቆጠር ካደረገው ሙከራ ውጪ ሁለቱም ቡድኖች ግልፅ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ የአዞዎቹ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የማጥቃት ባሕርይ ያላቸውን ተጫዋቾች የመከላከል ባሕርይ ባላቸው ተጫዋቾች ቀይረው በማስገባት ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት ሲሞክሩ የአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ተጫዋቾች ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደራሳቸው የሜዳ ክፍል ተጠግተው በሚያገኙት ኳስ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሙከራቸውን ቀጥለዋል።

አዞዎቹ በኳስ ቁጥጥሩ በኩል ከመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ ተሻሽለው ሲቀርቡ የጠሩ የግብ ዕድሎች በመፍጠሩ በኩል ግን በባህር ዳር ከተማ ተከላካዮች መፈተናቸውን ቀጥለዋል። የሚያገኟቸውን ኳሶች በቀጥተኛ አጨዋወት መዳረሻቸውን አህመድ ሁሴን ላይ በማድረግ ጥቃት ለመሰንዘር ቢሞክሩም ሊሳካላቸው አልቻለም። 81ኛው ደቂቃ ላይም ልፋታቸው ላይ ውሃ የቸለሰ ግብ ተቆጥሮባቸዋል።

በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከሩት ባህርዳሮች ተሳክቶላቸው ሀብታሙ ታደሰ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ኦሴይ ማውሊ ተከላካይ አታልሎ በማለፍ በድንቅ አጨራረስ ለራሱ እና ለክለቡ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሮ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀዛቅዘው ለቀረቡት እና ሥራ ለበዛባቸው የጣና ሞገዶቹ መሪነታቸውን በማጠናከር እፎይታን ፈጥሯል።

በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን አዞዎቹን ለባዶ ከመሸነፍ የሚያድናቸውን ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ የነበር ሲሆን ያደረገውን ሙከራ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። ጨዋታውም በባህር ዳር ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።