ሰበር ዜና | “ራሴን ከብሔራዊ ቡድን አግልያለሁ” ጌታነህ ከበደ

የዋልያዎቹ ወሳኝ አጥቂ ራሱን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማግለሉን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል።

7ኛው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒየን ሺፕ ውድድር ከቀናት በኋላ በአልጄሪያ ይደረጋል። የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ለዚሁ የቻን ውድድር 28 ተጫዋቾችን የመረጡ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ ስብስብ ውስጥ አጥቂው ጌታነህ ከበደ እንደሚገኝ ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድኑ በዛሬው ዕለት ዝግጅቱን ሲጀምር ተጫዋቹ አለመገኘቱን ጠዋት አጋርተን የነበረ ሲሆን አጥቂው አሁን ለድረ ገፃችን ባሳወቀው መሰረት ደግሞ ራሱን ከብሔራዊ ቡድን ማግለሉን ገልጿል።

ከ2001 ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በወጥነት ያገለገለው ተጫዋቹ በሀገሩ መለያ ሪከርድ እንደሆነ የሚገለፀውን 33 ግብ በስሙ ማስቆጠሩ ይታወሳል። ጌታነህ ከበደ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ እንዲመለስ በእግርኳሱ አመራሮች ከፍተኛ ማግባባቶች እየተደረጉ እንደሆነ ብንሰማም ተጫዋቹ ለሶከር ኢትዮጵያ ይህንን ውሳኔ አስቦበት እንደወሰነ ከደቂቃዎች በፊት አሳውቋል።

ጌታነህ ከበደ በውሳኔው ዙሪያ በነገው ዕለት ዝርዝር ጉዳዮችን የሚያነሳበትን ቆይታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር እንደሚያደርግ ጠቁሟል።