ቻን | የዋልያዎቹ የመጀመሪያ ተጋጣሚ ከሌሎች ሀገራት ቀድማ አልጄሪያ ትደርሳለች

በምድብ የመጀመሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የምትገጥመው ሞዛምቢክ ወደ አልጄሪያ የምትገባ የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች።

የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒየንሺፕ (ቻን) ውድድር ከሁለት ሳምንት በኋላ በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ይከናወናል። በዚህ ውድድር ከሚሳተፉ 18 ብሔራዊ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ አንድ ከአስተናጋጇ አልጄሪያ፣ ሞዛምቢክ እና ሊቢያ ጋር መደልደሉ ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድኑ በአሁኑ ሰዓት የሀገር ቤት ልምምዱን እየከወነ የሚገኝ ሲሆን በቀጣዩ ሳምንት አጋማሽ ወደ ሞሮኮ አምርቶ የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅቱን ከከወነ በኋላ ጥር 3 ወይም 4 ወደ አልጄሪያ የሚያመራ ይሆናል።

በዚህ የቻን ውድድር ለሁለተኛ ጊዜ የምትሳተፈው እና በኢትዮጵያ ምድብ የምትገኘው ሞዛምቢክም ከሁሉም ሀገራት ቀድማ በዛሬው ዕለት አልጄሪያ እንደምትገባ ተጠቁሟል። በአሠልጣኝ ቼኪኒዮ ኮንዴ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ ወደ ሥፍራው ካቀና በኋላ በቀጣዮቹ 15 ቀናት ዝግጅቱን አድርጎ ጥር 6 የመጀመሪያ ጨዋታውን ከኢትዮጵያ ጋር በባራኪ ስታዲየም ያደርጋል።