ቻን | በኢትዮጵያ ምድብ የምትገኘው ሊቢያ የቻን ተሳትፎ አደጋ ውስጥ ገብቷል

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በምድብ አንድ የተደለደለችው ሊቢያ ከቻን ውድድር ራሷን ልታገል እንደምትችል ተሰምቷል።

ከ2022 ወደ 2023 የተዘዋወረው 7ኛው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒየንሺፕ ውድድር በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ከጥር 5 ጀምሮ ይከናወናል። በ18 ሀገራት መካከል በሚደረገው ውድድር ላይም ሀገራችን ኢትዮጵያ ከአስተናጋጇ አልጄሪያ፣ ሊቢያ እና ሞዛምቢክ ጋር መደልደሏ ይታወቃል። ባለንበት የውድድሩ መቃረቢያ ጊዜ ብሔራዊ ቡድኖቹ ዝግጅታቸውን አቀላጥፈው እየሰሩ እንደሆነ ቢታወቅም በሊቢያ ብሔራዊ ፌዴሬሽን ላይ የተከሰተው ነገር ግን ቡድኑን ከቻን ውድድር ራሱን እንዲያገል ሊያደርገው እንደሚችል ተሰምቷል።

ብሔራዊ ቡድኑ ባለንበት ሳምንት ዝግጅቱን ሀገሩ ላይ ጀምሮ በቀጣዩ ሳምንት የመጀመሪያ ቀናት ወደ ቱኒዚያ አምርቶ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ለማድረግ ቢያስብም አመሻሹን የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ የሂሳብ አካውንት በፍርድ ቤት በመታገዱ ከዝግጅት ጀምሮ ያሉ ወጪዎችን ለመሸፈን እንደማይችል በመግለፁ ከውድድሩ ራሱን ሊያገል እንደሚችል ተገልጿል።

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አካውንቱ ስለታገደ ተቃውሞውን ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ ችግሩን እንዲፈቱ የጠየቀ ሲሆን አዎንታዊ ምላሽ ካልተሰጠው ከአሠልጣኝ ደሞዝ ጀምሮ ያሉ ወጪዎችን መፈፀም ስለማይችል ዝግጅቱንም እንደሚያቆም ይፋ አድርጓል።