የፋሲል ከነማን ቀጣዩ አሰልጣኝ ማን ይሆን ?

አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽን ያሰናበተው ፋሲል ከነማ ቀጣዩን አሰልጣኝ ለመሾም ከጫፍ መድረሱን ሶከር ኢትዮጽያ አረጋግጣለች።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ከሆኑ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው እና የ2013 የሊጉ የዋንጫ ማንሳት የቻለው ፋሲል ከነማ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን አጋማሽ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደን ካሰናበተ በኋላ ምክትል አሰልጣኝ የነበሩት ኃይሉ ነጋሽን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት እንዲመሩ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል።

\"\"

ክለቡ አሰልጣኙ የቀሩትን ጨዋታዎች መርተው ባስመዘገቡት አመርቂ ውጤት መነሻነት የዘንድሮውን የውድድር ዘመን በዋና አሰልጣኝነት እንዲመሩ በኃላፊነት ሾሞ የነበረ ቢሆንም አሰልጣኙ መቆየት የቻሉት አስራ ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ሆኗል። ፋሲል ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ያለ ጎል ካጠናቀቀበት ጨዋታ በፊት አሰልጣኙ ከክለቡ ጋር የተለያዩ ሲሆን የክለቡ ቦርድም በምትኩ ዋና አሰልጣኝ ለመሾም ከሰሞኑ እንቅስቃሴ ጀምሯል።

ቦርዱ ቀጣዩ የክለቡ አሰልጣኝ እንዲሆኑ
አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ እና አሸናፊ በቀለን ለይቶ ሲያነጋግር ቆይቶ በመጨረሻም ሚዛኑ ወደ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ያመዘነ ይመስላል። እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የሚያቆያቸውን ስምምነት እንደሚፈፅሙ ሲጠበቅ አዲስ ነገር ካልተፈጠረ በቀር ዛሬ አዲስ አበባ ላይ አልያም የፊታችን ረቡዕ ጎንደር ላይ ክለቡ የአሰልጣኙን ሹመት ይፋ እንደሚያደርግ ተሰምቷል።

\"\"