ከፍተኛ ሊግ | የምድብ ሀ ውሎ

ባህር ዳር ላይ በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ቤንች ማጂ ቡና ምድቡን መምራት የቀጠለበትን ድል ሲያሳካ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ሀላባ ከተማ እና ወልዲያም አሸንፈው በፉክክሩ ቀጥለዋል።

ሰበታ ከተማ 1-4 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

03:00 ላይ ጀምሮ ብርቱ ፉክክር ባስተናገደው ጨዋታ በተለይም የጨዋታው የመጀመሪያ 25 ደቂቃዎች ለተመልካች እጅግ አዝናኝ ነበሩ። ጨዋታው ከጀመረ ሁለት ደቂቃ ሳይሞላ ንግድ ባንኮች መሪ መሆን ችለዋል። በረከት ግዛቸው ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ  መታሠቢያ ገዛኸኝ ሊያወጣ ቢሞክርም ተጨርፎ የራሱ መረብ ላይ አርፏል።

\"\"

በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ናትናኤል ጋንጁላ በቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት በጥሩ ሁኔታ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ያስወጣው ኳስ በሰበታዎች በኩል የመጀመሪያው ሙከራ ነበር። በሚያገኙት ኳስ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር የሚያደርጉት ባንኮቹ 5ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ብሩክ ብፁዕአምላክ  ከሳጥኑ የሜዳ ክፍል ወደ ውስጥ ባሻገረው እና ሄኖክ አቻምየለህ ለማስወጣት ሲሞክር ራሱ መረብ ላይ ባረፈው ኳስ መሪነታቸውን አጠናክረዋል።

8ኛው ደቂቃ ላይ የባንኩ ፍቃዱ ደነቀው  ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ኤፍሬም ቀሬ አስቆጥሮት ሰበታን ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሞክሯል። በሁለቱም በኩል ፈጣን ሽግግሮችን ሲያስመለክተን የነበረው ጨዋታ ቀስ በቀስ እየቀዘቀዘ ሲሄድ የንግድ ባንኮች የበላይነት እየታየበት ሄዷል። 32ኛው ደቂቃ ላይም ብሩክ ብፁዕአምላክ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ልዑልሰገድ አስፋው ሳይጠበቅ የመታውና ግብጠባቂው የመለሰበት ኳስ በአጋማሹ የተሻለው የመጨረሻ ሙከራ ነበር።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ኳስ ሲይዙ ጥሩ ለመጫወት የሚሞክሩት ከኳስ ውጪ ግን እጅግ ደካማ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ሰበታ ከተማዎችን የፈተነ አጋማሽ ነበር። 57ኛው ደቂቃ ላይ ትኩረታቸውን በተነጠቁበት ሰዓት አቤል ማሙሽ ግብ አስቆጥሮባቸው ጨዋታውን ይበልጥ አክብዶባቸዋል። ጨዋታውን አረጋግተው የቀጠሉትና ካለፉት ጨዋታዎች እጅግ ተሻሽለው የቀረቡት ንግድ ባንኮች 75ኛው ደቂቃ ላይም ዳግማዊ ዓባይ በጥሩ የአጨራረስ ብቃት ባስቆጠራት ተጨማሪ ግብ ታግዘው ጨዋታውን 4-1 ማሸነፍ ችለዋል።

ቡታጅራ ከተማ 0-2 ቤንች ማጂ ቡና

ረፋድ 05:00 ላይ የጀመረው ጨዋታ እጅግ ቀዝቃዛ እና ለተመልካች ብዙም ሳቢ አልነበረም። በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ለመውሰድ ከሚደረጉ መጠነኛ ፉክክሮች ውጪ ብዛት ያላቸው የጠሩ የግብ ዕድሎች አልተፈጠሩበትም ነበር። ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተሻለ ሁኔታ ሲደርሱ የነበሩት ቤንች ማጂዎች 15ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይም የቡታጅራው ግብጠባቂ ምንተስኖት የግሌ በትክክል ያላራቀውን ኳስ ሲደረብ ያገኘው ብሩክ ወልዱ ማስቆጠር ችሏል።

በየጨዋታው የሚኖራቸውን የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የማይጠቀሙት ቡታጅራዎች 43ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ በተሠራባቸው ጥፋት የፍጹም ቅጣት ምት ቢያገኙም ምንተስኖት ዮሴፍ የመታውን የፍጹም ቅጣት ምት ግብጠባቂው መስፍን ሙዜ መልሶበታል። ይሄም በቡታጅራዎች በኩል ትልቁ አስቆጪ አጋጣሚ ነበር።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ይበልጥ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በቡታጅራ በኩል የተሻለው ሙከራ 51ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ ክንዴ አብቹ ከቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት በጥሩ ሁኔታ ቢሞክርም ግብጠባቂው አስወጥቶበታል። በአቦሎቹ በኩል የተሻለው የግብ ዕድል 57ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጠር ወደግብነት ተቀይሯል። በቀኝ መስመር ከረጅም ርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት ጄይላን ከማል ሲያሻማ ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ የነበረ የሚመስለው ዘላለም በየነ በግሩም የመግባባት ሂደት በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ የበድኑን መሪነት አጠናክሯል። ከዚህ ግብ በኋላም ቡታጅራዎች ለባዶ ከመሸነፍ የሚያድናቸውን ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ጨዋታው በቤንች ማጂ ቡና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ቤንች ማጂ ቡና ነጥቡን 17 አድርሶ መሪነቱን ቀጥሏል።


ወሎ ኮምቦልቻ 0 – 3 ሀላባ ከተማ

መጠነኛ ፉክክር በታየበት የ08:00 ሰዓቱ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል ሀላባቸው የተሻሉ ነበሩ። በ5ኛው ደቂቃም መሪ መሆን የሚችሉበት አጋጣሚ ያገኙ ሲሆን ከግብጠባቂው ጋር የተገናኘው ሙሉቀን ተሾመ ሳይጠቀምበት ቀርቶ ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል። ሀላባዎች ቀስ በቀስ ያልታሰቡ ሙከራዎችን ማድረግ ሲቀጥሉ አቡሽ ደርቤ እና በክሬ መሐመድ ከረጅም ርቀት ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ኳስ መስርቶ በመጫወት ዝግ ያለ የማጥቃት ሽግግር የሚያደርጉት ኮምቦልቻዎች የተሻለውን የግብ ዕድል 28ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጥሩ ከተጋጣሚ ሳጥን የግራ ክፍል ላይ የነበረው ናትናኤል ሌሊሳ ከማቀበል አማራጭ ጋር ጥሩ አጋጣሚ ቢያገኝም ኃይል ባልነበረው እና የውሳኔ ችግር በታየበት ኳስ ወደ ግብ ጠቂው አቅጣጫ መትቶ የግብ ዕድሉን አባክኗል።

\"\"

33ኛው ደቂቃ ላይም ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ሰዒድ ግርማ አስቆጥሮ ሀላባን መሪ ማድረግ ሲችል 43ኛው ደቂቃ ላይ እጅግ አላስፈላጊ የሜዳ ላይ ጉሽሚያዎች እና የዳኛን ውሳኔ ያለመቀበል ችግር  በሚታይበት ሁኔታ የወሎ ኮምቦልቻው አብዱሰላም አማን በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።

ከዕረፍት መልስ የአንድ ሰው ብልጫ የተወሰደባቸው ኮምቦልቻዎች በጨዋታው መረጋጋት ተስኗቸዋል። የተሻለውን የግብ ሙከራም 57ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ኤፍሬም አሰፋ ከቅጣት ምት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው መልሶበታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። አቡሽ ደርቤ እና ሙሉቀን ተሾመ በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ በመጨረሻም አቡሽ ደርቤ አስቆጥሮ የክለቡን መሪነት አጠናክሯል። ጨዋታውን በቁጥጥራቸው ሥር ያደረጉት ሀላባዎች በማራኪ ቅብብል በታጀበው የተረጋጋ አጨዋወታቸው ሲቀጥሉ 72ኛው ደቂቃ ላይም ፎሳ ሰዴቦ ባስቆጠራት ተጨማሪ ግብ ታግዘው ጨዋታውን 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል። 80ኛው ደቂቃ ላይ ከባድ ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ የወጣው የሀላባው ግብ ጠባቂ ስንታየሁ ታምራት በጨዋታው ማብቂያ ላይ ወደ ሆስፒታል አምርቷል።

\"\"

ወልዲያ 2-0 ሰንዳፋ በኬ

በዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ቢታይም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል ግን ወልዲያዎች የተሻሉ ነበሩ። 5ኛው ደቂቃ ላይም የወልዲያው  ብሩክ ጌታቸው ከረጅም ርቀት አክርሮ በመምታት ጥሩ ሙከራ አድርጎ ግብጠባቂው የመለሰበት ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያ ፈታኝ ሙከራ ነበር።

በተረጋጋ አጨዋወት በጥሩ ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ የግብ ዕድል ለመፍጠር የሚሞክሩት ሰንዳፋዎች 16ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል አየለ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው መሳይ ሰለሞን ያደረገውና ግብ ጠባቂው በቀላሉ የያዘው ኳስ በአጋማሹ የተሻለው ሙከራቸው ነበር። በተደጋጋሚ በሚያገኙት ኳስ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚሞክሩት ወልዲያዎች ተሳክቶላቸው 35ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋ ማቲዎስ ባስቆጠረው ግብ መሪ መሆን ሲችሉ 40ኛው ደቂቃ ላይ የቡድን አጋራቸው በድሩ ኑርሁሴን በሠራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።

ከዕረፍት መልስ ሰንዳፋዎች በኳስ ቁጥጥሩ እጅግ ተሻሽለው ሲቀርቡ ወልዲያዎች በበኩላቸው በተወሰደባቸው የተጫዋች የቁጥር ብልጫ ነጥቡን አሳልፈው ላለመስጠት ወደራሳቸው የሜዳ ክፍል ጥቅጥቅ ብለው በመቆም በሚያገኙት ኳስ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ለማድረግ ሲሞክሩ ተስተውሏል። 57ኛው ደቂቃ ላይም ወልዲያዎች በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ በስተመጨረሻ ያገኘው በጋሻው ክንዴ መረቡ ላይ አሳረፈው ተብሎ ሲጠበቅ ተረጋግቶ የመታው ኳስ የግቡን የግራ ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል።

\"\"

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ይውሰዱ እንጂ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ሰንዳፋዎች ይባስ ብሎም 80ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ሊያስተናግዱ ተቃርበው ነበር። ተቀይሮ በመግባት የወልዲያ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ነፍስ የዘራው ኃይሌ ጌታሁን በግሩም ሁኔታ ገፍቶ በወሰደው ኳስ ከግብጠባቂ ጋር ቢገናኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ግን የግብጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ከፍ አድርጎ በመምታት ድንቅ በሆነ አጨራረስ ሲያስቆጥር ጨዋታውም በወልዲያ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።