ቻን | በሊቢያ ብሔራዊ ቡድን ላይ ተጋርጦ የነበረው ችግር ተፈቷል

በኢትዮጵያ ምድብ የምትገኘው ሊቢያ እግርኳስ ፌዴሬሽኗ አጋጥሞት የነበረው ችግር መፍትሔ ሲያገኝ ዛሬም ከአይቮሪኮስት ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ታደርጋለች።

\"\"

በሀገር ውስጥ ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት 7ኛው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒየንሺፕ ውድድር በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር አልጀሪያ እንደሚደረግ ይታወቃል። ለሦስተኛ ጊዜ በውድድሩ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከሞዛምቢክ፣ ሊቢያ እና አዘጋጇ አልጄሪያ ጋር መደልደሉ ይታወሳል። ከሦስቱ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ሊቢያ ደግሞ በብሔራዊ እግርኳስ ፌዴሬሽኑ ላይ በተከሰተ ችግር ከውድድሩ ራሱን ሊያገል እንደሚችል የተሰማውን መረጃ ከሁለት ቀናት በፊት አጋርተናችሁ ነበር። አሁን ከስፍራው ባገኘነው መረጃ መሠረት ግን የተከሰተው ችግር መፍትሔ በማግኘቱ ብሔራዊ ቡድኑ በውድድሩ እንደሚሳተፍ ተረጋግጧል።

ብሔራዊ እግርኳስ ፌዴሬሽኑ የሂሳብ አካውንቱ በፍርድ ቤት በመታገዱ ምክንያት ወጪዎችን ለመሸፈን እቸገራለው ብሎ በይፋ መግለጫ አውጥቶ የነበረ ሲሆን የሀገሪቱ የስፖርት ሚኒስቴር ግን አስፈላጊ የወጪ ድጋፍ ለማድረግ በመወሰኑ ቡድኑ ቱኒዚያ ላይ እያደረገ ያለውን ዝግጅት አጠናክሮ ቀጥሏል ፤ በውድድሩም እንደሚሳተፍ ማረጋገጫ ተሰጥቷል።

በተጨማሪ ዜና ቡድኑ በዛሬው ዕለት ዝግጅቱን እያደረገ በሚገኝበት ቱኒዚያ ከአይቮሪኮስት አቻው ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ ይዟል።

\"\"