የፕሪምየር ሊጉ የበላይ አካል ያስጠናውን ጥናት በተመለከተ መግለጫ ሰጠ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር አንድ ዓመት ተኩል በፈጀ ጊዜ ያስጠናውን ጥናት ለባለ-ድርሻ አካላት ከማቅረቡ በፊት ጥናቱን በተመለከተ ከአጥኚው አካል ጋር በጋራ መግለጫ ሰጥቷል።

2012 ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ሊጉን ራሱ ከማስተዳደሩ ባለፈ በአጠቃላይ የሀገሪቱ እግርኳስ ላይ ያሉትን ሳንካዎች ለማሳየት እና መፍትሔ ለማምጣት ሁለንተናዊ ጥናት እያስጠና እንደነበር በተለያዩ አጋጣሚዎች ማሳወቁ ይታወሳል። አንድ ዓመት ተኩል የፈጀው ጥናትም መገባደዱን ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ ካደረገ በኋላ ጥናቱ ለባለድርሻ አካላት የፊታችን ረቡዕ እና ሐሙስ እንደሚቀርብ አመላክቶ ነበር። ጥናቱ የሚቀርብበት ሲምፖዚየም ከመከናወኑ በፊት ደግሞ የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ፣ ሥራ አስኪያጁ አቶ ክፍሌ ሰይፈ እንዲሁም ጥናቱን ያጠኑት ዶ/ር ጋሻው አብዛ ዛሬ ከሰዓት ለብዙሃን መገናኛ አባላት መግለጫ ሰጥተዋል።

‘ዘርፈ ብዙ የግምገማ ጥናት እና የልማት ፍኖተ ካርታ\’ በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን ጥናት በተመለከተ አጥኚው አካል ማብራሪያ ከመስጠታቸው በፊት መቶ አለቃ ፍቃደ እና አቶ ክፍሌ ጥናቱ እንዲደረግ የተወሰነበትን መንገድ እና አጥኚው አካል የተመረጠበትን ሂደት አስረድተዋል። በቅድሚያ መቶ አለቃ ፍቃደ አክሲዮን ማኅበሩ እንደተቋቋመ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ሥራዎች እየሰራ የክለቦችን እና አጠቃላይ የእግርኳሱን መዋቅር የተመለከቱ ጥያቄዎችን የሚመልስ ጥናት ለማስጠናት የዩኒቨርስቲ ምሁራን የተሳተፉበት ጨረታ ወጥቶ ቴክኒካል እና ፋይናንሻል ዶክመንት በቦርድ ከታየ በኋላ አጥኚው መመረጡን ገልፀዋል። የቦርድ ሰብሳቢው ጥናቱ በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመነሻው እስከ መጨረሻው በእግርኳሱ ዙሪያ ያሉ ነገሮችን የተመለከተ እንደሆነ አመላክተው ከጥናቱ የሚቀርበውን ምክረ-ሀሳብ የመተግበር ችግር እንዳይፈጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን እንዲወጣ አደራ ብለዋል።

\"\"

አቶ ክፍሌ በበኩላቸው በስራ አስኪያጅነት የሚመሩት ማኅበር ተቋቁሞ ራሱን በፋይናንስ ካደራጀ በኋላ ትውልድ መሰረት የሚያደርገው ጥናት ያስፈልጋል በሚል አቅጣጫ ጥናቱ እንዲጠና ወደ እንቅስቃሴ እንደተገባ አመላክተዋል። ይህ ጥናት እንዲጠና ከአንድም ሁለት ጊዜ በወጣው ጨረታ ላይ በአጠቃላት ሰባት ተጫራቾች እንደተሳተፉ የገለፁት አቶ ክፍሌ አንድ ዓመት ተኩል የፈጀው ጥናት የፊታችን ረቡዕ እና ሐሙስ የሚቀርብበትን ወጪ ጨምሮ በአጠቃላይ 2.4 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ሲናገሩ ተደምጠዋል። ጨምረውም ይህ ጥናት ብዙ ጉዳዮችን እንደነካ አመላክተው ጥናቱ ቀርቦ ግብዐት ከተሰበሰበ በኋላ በጥሩ ሁኔታ ታትሞ በገንዘብ ለገበያ እንደሚቀርብ በመግለፅ ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

በመግለጫው ለሁለት ቀናት ረቡዕ እና ሐሙስ በተዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ ሚኒስቴሮች፣ በክልል ደረጃ ስፖርቱን የሚመሩ አካላት እና ኮሚሽነሮች፣ የዩኒቨርስቲ ተወካዮች፣ የክለብ ፕሬዝዳንቶች፣ ሥራ-አስኪያጆች፣ አሠልጣኞች፣ ዳኞች፣ የተጫዋች ወኪሎች (ኢንተርሚዲየሪ)፣ ሚዲያዎች፣ የአካዳሚ ባለሙያዎች እና በርካታ የእግርኳሱ ባለድርሻ አካላት በአጠቃላይ 220 ሰዎች ከመንግስት እስከ ታችኛው የእግርኳሱ አካል ድረስ ያሉ ግለሰቦች እንደሚሳተፉ ተጠቁሟል።

መድረኩን በመቀጠል የተረከቡት ጥናቱን ያጠኑት ዶ/ር ጋሻው አብዛ አክሲዮን ማኅበሩ ጥናቱ እንዲጠና በማድረጉ እና የእሳቸውን ድርጅት በመምረጡ እንዲሁም ጥናቱ ሲጠና የተባበሩ አካላትን በማመስገን ንግግራቸውን ጀምረዋል። በማስከተልም አክሲዮን ማኅበሩ የተቋቋመበትን መንገድ ካነሱ በኋላ ጥናቱ የተሰናዳው በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች እንደሆነ ማስረዳት ጀምረዋል። በጥናቱም ራሱ የኢትዮጵያ አክሲዮን ማኅበሩን የተመለከተ፣ በሊጉ ሥር ያሉ ክለቦችን የዳሰሰ እንዲሁም አክሲዮን ማኅበሩ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር ያለውን ግንኙነት የለየ ሰፊ ሀሳቦች እንደተነሱ ተገልጿል። በአጠቃላይ 33 አጀንዳዎች ያሉት ጥናቱ ሲጠና ደግሞ 5 የመረጃ ማሰባሰቢያ ቋቶች እንደተጠቀሙ ዶ/ር ጋሻው በማብራሪያቸው አስረድተዋል።

በዚህም ዶ/ር ጋሻው ከክለብ አስተዳዳሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የክልል የስፖርት አመራሮች፣ ዳኞች፣ ኤጀንቶች እና ሌሎች አጠቃላት 15 አካላትን ያማከለ የባለድርሻ አካላት ቃለ-ምልልስ ከ90 ሰዎች ጋር መደረጉን፣ የ140 ሀገሮች ተሞክሮ መወሰዱን ፣ 300 ሳይንሳዊ ጥናታዊ ፅሁፎች መዳሰሱን፣ የህግ ማዕቀፎች መፈተሹን እንዲሁም ከክለቦች፣ የእግርኳስ ፌዴሬሽን እና አክሲዮን ማኅበሩ የተገኙ ሰነዶች እንደተወሰዱ ተናግረዋል።

ሰፊ እንደሆነ የተገለፀው ጥናቱም ችግሮችን ከማመላከት ባለፈ የመፍትሔ ምክረ-ሀሳቦችን እንዳካተተ ተገልጿል። በዚህም በ6 የአማራጭ መንገዶች በአጠቃላይ 46 ምክረ-ሀሳቦች እንደተቀመጡ ተጠቁሟል። ጥናቱ ከነገ በስትያ እና ሐሙስ ቀርቦ ተጨማሪ ግብዐቶች የሚገኝ ከሆነ የዳበሩ ሀሳቦች ተካተውበት ቢበዛ በሁለት ሳምንት ውስጥ በመፅሐፍ መልክ ተዘጋጅቶ ለገበያ እንደሚቀርብ ይፋ ሆኗል።

\"\"

በዋናነት የጥናቱን ተግባራዊነት በተመለከተ ደግሞ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በደንብ በጥናቱ ላይ ተመካክረው ውል ካሰሩ በኋላ የክልል የበላይ ኃላፊዎችን ባማከለ መልኩ ስራዎች ወደታች ወርደው እንዲሰሩ እንደሚደረግ ከመድረኩ ሀሳብ ተንፀባርቋል። የሚዲያ አካላት እና ሌሎች ባለ-ድርሻ አካላትም የጥናቱን ምክረ-ሀሳብ መሬት ላይ ለማውረድ የበኩላቸውን እንዲሰሩ የአደራ መልዕክት ተላልፏል።