ቻን | ኢንስትራክተር አብርሃም በቻን ውድድር ቴክኒካዊ ግምገማ የሚያደርጉበት ምድብ ታወቀ

የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር የሆኑት አብርሃም መብራቱ የፊታችን ዓርብ በሚጀምረው የቻን ውድድር ላይ በገምጋሚነት ግልጋሎት የሚሰጡበት ምድብ ተለይቷል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት የቻን ውድድር ከጥር 5 ጀምሮ በአልጄሪያ ይደረጋል። በዚህ መድረክ ላይ ብሔራዊ ቡድናችን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ በኦርጋናይዚን ኮሚቴ እንዲሁም ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በቴክኒካል ኮሚቴ ግልጋሎት እንዲሰጡ ሲመረጡ ኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማ ደግሞ በቪ ኤ አር ዳኝነት እንደሚሳተፉ መገለፁ አይዘነጋም።

\"\"

ከሦስት ግለሰቦች አንዱ የሆኑት የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ከትናንት በስትያ ወደ አልጄሪያ ያመሩ ሲሆን ትናንት እና ዛሬ በተደረገው የውድድሩ ቅድመ ወርክ ሾፕ ላይም ተሳትፎ ማድረጋቸው ታውቋል። በዚህ ወርክ ሾፕ በመጀመሪያው ቀን ያለፈው የቻን ውድድር ግምገማ እንደተደረገበት ሲመላከት በዛሬው የሁለተኛ ቀን ውሎ ደግሞ አዲሱ የጨዋታ መገምገሚያ ፕላትፎርም ስልጠና ተሰጥቶበታል።

\"\"

ከኢትዮጵያ የተመረጡት ኢንስትራክተር አብርሃምን ጨምሮ ከ10 የተለያዩ ሀገራት የመጡት ባለሙያዎችም ከደቂቃዎች በፊት ትኩረት ሰጥተው ቴክኒካዊ ግምገማ የሚያደርጉበት ምድብ ተለይቷል። በዚህም ኢንስትራክተር አብርሃም ከዩጋንዳ ከተመረጡት ኤድጋር ዋትሰን ጋር በጣምራ በኦራን ስታዲየም የሚደረጉትን የምድብ 4 ጨዋታዎች እንዲገመግሙ መመደባቸው ታውቋል።