ጥቂት መረጃዎች ስለ ብሔራዊ ቡድናችን ስብስብ…

በአልጄሪያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የቻን አፍሪካ ዋንጫ ሊጀመር የቀናት ዕድሜ ብቻ ቀርተውታል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዚህ ውድድር ለሦስተኛ ጊዜ ለመሳተፍ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል። እኛም የብሔራዊ ቡድናችንን የመጨረሻ ተመራጭ 26 ተጫዋቾች የተመለከቱ መረጃዎችን በተከታዩ መልኩ አቅርበናል።

👉 ግብ ጠባቂዎች

በዚህኛው የመጫወቻ ስፍራ በክለባቸው በወጥነት የመሰለፍ ዕድልን እያገኙ ያሉ ኢትዮጵያዊ የግብ ዘቦችን ፈልጎ ማግኘት እጅግ ከባድ መሆኑን ተከትሎ በተነፃፃሪነት ከዚህ ቀደም የብሔራዊ ቡድን አባል የነበሩት በረከት አማረ እና ፋሲል ገብረሚካኤል እንዲሁም ጥሩ የሆነ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘውን ባህሩ ነጋሽ የስብስቡ አካል ሆነዋል።

ፋሲል ገብረሚካኤል (ባህር ዳር ከተማ)

ሁለተኛ የውድድር ዘመኑን በባህር ዳር ከተማ እያሳለፈ የሚገኘው ፋሲል ገብረሚካኤል የውድድር ዘመኑን የመክፈቻ ጨዋታ ለቡድኑ በቋሚዎቹ መሃል ሆኖ ቢጀምርም ቀጥለው በነበሩ አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ግን ስፍራውን በአይቮሪኮስታዊው ኤላዛር ቴፔ ተነጥቆ ነበር። ነገር ግን ኤላዘር ለሀገራዊ ግዳጅ ወደ ሃገሩ ማቅናቱን ተከትሎ ባገኘው ዕድል ቦታውን በቋሚነት መረከብ ችሏል። በሊጉ በ7 ጨዋታዎች የባህር ዳርን ግብ መጠበቅ የቻለው ፋሲል በ3 ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር መውጣት ችሏል።

ባህሩ ነጋሽ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ረዘም ላሉ ዓመታት ማሳለፍ የቻለው ባህሩ ነጋሽ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ላይ ተሳትፎ ከማድረግ በዘለለ በዋናው ቡድን እምብዛም የተሰላፊነት ታሪክ አልነበረውም። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን ምንም እንኳን ሁለተኛ ተመራጭ ግብ ጠባቂ በመሆን የውድድር ዘመኖችን ቢጀምርም የቡድኑ ተቀዳሚ ግብ ጠባቂዎች አቋም ሲዋዥቅ የሚሰጡትን ዕድሎች በሚገባ እየተጠቀመ ይገኛል። ዘንድሮም የዩጋንዳዊው ቻርልስ ሉኩዋጎ ተጠባባቂ በመሆን የጀመረው ግብ ጠባቂው ቻርልስ ሉኩዋጉ ለስህተቶች ተጋላጭነቱ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በተለይም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልቂጤ ከተማ ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ያሳየውን ደካማ ብቃት ተከትሎ ወደ ተጠባባቂ ወንበር መውረዱን ተከትሎ የመሰለፍ ዕድሉን ያገኘው ባህሩ ነጋሽ በሊጉ እስካሁን ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ምንም ግብ ሳያስተናግድ እጅግ ድንቅ ብቃት ላይ ሆኖ ነው ለሀገራዊ ግልጋሎት ብሔራዊ ቡድኑን የተቀላቀለው።

በረከት አማረ (ኢትዮጵያ ቡና)

የውድድር ዘመኑን በጥሩ ብቃት መጀመር ችሎ የነበረው በረከት አማረ በሊጉ የመጨረሻዎቹ ሳምንታት ግን ኢትዮጵያ ቡናዎች በክረምቱ የዝውውር መስኮት የመጨረሻ ቀናት ባስፈረሙት ቦትስዋናዊው ኢዚቅኤል ሞራኬ ቦታውን ተነጥቋል። ዘንድሮ በ8 የሊግ ጨዋታዎች መሰለፍ የቻለው በረከት አማረ በ4(50%) በሚሆኑት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር የወጣ ሲሆን በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች በቀላሉ ለተጋጣሚ ዕድሎችን በሚሰጠው የቡድኑ መከላከል መነሻነት በርከት ያሉ ጥራታቸው የላቁ ሙከራዎችንም ለመጋፈጥ ቢገደድም በአስደናቂ ብቃት ኳሶቹን ሲያድን ተስተውሏል። ጥሪ ከተደረገላቸው ግብ ጠባቂዎች የተሻለ የእግር አጠቃቀም ባለቤት የሆነው በረከት ቡድኑ በዚህኛው መንገድ መጫወትን ከመረጠ የተሻለው አማራጭ እሱ ይመስላል።

\"\"

👉 ተከላካዮች

ባለፉት ጥቂት አመታት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ መስመር ተሰላፊ የነበሩት ያሬድ ባየህ እና አስራት ቱንጆን በጉዳት ያጡት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በቀደመ ብቃታቸው ላይ የማይገኙ ነባር ተጫዋቾችን ከአዲስ መጪዎች ጋር ለማሰባጠር ሞክረዋል።

ዓለምብርሃን ይግዛው (ፋሲል ከነማ)

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በፋሲል ከነማ በነበራቸው ቆይታ ከታችኛው ቡድን ወደ ዋናው ቡድን አሳድገዋቸው ተፅዕኖ መፍጠር ከቻሉ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ዓለምብርሃን በሂደት ከቀደመው የመስመር አጥቂነት ሚናው ወጥቶ አሁን ላይ ወደ ጥሩ የመስመር ተከላካይነት እየተሸጋገረ ይገኛል። የእንየው ካሳሁን መልቀቅን ተከትሎ የፋሲልን የቀኝ መስመር ተከላካይ ስፍራን የግሉ ያደረገው አለምብርሃን ፋሲል እስካሁን ባደረጋቸው አስራ ሦስቱም የሊግ ጨዋታዎች መሰለፍ ሲችል በዚህም 1170 ደቂቃዎችን መጫወት ችሏል። ሁለት ለግብ የሆኑ ኳሶችን በስሙ ያስመዘገበው ዓለምብርሃን በቅርቡ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ጥሪ በኋላ በዋናው ቡድን የመጀመሪያ ተሳትፎውን ለማድረግ እየተዘጋጀ ይገኛል።

ብርሃኑ በቀለ (ሀዲያ ሆሳዕና)

ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት በሊጉ በቀኝ መስመር ተከላካይነት ሆነ የቀኝ መስመር ተመላላሽነት ሚና ፍፁም እያደጉ ከመጡ ተጫዋቾች መካከል ብርሃኑ በቀለ ቀዳሚው ተጫዋች ነው። ጊዜውን ጠብቆ በማጥቃት ላይ በመሳተፍ ለቡድን አጋሮቹ ዕድሎችን በመፍጠር እንዲሁም በመከላከሉ ወቅት በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች በቀላሉ የማይረታው ብርሃኑ በቀለ በሊጉ በ11 ጨዋታዎች በድምሩ 990 ደቂቃዎች አንድ ለግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። ምንም እንኳን በግቦች ላይ ያለው ተሳትፎ አነስተኛ ቢመስልም የሆሳዕናን ጨዋታ ለተከታተለ ከብርሃኑ የሚነሱ ኳሶች የአጥቂው መስመር ስል ቢሆን ከዚህ በላይ ወደ ግብነት በተቀየሩ ነበር።

ሱሌይማን ሀሚድ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

በተከላካይ መስመር ላይ ከተካተቱ ተጫዋቾች መካከል ከጥቂት ባለልምዶቹ መካከል የሚጠቀሰው ሱሌይማን ሀሚድ አስራት ቱንጆ በጉዳት ምክንያት በስብስቡ አለመኖሩን ተከትሎ የቀኝ መስመር ተከላካይነት ሚናን በውድድሩ እንደሚወጣ ይጠበቃል። በፈረሰኞቹ ቤት ሁለተኛ የውድድር ዘመኑን እያሳለፈ የሚገኘው ሱሌይማን በዘንድሮው የውድድር ዘመን በ9 ጨዋታዎች መሰለፍ ሲችል በድምሩ 749 ደቂቃዎችን ሲጫወት አንድ ለግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

ረመዳን የሱፍ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከአበባው ቡጣቆ በኋላ በግራ መስመር ተከላካይ ስፍራ ላይ የነበረባቸውን የተፈጥሮአዊ ተጫዋቾች እጥረት ለመድፈን በማለም ያስፈረሙት ረመዳን የሱፍ በፈረሰኞቹ ቤት ጥሩ አጀማመርን እያደረገ ይገኛል። በ10 ጨዋታዎች በአጠቃላይ በሜዳ ላይ ለ900 ደቂቃዎች ቆይታ ማድረግ የቻለው ረመዳን አንድ ለግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። በብሔራዊ ቡድኑ ከአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ዘመን አንስቶ የግራ መስመር ተከላካይ ስፍራን የግሉ ያደረገው ረመዳን በዚህም ውድድር ቦታውን እንደሚያስጠብቅ ሲጠበቅ ያለውን የማጥቃት ነፃነት ተጠቅሞ ለቡድኑ ማጥቃት የግራ ወገን ስፋት ይጨምራል ተብሎ ይታመናል።

ገዛኸኝ ደሳለኝ (ኢትዮጵያ ቡና)

በሊጉ በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ተሰለፎ በድምሩ 151 ደቂቃዎችን የተጫወተው ገዛኸኝ ደሳለኝ ወደ አልጄሪያ የሚያቀናው ስብስብ አካል መሆኑ ብዙዎችን ያስገረመ ምርጫ ነበር። በዕድሜ እርከን ቡድኖች ውስጥ በአጥቂ መስመር በመጫወት የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው ገዛኸኝ አሁን ላይ ግን በመሀል ሆነ በመስመር ተከላካይነት እየተጫወተ ይገኛል። ምናልባት ከረመዳን የሱፍ ውጪ ተፈጥሮአዊ የግራ እግር ተጫዋች በተከላካይ መስመሩ ለሌለው ስብስብ ገዛኸኝ ከሁለገብነቱ ጋር ተዳምሮ አማራጭ ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል።

ጊት ጋትጉት (ሲዳማ ቡና)

አዲስ አበባ ከተማን ለቆ ሲዳማ ቡናን ከተቀላቀለ ወዲህ ባሉት ዓመታት ፈጣን እምርታን እያሳየ የነበረው ጊት ጋትጉት ዘንድሮው በሊጉ በሲዳማ ቡና መለያ በ10 ጨዋታዎች በድምሩ 898 ደቂቃዎችን ማሳለፍ ችሏል። ከፈጣን ዕድገቱ ማግስት መጠነኛ መቀዛቀዝ ውስጥ የገባው ጊት በዘንድሮው የውድድር ዘመን በሲዳማ እያሳለፈ የሚገኘው ጊዜ አመርቂ የሚባል አይደለም። በሊጉ ከለገጣፎ ለገዳዲ ቀጥሎ ሁለተኛው ደካማ የመከላከል መስመር ባለቤት በሆኑት ሲዳማ ቡናዎች የመከላከል አወቃቀር ውስጥ የሚሰራቸው የቦታ አያያዝ ሆነ የውሳኔ አሰጣጥ ስህተቶች ቡድኑን ዋጋ ሲያስከፍሉ የተመለከትን ሲሆን ይህ በግዴለሽነት ከሚሰራቸው ጥፋቶች ጋር ተዳምሮ ያልተረጋጋ ጊዜ ውስጥ እንዲገኝ አድርገውታል።

ሚሊዮን ሰለሞን (አዳማ ከተማ)

በሊጉ በወጥነት ብቃታቸውን ስለሚያሳዩ ተጫዋቾች ስናስብ በፍጥነት ወደ ምናባችን ከሚመጡ ተጫዋቾች አንዱ የአዳማው ሚሊዮን ሰለሞን ነው። በጥሩ መልኩን ውድድር ዘመኑን ቢጀምርም 4ኛ ሳምንት አዳማ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲገጥም ጉዳት ማስተናገዱን ተከትሎ ተከላካዩ በርከት ላሉ ሳምንታት በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ቢርቅም ከ11ኛ የጨዋታ ሳምንት አንስቶ አዳማ ባደረጋቸው አራት መርሃግብሮች(ተስተካካይ ጨዋታን ጨምሮ) ላይ ተሰልፎ መጫወት ችሏል። ሚሊዮን በጉዳት ባልነበረባቸው ጨዋታዎች የአዳማ መከላከል ፍፁም ተዳክሞ ነጥቦችን ለመያዝ እንኳ ተቸግሮ ቢቆይም ከሚሊዮን መመለስ በኋላ በነበሩ ጨዋታዎች ግን ይህ ሂደት ተሻሽሎ ተመልክተናል። እጅግ ጠንቃቃ ተከላካይ እንደሆነ እያሳየ የሚገኘው ሚሊዮን ጥንቃቄ ላይ ላተኮረ መከላከል ሆነ ኳስን መስርቶ ለመጫወት የሚያስችሉ ክህሎቶች የታደሉት ተጫዋች ነው። በስምንት ጨዋታዎች ተሳትፎ ማድረግ የቻለው ሚሊዮን ሰለሞን በስሙ አንድ ግብ የሆነችም ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። ሚሊዮን ባለፉት ሁለት ዓመታት እያሳየ ከሚገኘው ብቃት አንፃር በመጀመሪያ ተሰላፊነት ለመጀመር በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ አዕምሮ ውስጥ መመላለሱ የሚቀር አይደለም።

አስቻለው ታመነ (ፋሲል ከነማ)

ገና በለጋ ዕድሜው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በርካታ ጨዋታዎችን ማድረግ የቻለው አስቻለው ታመነ ዘንድሮም በፋሲል ቤት በግሉ ጥሩ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። ምንም እንኳን ሊጉ ለውድድሩ ከመቋረጡ በፊት ቡድኑ ያደረጋቸው የመጨረሻ ሦስት የሊግ ጨዋታዎች በጉዳት ያመለጡት አስቻለው ወደ ቻኑ የአፍሪካ ዋንጫ ሲጓዝ በሙሉ ጤንነት ላይ የመገኘቱ ጉዳይ አጠራጥሯል። ፍፁም በሆነ የራስ መተማመን የሚጫወተው አስቻለው በጫና ውስጥ ሆኖ እንኳን ኳሶቹን ከመከላከል ሲሶ ይዞ ለመውጣት ያለው ተነሳሽነት እና በመከላከል የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ያለው የበላይነት እጅግ አስገራሚ ነው። ዘንድሮ ለፋሲል 9 ጨዋታዎችን ማድረግ የቻለው አስቻለው የጤንነቱ ሁኔታ አስተማማኝ ከሆነ በመሀል ተከላካይ ስፍራ በቋሚነት መጀመሩ አይቀሬ ነው።

ምኞት ደበበ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

በፈረሰኞቹ ቤት በ2014 የወድድር ዘመን ከጋናዊው ፍሪምፖንግ ሜንሱ ጋር በመሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ የመሀል ተከላካይ ስፍራ ላይ የፈጠሩት ጥምረት ፈረሰኞቹን ለሊጉ ክብር ማብቃት መቻላቸው አይዘነጋም። ዘንድሮ ግን የምኞት ደበበ አበርክቶ የተገደበ ሆኗል። በስድስት ጨዋታዎች በተጠባባቂ ወንበር ለመጀመር የተገደደው ምኞት እስካሁን በሊጉ በ5 ጨዋታዎች በድምሩ ለ450 ያክል ደቂቃዎች ብቻ በሜዳ ላይ ተመልክተነዋል። ቡድኑ በ6ኛ የጨዋታ ሳምንት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ በኃላ ፈረሰኞቹ ካደረጓቸው የመጨረሻ ስድስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ የተሰለፈው ተጫዋቹ ወደ ቻን ውድድር ሲያቀና ከጨዋታ ቅኝት አንፃር ጥያቄ ውስጥ ሆኖ ነው።

ፈቱዲን ጀማል (ባህር ዳር ከተማ)

ጥሩ የሚባል የመጀመሪያ ዙርን እያሳለፉ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች ጠንካራ የመከላከል ክፍልን መገንባት ሲችሉ በዚህም የፈቱዲን ጀማል እና ያሬድ ባየህ አስደናቂ ጥምረት ወሳኙን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል። በዘንድሮው የውድድር ዘመን በ10 ጨዋታዎች በቋሚነት የተሰለፈው ፈቱዲን በ900 የጨዋታ ደቂቃዎች ከመከላከል ባለፈ በቀደመው ጊዜ የሚታወቅበትን የማጥቃት ደመነፍስ እያስመለከተን ይገኛል።

👉 አማካዮች

ከሀገር ውጭ ከሚጫወተው ሽመልስ በቀለ ውጭ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ በራቁት በዛብህ መለዮ እና ሱራፌል ዳኛቸው ምትክ ሌሎች ተጫዋቾች በተተኩበት የመሀል ክፍል ላይ ፉዓድ ፈረጃ ዕድሉን ማግኘት ከቻለ ጉልቶ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ጋቶች ፖኖም (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

በመጨረሻዎቹ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ላይ እጅግ ድንቅ ብቃታቸውን ካሳዩ ተጫዋቾች ተርታ የሚመደበው ጋቶች ፖኖም በተለያዩ ምክንያቶች በክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን በቂ የጨዋታ ደቂቃን እየተሰጠው አይገኝም። በድምሩ በ10 ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎን ያደረገው ጋቶች በአጠቃላይ ሜዳ ላይ የቆየባቸው ደቂቃዎች ብዛት 656 ብቻ ነው። በዚህም ቆይታው አንድ ግብ እና አንድ ለግብ የሆነ ኳስ በስሙ ማስመዝገብ ችሏል። ከተከላካዮች ፊት ባሉት የአማካይ ስፍራ ቦታ ላይ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን እያፈራረቁ እየተጠቀሙ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጋቶች ሜዳ ላይ በሚኖርባቸው ጨዋታዎች አማካይ ክፍሉ በተለየ ኃይል ሲንቀሳቀስ እያስተዋልን እንገኛለን። በብሔራዊ ቡድኑ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየሰጠው ካለው አበርክቶ አንፃር በመጀመሪያ ተሰላፊነት እንደሚጀምር ይጠበቃል።

ይሁን እንደሻው (ፋሲል ከነማ)

ፋሲል ከነማ እንደ ቡድን በዘንድሮው የውድድር ዘመን ደካማ ጊዜን እያሳለፈ ቢገኝም በ11 ጨዋታዎች በድምሩ 892 ደቂቃዎችን መጫወት የቻለው ይሁን እንደሻው ጥረት ግን የሚደነቅ ነው። የቡድኑን የመከላከል ሚዛን በመጠበቅ ሆነ ለቡድን አጋሮቹ የተመጠኑ አጭር ፣ መካከለኛ እና ረጃጅም ኳሶች ስርጭትን የሚዘውረው ይሁን ለቡድኑ ወሳኝ ሚናን እየተወጣ ይገኛል። የኳስ እንቅስቃሴን የሚወስነው ይሁን ኳስን መቆጣጠር ለሚሻ አልያም በረጃጅም ኳሶች ለመጫወትም የተመቸ መሆኑ ለአሰልጣኝ ውበቱ መሀል ሜዳ ላይ የተለየ አማራጭ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

\"\"

አለልኝ አዘነ (ባህር ዳር ከተማ)

በሊጉ የመክፈቻ የጨዋታ ዕለት የቡድናቸውን ወሳኙን አማካይ ፍቅረሚካኤል ዓለሙን በረጅም ጊዜ ጉዳት ያጡት ባህር ዳር ከተማዎች ይህን ስፍራ ለመድፈን የተለያዩ አማራጮችን ሲሞክሩ ቢቆዩም አለልኝ አዘነ ግን ትክክለኛው ተተኪ ይመስላል። በሊጉ በ12 ጨዋታዎች ላይ በመሳተፍ በባህር ዳር መለያ 920 ደቂቃዎችን የተጫወተው አለልኝ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ የተሻለ አበርክቶን ለቡድኑ አየሰጠ ይገኛል። እስካሁን አንድ ለግብ የሆነ ኳስን አመቻችቶ ማቀበል የቻለው አለልኝ እንቅስቃሴን የሚያቋርጥበት እንዲሁም ከርቀት ወደ ግብ የሚልካቸው ኳሶች ጠንካራ መገለጫው ናቸው።

ከነዓን ማርክነህ (መቻል)

ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቆ ወደ መቻል ካመራ በኋላ በ13 ጨዋታዎች በድምሩ 901 ደቂቃ የተጫወተው ከነዓን ማርክነህ በሊጉ አንድ ግብን ብቻ ማስቆጠር ችሏል። በክረምቱ ከወገብ በላይ ጥራታቸው የላቁ ተጫዋቾችን ማሰባሰብ የቻሉት መቻሎች ከነዓን ማርክነህን ጨምሮ ከአብዛኞቹ ተጫዋቾች የሚፈልጉትን እያገኙ አይገኝም። በ8 ቁጥር ሚና ከሦስቱ አማካዮች አንዱ በመሆን እያገለገለ የሚገኘው ከነዓን በማጥቃት ካለው አበርክቶ መቀዛቀዝ ባለፈ በመከላከሉ ያለው ተሳትፎ አናሳ መሆኑ በመቻል የቡድን ሚዛን ላይ ተፅዕኖ ሲፈጥር አስተውለናል።

መስዑድ መሐመድ (አዳማ ከተማ)

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ወደ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ከመጡበት ጊዜ አንስቶ መስዑድ መሐመድ በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ከማይቀሩ ስሞች መካከል አንዱ ሆኗል።በሜዳ ላይ ካለው የጨዋታ አረዳድ ባለፈ ተጫዋቾችን በምሳሌ የሚመራው መስዑድ ዘንድሮም በአዳማ ቤት ጥሩ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። በ12 ጨዋታዎች በድምሩ 929 ደቂቃዎችን ተሰልፎ የተጫወተው መስዑድ አንድ ግብ ሲያስቆጥር አንድ ኳስ ደግሞ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። በዚህ ውድድርም በንፅፅር በወጣት ተጫዋቾች ለተሞላው ስብስብ በሜዳ ላይ ሆነ ከሜዳ ውጭ የመሪነት ሚናውን ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ወንድማገኝ ኃይሉ (ሃዋሳ ከተማ)

የ2013 የውድድር ዘመን የሊጉ የዓመቱ ምርጥ ወጣት ተጫዋች የነበረው ወንድማገኝ ሃይሉ የዘንድሮው የውድድር ዘመን የመጀመሪያዎቹ 13 የጨዋታ ሳምንታት እምብዛም ሊያስታውሳቸው የሚፈልጋቸው አልነበሩም። ከውል ስምምነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ከአሳዳጊ ክለቡ ጋር እሰጣ አገባ ውስጥ የሰነበተው ወንድማገኝ በሊጉ በ9 ጨዋታዎች በድምሩ 712 ደቂቃዎችን መጫወት ቢችልም በግቦች ላይ ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ተሳትፎ ሳያደርግ ያጠናቀቀበት ነበር። ፈጣን ዕድገቱን ለማስቀጠል እየተቸገረ የሚገኘው ወንድማገኝ በዚህ ወድድር የመሰለፍ ዕድሉን ካገኘ የእግርኳስ ህይወቱን ዳግም ለማቃናት ይጠቀምበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ፉዓድ ፈረጃ (ባህር ዳር ከተማ)

በዘንድሮ የውድድር ዘመን እንደ አዲስ የተወለደ የሚመስለው ፉዓድ ፈረጃ እጅግ አስደናቂ ጊዜን በጣናዎቹ ሞገዶች እያሳለፈ ይገኛል። አዳማን ከለቀቀ ወዲህ የቀደመ ማንነቱን ለማግኘት ተቸግሮ የቆየው ፉዓድ ዘንድሮ በ13 ጨዋታዎች 4 ግቦችን ሲያስቆጥር 1 ግብ የሆነችንም ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። ፈጣን ከመስመር የሚነሱ ሯጮችን ወደ ጥልቀት በማስገባት ማጥቃትን ተቀዳሚ ምርጫቸው ላደረጉት ባህር ዳር ከተማዎች ፈዓድ ፈረጃ ይህን የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚያስጀምረው ቁልፍ ሰው ከመሆን ባለፈ ዘግይቶ ወደ ሳጥን በመድረስ ግቦችንም እያስቆጠረ ይገኛል። በጨዋታዎች በአስደናቂ ትጋት ሲጫወት የምናስተውለው ፉዓድ ጨዋታዎችን በጀመረበት የትጋት ደረጃ በመጨረስ ረገድ ግን ውስነቶች አሉበት። በዚህም ከተጫወተባቸው 13 ጨዋታዎች በሰባቱ ጨዋታዎች ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል።

👉 አጥቂዎች

አቡበከር ናስር በተገቢነት እንዲሁም ዳዋ ሆቴሳ በጉዳት እና ጌታነህ ከበደን ደግሞ በሥነምግባር ጉዳይ ያላካተተው ስብስቡ በውድድሩ የተሻለ ርቀት ለመጓዝ አዳዲስ ጀግኖችን ይፈልጋል።

ይገዙ ቦጋለ (ሲዳማ ቡና)

አምና በ16 ግቦች የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የነበረው ይገዙ ቦጋለ ዘንድሮ በሊጉ እያሳለፈ የሚገኘው ጊዜ ወጥነት የጎደለው ሆኗል። በ12 ጨዋታዎች በድምሩ 1047 ደቂቃዎችን ተሰልፎ መጫወት የቻለው አጥቂው ስድስት ግቦችም ማለትም በ176 የጨዋታ ደቂቃዎች አንድ ግብ እያስቆጠረ ይገኛል። ይህም አምና በ160 ደቂቃ አንድ ግብ ከሚያስቆጥርበት ንፃሬ አንፃር ጭማሬን አሳይቷል። ስድስት የሊግ ግቦችን ሲያስቆጥር በሁለት ጨዋታዎች ሁለት ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ሲችል የተቀሩት ሁለት ግቦች ደግሞ በተለያዩ ጨዋታዎች የተገኙ ነበሩ። ከጨዋታ ጨዋታ ወጥ የሆነ ብቃት ለማሳየት በተቸገረው ሲዳማ ቡና ውስጥ እየተጫወተ የሚገኘው ይገዙ የቡድኑ የሚዋዥቅ የሜዳ ላይ ብቃት እሱ ላይም ተፅዕኖ እያሳደረበት ይገኛል በአመዛኙ የሊጉ የእስካሁን ጉዞ የሰልሀዲን ሰዒድን ጉዳት ተከትሎ ብዙ የተጠበቀበት ይገዙ በቂ ግልጋሎት ለቡድኑ እየሰጠ አይገኝም። በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሚመራው ስብስብ ውስጥም የጌታነህ ከበደ ከስብስቡ መለየት ተከትሎ ብሔራዊ ቡድን አሁን ላይ ያለው ብቸኛ ተፈጥሮአዊ የዘጠኝ ቁጥር ተጫዋች ይገዙ ቦጋለ መሆኑን ተከትሎ በውድድሩ ከእሱ ብዙ ይጠበቃል።

ቸርነት ጉግሳ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ሁለተኛ የውድድር ዘመኑን በፈረሰኞቹ ቤት እያሳለፈ የሚገኘው ቸርነት በዘንድሮው የውድድር ዘመን በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣርያ ጀምሮ የተሻለ ብቃቱን የሚያሳይበት የውድድር ዘመን ስለመሆኑ ፍንጭ መስጠቱ ይታወሳል። በሊጉም በ12 ጨዋታዎች በድምሩ 965 ደቂቃን መጫወት ሲችል ሦስት ግቦች እና ሦስት ለግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።ይህም አምና በአጠቃላይ የውድድር ዘመኑ ከነበረው ሁለት የግብ ተሳትፎ አንፃር ዘንድሮ ፍፁም ስለመሻሻሉ ማሳያ ነው። በዚህም የቻን ውድድር ምናልባት በብሔራዊ ቡድን ራሱን የሚያሳይበትን ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

አማኑኤል ገ/ሚካኤል (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

በአንድ ወቅት በሊጉ ከፍተኛ አስቆጣሪ ዝርዝር ውስጥ ከዓመት ዓመት ተፎካካሪ የነበረው አማኑኤል ገ/ሚካኤል አሁን ከግቦቹ ይልቅ ሌሎች አበርክቶዎቹ ጎልተው የሚነሱለት ተጫዋች ሆኗል። በ12 የሊግ ጨዋታዎች በድምሩ 842 ደቂቃዎችን የተጫወተው አማኑኤል ገ/ሚካኤል አራት ግቦችን ሲያስቆጥር አንድ ለግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። በግቦች ላይ ካለው ተሳትፎ በላቀ አማኑኤል ከኳስ ውጭ የሚያደርጋቸው ሩጫዎች የተጋጣሚን የመከላከል መዋቀር በመረበሽ እንዲሁም ቡድኑ ኳስ ሲያጣ ከኳሷ በተቃራኒ ያለው ትጋት እጅግ የሚደንቅ ነው ይህም በቅዱስ ጊዮርጊስ አጨዋወት ውስጥ ወሳኝ ሚናን እንዲወጣ አስችሎታል። ፊት መስመር ላይ ከተመረጡት ተጫዋቾች ውስጥ የተሻለ የብሔራዊ ቡድን ልምድ ያለው አማኑኤል ፊት መስመሩን የመምራት ትልቅ ሀላፊነት በትከሻው ወድቋል።

ኪቲካ ጅማ (ኢትዮጵያ መድን)

በሊጉ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከተመለከትናቸው እና ድንቅ ብቃታቸውን እያሳዩ ከሚገኙ አዳዲስ ፊቶች መካከል ኪቲካ ጅማ ቀዳሚው ነው። በሊጉ የመክፈቻ ዕለት ኢትዮጵያ መድን አሰቃቂ ሽንፈትን ሲያስተናግድ በ65ኛው ደቂቃ ያሬድ ዳርዛን ተክቶ ወደ ሜዳ በመግባት ለፕሪምየር ሊጉ ተመልካች ራሱን ያስተዋወቀው ኪቲካ ከዚያ ጨዋታ በኃላ ወደ ኋላ አልተመለከተም። በ13 የሊግ ጨዋታዎች በድምሩ ለ1052 ደቂቃ ተሰልፎ መጫወት የቻለው ኪቲካ በስድስት ግቦች ላይ (3 ግቦች ፣ 3 ለግብ የሆኑ ኳሶችን በማመቻቸት) ጥሩ የሚባልን ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። ከመስመር መነሻውን ያድርግ እንጂ ከፊት አጥቂ ጀርባ ባሉት ስፍራዎች በነፃነት እየገባ የሚጫወተው ኪቲካ በግሉ ነገሮችን ለመፍጠር ያለው ድፍረት እንዲሁም ከቡድን አጋሮቹ ጋር በቡድን ጨዋታ ወቅቅ ያለው ተግባቦት እጅግ አስደናቂ ነው።

ዱሬሳ ሹቢሳ (ባህር ዳር ከተማ)

ከአዳማ ከተማ የዕድሜ እርከን ቡድን የተገኘው ዱሬሳ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ከመጣ በኋላ በስፋት ከተጠባባቂ ወንበር እየተነሳ ጨዋታዎች ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚታትር ተጫዋች የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ ግን ከባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ተመራጭ ተጫዋቾች አንዱ ሆኗል። በአዲሱ ክለቡ በ13 ጨዋታዎች 1113 ደቂቃዎችን መጫወት የቻለው ዱሬሳ በሊጉ 5 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። መነሻውን ከመስመር በማድረግ ወደ ውስጥ እየሰበረ ለመግባት የሚጥረው ተጫዋቹ ከውሳኔ አሰጣጥ ጋር የተወሰኑ ችግሮች ቢኖሩበትም ዘንድሮ ግን በውሃ ሰማያዊው ቤት ጥሩ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል።

ቢኒያም በላይ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ከአውሮፖ ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ከተመለሰ ወዲህ ዳግም ራሱን ወደ ብሔራዊ ቡድን ለመመለስ ሲተጋ የነበረው ቢኒያም በላይ ዘንድሮ በፈረሰኞቹ ቤት እያሳየ ባለው ብቃት መሻቱን አሳክቷል። በፈረሰኞቹ መለያ በ12 ጨዋታዎች 1005 ደቂቃን ማሳለፍ የቻለው ቢኒያም በስሙ አንድ ግብ ሲያስመዘግብ ሥስት ለግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። በፈረሰኞቹ ቤት ሲጀምር አምና በመቻል ጥቅም ላይ ይውል እንደነበረው ከመስመር እየተነሳ ሲጫወት የነበረ ቢሆንም በተለይ የዳዊት ተፈራን ጉዳት ተከትሎ የተዳከመውን የቡድኑን የመሀል ለመሀል የመፍጠር አቅም ለማሻሻል ወደ መሀል ተስቦ እንዲጫወት እየተደረገ ሲገኝ ከዚህ ቀደም ከነበረው የብሔራዊ ቡድን ልምድ አንፃር ስብስቡን ይጠቅማል ተብሎ ይታመናል።