የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ድሬዳዋ ከተማ ድል ሲቀናው ልደታ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ ወሳኝ ድል ያሳካበት እንዲሁም ልደታ ክፍለ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ 1ለ1 የተለያዩበት ውጤቶች ተመዝግበዋል።

የ2015 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በሀዋሳ ከተማ እየተደረገ የ12ኛ ሳምንት የሦስተኛ እና የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎችን ዛሬ በማስተናገድ ተጠናቋል። ረፋድ 4 ሰዓት ላይ ድሬዳዋ ከተማ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ሦስት ጎሎችን አስመልክቶን በመጨረሻም የምስራቁን ክለብ ባለ ድል በማድረግ ፍፃሜውን አግኝቷል።

ጥሩ የመሸናነፍ ፉክክርን ያስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ተመጣጣኝ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን የተስተዋለበት ቢሆንም ከሙከራዎች አንፃር ግን ድሬዳዋ ከተማ የተሻለ ሆኖ ቀርቧል። ከመስመር በሚነሱ እና በአጥቂ መስመሩ ላይ ለነበሩት ሊዲያ ጌትነት እና ስራ ይርዳው በማሻገር ለመጫወት የሚታትሩት ድሬዎች 9ኛው ደቂቃ ላይ በዚህ የጨዋታ መንገድ በሊዲያ ጌትነት አማካኝነት ጎል አስቆጥረው መምራት ጀምረዋል። ግብ ካስተናገዱ በኋላ በመልሶ ማጥቃት ሽግግር ከወትሮ እንቅስቃሴያቸው በተለየ መልኩ በመጫወት ጎል ለማስቆጠር ጥረት ውስጥ የገቡት ንፋስ ስልኮች በበኩላቸው በበሬዱ በቀለ የ37ኛ ደቂቃ ጎል ወደ አቻነት ተመልስዋል።


ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ድሬዳዋ ከተማዎች አንፃራዊ የበላይነትን ሲያሳዩ የነበረ ሲሆን በይበልጥ ባደረጉትም የመስመር ላይ አጨዋወት አጋማሹ በጀመረ በሰባት ደቂቃዎች ውስጥ ስራ ይርዳው የግል ጥረቷን ተጠቅማ ያቀበለቻትን ኳስ ቤዛዊት ንጉሴ ከመረብ አዋረዳው ዳግም ድሬዳዋን ወደ መሪነት አሸጋግራለች። በቀሩት ደቂቃዎችም ንፋስ ስልኮች በመልሶ ማጥቃት አቻ ለመሆን ድሬዳዋዎች በበኩላቸው ጥንቃቄ አዘል የጨዋታ መንገድን ተከትለው በተሻጋሪ ኳስ ላይ አተኩረው ቢጫወቱም ጨዋታው በእንስት የምስራቁ ተወካይ ክለብ የበላይነት ተደምድሟል።

\"\"

የሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ የነበረው የልደታ ክፍለ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በሙሉ የጨዋታ ደቂቃ የእንስት ፈረሰኞቹን ፍፁም የእንቅስቃሴ ብልጫን አሳይቶን በመጨረሻም 1ለ1 ተገባዷል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከጨዋታው ጅምር አንስቶ እስከ ፍፃሜው ድረስ ኳስን በራሳቸው እግር ስር በማድረግ በአንድ ሁለት ቅብብል በመጫወት ጎልን ለማግኘት ቢታትሩም የአጥቂ ክፍላቸው መሳሳት ያገኟቸውን በርካታ አጋጣሚዎች እንዳያስቆጥሩ እንከን ሆኖባቸው በግልፅ ተስተውሏል። ልደታዎች ደግሞ ከየትኛውም የሜዳ ክፍል የሚያገኟቸውን ኳሶች ከፊት ወደ ተሰለፉት አጥቂዎች በመጣል የጊዮርጊስን የተከላካይ ክፍል ለመረበሽ ጥረዋል።


26ኛው ደቂቃ ላይ ከተከላካይ ክፍሉ ወደ ጊዮርጊስ የመከላከል ወረዳ በረጅሙ የተሻገረላትን ኳስ ዓለሚቱ ድሪባ ፍጥነቷን ተጠቅማ ኳስ እና መረብን በማዋሀድ ልደታን 1ለ0 አድርጋለች። ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ በተለየ መልኩ በሁለተኛው አጋማሽ የተንቀሳቀሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች መደበኛው የጨዋታ አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ብቻ እየቀረው ተቀይራ በገባችው ቃልኪዳን ወንድሙ ግሩም ጎል ከተጋጣሚያቸው ጋር አንድ ነጥብን ተቋድሰው ጨዋታው 1ለ1 ፍፃሜውን አግኝቷል።

\"\"