ቱሪስት ለማ የሰባት ጨዋታዎች ቅጣት ተጥሎባታል

ሀዋሳ ከተማ በኢትዮ ኤሌክትሪክ በተሸነፈበት ጨዋታ ያልተገባ ባህሪን ያሳየችው አጥቂዋ ቱሪስት ለማ ላይ የቅጣት ውሳኔዎች ተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በሀዋሳ ከተማ እየተደረገ የአንደኛ ዙር መርሀግብር ሊጠናቀቅ የመጨረሻ ሳምንቱ ላይ ደርሷል።

\"\"

የ12ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ከአንድ ቀን በፊት ተከናውነው የተጠናቀቁ ሲሆን ተጠባቂ በነበረው የሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ላይ በነበረ ሁነት ላይ ተመስርቶ አወዳዳሪው አካል በአጥቂዋ ቱሪስት ለማ ላይ ጠንከር ያለ ውሳኔ ጥሎባታል።

በቅድሚያ ተጫዋቿ በተመለከተቻቸው ተከታታይ አምስት ቢጫዎች የብር 1500 እና የአንድ ጨዋታ ቅጣት አግኝቷታል። በመቀጠል በኢትዮ ኤሌክትሪኩ ጨዋታ 66 ኛው ደቂቃ ላይ የዕለቱን ዋና ዳኛ ማርታ መለሰን በመማታቷ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣች ሲሆን በዕለቱ የጨዋታ አመራሮች ሪፖርት ስለቀረበባት የመጀመሪያው ቅጣት እንዳለ ሆኖ በተጨማሪ 6 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፋ እንዳትጫወት እና ብር አስር ሺህ እንድትከፍል ተወስኖባታል። የገንዘብ ቅጣቱ በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ካልተከፈለ በየቀኑ 2% እየጨመረ እንደሚከፈልም በውሳኔው ተያይዞ ወጥቷል፡፡

\"\"

ተጫዋቿ የተወሰነባትን የጨዋታ መጠን ብትጨርስም ገንዘቡን ካልከፈለች ተሰልፋ እንዳትጫወት የተባለ ሲሆን ይህንን ውሳኔ ተላልፋ ብትጫወት የተጫወተችባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ቡድኑ በፎርፌ ተሸናፊ እንዲሆን ተወስኗል፡፡