የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የአንደኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገው ተቋጭቷል

የ2015 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአንደኛው ዙር የ13ኛ ሳምንት የሊጉ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገው ሲጠናቀቁ ሀዋሳ ከተማ ፣ መቻል እና ልደታ ክ/ከ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ዙሩን ፈፅመዋል።

በሀዋሳ ከተማ አስተናጋጅነት ያለፉትን ወራት ሲደረግ የነበረው የ2015 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር ጨዋታዎች በ13ኛ ሳምንት የመጨረሻ ሦስት መርሀግብሮች በዛሬው ዕለት ተካሂደው በመሸናነፍ ፍፃሜያቸውን አግኝተዋል።

\"\"

የዕለቱ የመጀመሪያ የሆነው የሀዋሳ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ ጠንካራ ፉክክርን አስመልክቶን በመጨረሻም በሀዋሳ ከተማ አሸናፊነት ተደምድሟል። በጨዋታው ሀዋሳ ከተማዎች መሀል ሜዳ ላይ አመዝነው ኳስን በመቆጣጠሩ ረገድ የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም በመስመር ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩት አዲስ አበባ ከተማዎች የዋዛ አልነበሩም። መደበኛው የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አስር ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩ ህይወት ረጉ ከቀኝ ወደ ውስጥ ያሻገረችውን ኳስ ተቀይራ የገባችው ረድኤት አስረሳኸኝ ከመረብ አገናኝታ ሀዋሳ ከተማ ተፈትኖም ቢሆን 1ለ0 በማሸነፍ ዙሩን አገባዷል።
\"\"

ከጨዋታው ጅማሮ አስቀድሞ ከሰሞኑ የሰባት ጨዋታዎች ቅጣትን ዳኛ በመማታቷ የተላለፈባት አጥቂዋ ቱሪስት ለማ በስታዲየሙ የሚገኙትን ተመልካቶች አበባ ይዛ ላጠፋችው ጥፋት ይቅርታ ስትጠይቅ አስተውለናል።

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በመቻል እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መካከል የተካሄደ ሲሆን መቻሎች በጎል ተንበሽብሸው ሦስት ነጥብን ከተጋጣሚያቸው ላይ ወስደዋል። መሀል ሜዳ ላይ በሚደረግ ቅብብል ወደ መስመር በመለጠጥ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመግባት የሚዳዱት መቻሎች የመጀመሪያውን ሀያ ደቂቃዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሽግግር በሚጫወቱት ንፋስ ስልኮች በተወሰነ መልኩ ለመፈተን ተገደዋል። ይሁን እና 11ኛው ደቂቃ ላይ እፀገነት ግርማ መቻልን መሪ ያደረገች ግብን ከመረብ አገናኝታ ቡድኗን ቀዳሚ አድርጋለች። ጎል ካስተናገዱ በኋላ ያለ መታከት መልሶ ማጥቃት ላይ በይበልጥ ያተኮሩት ንፋስ ስልኮች 23ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ሊሆኑ የሚችሉበትን ዕድል አግኝተው መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል የመቻሏ ተከላካይ አረጋሽ ፀጋ ኳስ በእጅ በሳጥን ውስጥ በመንካቷ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አለም በየቻ ብትመታውም የመቻሏ አበባየው ጣሰው መልሳባታለች።
\"\"

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ተጭነው በመጫወት ቶሎ ቶሎ ጥቃትን ወደ መሰንዘሩ የገቡት መቻሎች እፀገነት ግርማ 26ኛው ደቂቃ ላይ ግሩም ግብን ለራሷም ለቡድኗም ሁለተኛ ጎል ስታደርግ 36ኛው ደቂቃ ላይ የንፋስ ስልክ ተከላካዮች ኳስን በእጅ በመንካታቸው የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ሴናፍ ዋቁማ ሦስተኛ ጎል አድርጋዋለች። ከዕረፍት ተመልሶ ጨዋታው ሲቀጥል የእፀገነት ግርማ ግሩም የማቀበል እይታ ታክሎበት ምርቃት ፈለቀ በጥሩ አጨራረስ አራተኛ ጎልን ስታክል 78ኛው ደቂቃ ከሜሮን ገነሞ ያገኘችውን ሴናፍ በጨዋታው ሁለተኛ ለቡድኗ አምስተኛ ጎል አድርጋው ጨዋታው 5-0 የመቻል ድል አድራጊነት ተጠናቋል።

\"\"

የአንደኛው ዙር የማሳረጊያ ጨዋታ የነበረው የድሬዳዋ ከተማ እና ልደታ ክፍለ ከተማ ጨዋታ በልደታ ፍፁም የበላይነት 3ለ0 ተደምድሟል። ኳስን በራሳቸው እግር ስር በማድረግ ልየነትን ለመፍጠር የሚጥሩት ልደታዎች 37ኛው ደቂቃ ላይ ሔለን መንግሥቱ ከግራ የድሬዳዋ የግብ አቅጣጫ የተገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ጎል አክርራ ስትመታው የግብ ጠባቂዋ ብርሀን ባልቻ ግልፅ የሆነ ስህተት ታክሎበት ኳስ እና መረብ ተገናኝተው ልደታ መሪ ሆኗል። ሜዳ ላይ ደካማ አቀራረብ የነበረባቸው ድሬዳዋዎች በሳጥን ውስጥ ተከላካዮቻቸው የሰሩትን ጥፋት ተከትሎ ከዕረፍት በኋላ 73ኛው ደቂቃ ላይ የፍፁም ቅጣት ምት የተሰጠባቸው ሲሆን ረድኤት ዳንኤል ከመረብ አገናኝታ ልደታን ወደ 2-0 አሸጋግራለች።
\"\"

በቀሩት ደቂቃዎች የተጫዋች ለውጥን ጭምር በማድረግ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ድሬዳዋዎች መጣር ቢጀምሩም መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተሰጠ የጭማሪ ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት የተገኘን አጋጣሚ ህዳት ካሱ ወደ ስትመታ ተከላካዩዋ ህይወት ዳንኤል በራሷ ላይ አስቆጥራው ጨዋታው 3-0 በአሰልጣኝ ፍቅሬ ቢሆነኙ ልደታ ክፍለ ከተማ አሸናፊነት ተቋጭቷል።

በሀዋሳ ሲደረግ የነረው የአንደኛው ዙር የሊጉ ጨዋታዎች ዛሬ የተጠናቀቁ ሲሆን ሁለተኛው ዙር የካቲት 26 በባህርዳር የሚቀጥል ይሆናል። ስለ አንደኛው ዙር ሶከር ኢትዮጵያ የታዘበቻቸውን ጉዳዮች በቀጣይ ወደ እናንተ የምታደርስም ይሆናል።