ቻን | ዋልያዎቹ በነገው ጨዋታ የአንድ ተጫዋች ግልጋሎት ያጣሉ

ነገ ምሽት የአልጄሪያ አቻውን የሚገጥመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአጥቂ አማካዩን በጨዋታው አያገኝም።

\"\"

የቻን የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ነገ ሲጀምሩ ምሽት 4 ሰዓት ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ መርሐ-ግብራቸውን በኔልሰን ማንዴላ ስታዲየም ይከውናሉ። በዚህ ወሳኝ ጨዋታ ላይ ደግሞ የአጥቂ አማካዩ ወንድማገኝ ኃይሉ በጉዳት ምክንያት ለዋልያው ግልጋሎት እንደማይሰጥ ተረጋግጧል። በመጀመሪያው የሞዛምቢክ ጨዋታ በ81ኛው ደቂቃ ከነዓን ማርክነህን ቀይሮ ወደ ሜዳ ገብቶ የነበረው ወንድማገኝ ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ ከተቃራኒ ተጫዋች ጋር የአንድ ለአንድ ፍልሚያ በሚያደርግበት ወቅት ጉዳት አስተናግዶ በዱሬሳ ሹቢሳ ተቀይሮ እንደወጣ አይዘነጋም። ተጫዋቹ ካጋጠመው ጉዳት ማገገም እና አለማገገሙን የተጠየቁት የቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ይህንን አስተያየት ሰጥተዋል።

\”ወንድማገኝ የመጀመሪያው ጨዋታ ላይ ጉዳት አስተናግዷል። ዛሬ የኤም አር አይ ምርመራ ያደርጋል። እግሩ ላይ አሁንም እብጠት አለ። ስለዚህ በነገው ጨዋታ ተሳትፎ አያደርግም። በትክክል የጉዳቱን ዝርዝር እስካሁን ባናውቅም ከተጋጣሚ ተጫዋች በደረሰበት ነገር ከነገው ጨዋታ ውጪ ነው።\” በማለት ተናግረዋል።

\"\"

አሠልጣኙ በተያያዘ ከወንድማገኝ ኃይሉ ውጪ ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ አመላክተዋል።