ቻን | ከወሳኙ ጨዋታ በፊት የዋልያዎቹ አሠልጣኝ እና አምበል አስተያየት ሰጥተዋል

👉 በዐምሮም በአካልም ለዚህ ጨዋታ በደንብ እየተዘጋጀን ነው\” መስዑድ መሐመድ

👉\”…የተዘረዘሩት ነገሮች ከእኛ በተቃራኒ ቢሆኑም ከጨዋታው የተሻለውን ነገር ለማግኘት እንሞክራለን\” ውበቱ አባተ

በአፍሪካ ሀገራት ሻምፒየንሺፕ ውድድር ሀገራችን ኢትዮጵያ ከአልጄሪያ፣ ሞዛምቢክ እና ሊቢያ ጋር በምድብ አንድ ተደልድላ ጨዋታዎቿን እያደረገች እንደሆነ ይታወቃል። ሀገራችን በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታም ከሞዛምቢክ ጋር 0ለ0 የተለያየች ሲሆን ነገ ምሽት 4 ሰዓት ደግሞ ሁለተኛ ፍልሚያዋን ከአዘጋጇ አልጄሪያ ጋር ታደርጋለች። ከዚህ ወሳኝ ጨዋታ አስቀድሞ ደግሞ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና አምበሉ መስዑድ መሐመድ የቅድመ-ጨዋታ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በቅድሚያ አሠልጣኙ ለነገው ጨዋታ እያደረጉ ያለውን ዝግጅት በተመለከተ ተከታዩን አስተያየት በመስጠት መግለጫውን ጀምረዋል።

\"\"

\”ዝግጅታችንን የመጀመሪያውን ጨዋታ እንደጨረስን ወዲያው ለተጫዋቾቻችን እረፍት በመስጠት ጀምረናል። እንደምታውቁት በመጀመሪያው እና በሁለተኛው ጨዋታ መካከል የሁለት ቀን ልዩነት ብቻ ነው ያለው። ስለዚህ ብዙ ስራ ለመስራት ጊዜ የለም። ባለን ቀን እየሰራን ያለው የተጫዋቾቹ አምሮ እና እረፍት አወሳሰድ ላይ ነው። በአጠቃላይ ግን በዐምሮም ሆነ በአካል ለነገው ለአልጄሪያ ጨዋታ ተዘጋጅተናል።\” ካሉ በኋላ አምበሉ መስዑድ መሐመድም ሀሳባቸውን ተከትሎ አጠር ያለ ማብራሪያ ስለዝግጅታቸው ሰጥቷል። \”ከመጀመሪያው ጨዋታ እያገገምን ለሁለተኛው ጨዋታ እየተዘጋጀን ነው። የነገው ጨዋታ ከመጀመሪያው ፍፁም የተለየ ነው። ስለዚህ በዐምሮም በአካልም ለዚህ ጨዋታ በደንብ እየተዘጋጀን ነው።\”

በማስከተል ስለነገው ጨዋታ የተጠየቁት አሠልጣኝ ውበቱ ፍልሚያው ከባድ ቢሆንም በሙሉ የራስ መተማመን እንደሚጫወቱ ተናግረዋል። \”ነገ የምንጫወተው ከባለሜዳ ቡድን ጋር ነው። አንደኛው ነገር ጠንካራዋን አልጄሪያ ነው የምንገጥመው ፤ በተጨማሪም ስታዲየሙን በሞሉ ደጋፊዎቻቸው ፊት ነው የምንገጥማቸው። የመጫወቻ ሜዳ ጥቅምን ጨምሮ ሁሉም ነገሮች ለአልጄሪያ የተሻለ ጥቅም ይሰጣል። ከዚህ በዘለለ አልጄሪያዎች ከእኛ በበለጠ ከመጀመሪያው ጨዋታ የሚያገግሙበት አንድ ተጨማሪ የእረፍት ቀን አላቸውና ከእኛ የተሻለ ትኩስ ጉልበት ሊኖራቸው ይችላል። እነዚህ ነገሮች ጨዋታውን ከባድ ሊያደርጉብን ይችላሉ ግን ወደቀጣዩ ዙር ማለፍ እንዳለብን እናስባለን። የተዘረዘሩት ነገሮች ከእኛ በተቃራኒ ቢሆኑም ከጨዋታው የተሻለውን ነገር ለማግኘት እንሞክራለን። ቡድኑ ከደጋፊው የሚያገኘውን ድጋፍም ታክቲካዊ በሆኑ ነገሮች ለመቀነስ እንሞክራለን ፤ የሆነው ሆኖ በሙሉ የራስ መተማመን ጨዋታውን እናደርጋለን።\” ብለዋል።

\"\"

ባሳለፍነው የአፍሪካ ዋንጫ መጀመሪያ ከኬፕ ቨርዴ ጋር ተጫውተው ከዛ በሁለተኛው ጨዋታ ከአዘጋጇ ካሜሩን ጋር እንደተጫወቱ በማስታወስ \”በአፍሪካ ዋንጫ የገጠመን አይነት ነገር ነው አሁንም የገጠመን።\” ያሉት የዋልያው አለቃ በካሜሩኑ መድረክ የተሳተፉትም ሆነ አዳዲሶቹ ተጫዋቾች 40 እና 45 ሺ ደጋፊዎች ፊት ያላቸውን ለማሳየት የነገው ጨዋታ ጥሩ ዕድል እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

በመጨረሻም መስዑድ መሐመድ ከመጀመሪያ ጨዋታ እንደቡድን የተማሩትን ነገር ገልፆ ከብዙሃን መገናኛ አባላት ጋር ያደረጉት ቆይታ ተጠናቋል። \”የመጀመሪያው ነገር እንደ ሞዛምቢኩ ጨዋታ በተቻለ መጠን በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ነው። በእግርኳስ ጨዋታ የምትማረው ነገር አለ። ከግብ ዕድሎች ጋር ተያይዞም ከመጀመሪያው ጨዋታ የተማርነው ነገር አለ። ብዙ ዕድል ከፈጠርክ ለመጨረስ የተሻለ ነገር ይኖርካል።\”