ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ከሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ የቡድኑ አካል አድርጓል።

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ተወዳዳሪ የሆነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቀናት በፊት አብዱርሀማን ሙባረክን ማስፈረሙ ይታወሳል። በዛሬው ዕለት ደግሞ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ከሀገር ውስጥ እና ከኤርትራ ወደ ስብስቡ ስለ መቀላቀሉ በተለይ ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል።

\"\"

ከሀገር ውስጥ አማረ በቀለ ወደ ቀድሞው ክለቡ ተመልሷል። በመሀል እና በመስመር ተከላካይነት ከዚህ ቀደም በኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫውቶ ያሳለፈው እና ከዚያም ወደ ወልድያ አምርቶ የክለብ ህይወቱን የቀጠለው ተጫዋቹ በትውልድ ከተማው ድሬዳዋ ከተማ በመመለስ ያለፈውን አንድ ዓመት ከቆየ በኋላ ወደ ኤሌክትሪክ ተመልሷል።

በሌላ በኩል የመስመር አጥቂው ዮናስ ሰለሞን በሊጉ ሦስተኛው ኤርትራዊ ተጫዋች በመሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክን ተቀላቅሏል። ተጫዋቹ አብዛኛውን የእግር ህይወቱን በሱዳኖቹ ቱቲ ኤስ ሲ እና አልሀሊ አትባራ እንዲሁም በሀገሩ በአዱሊስ ከቆየ በኋላ በድጋሚ ወደ ሱዳን አምርቶ ሾርታ ካርዲፍ ለተሰኘው ክለብ እንደሚጫወተ መረጃዎች ያመለክታሉ።

\"\"

15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ክለቡ ሁለት የውጪ ዜግነት ያላቸው ተጫዋችን ጨምሮ በቀጣዮቹ ቀናት ሌሎች ዝውውሮችን እንደሚፈፅም ይጠበቃል። በሌላ በኩል በክረምቱ ቡድኑን ከተቀላቀሉት ወንድማገኝ ማዕረግ እና ዮሐንስ ሱጌቦ እንዲሁም ከነባሩ አጥቂ አቤል ሀብታሙ ጋር በስምምነት መለያየቱን የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ለማ ለሶከር ኢትዮጵያ ጠቁመዋል።