“ፋሲሎችን” እንታደጋቸው !

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስፖርት ሳይንስ እና ሳይኮሎጂ መምህር የሆነው ሳሙኤል ስለሺ በግብ ጠባቂዎች ሥልጠና ዙሪያ የላከልን ፅሁፍ እንደሚከተለው ይነበባል።

በሳሙኤል ስለሺ

“ፋሲል” ሲባል አብዛኛው የስፖርት ብሎም የእግር ኳስ ቤተሰብ ወደ አዕምሮው የሚመጣው ጃኖ ለባሹ ፋሲል ከነማ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይሄ ስም ከፋሲል ከነማ በተለየ መልኩ ሰሞኑን በተደጋጋሚ እየተነሳ ለትችት እና ወቀሳ እየተዳረገ ይገኛል ፤ አዎ ፋሲል ገ/ሚካኤልየኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የግብ ዘብ፡፡

ብሔራዊ ቡድናችን በቻን ቆይታው ባደረገው የመጨረሻ ጨዋታ ውጤት ያጣው በእርሱ ነው ተብሎ ይመናል፡፡ ከመምራት ተነስተን የተሸነፍነው ፣ በእጃችን የገባውን ውጤት አሳልፈን የሰጠነው ፣ በጥቅሉ ከውድድሩ የተሰናበትነው በፋሲል ገ/ሚካኤል ደካማ እንቅስቃሴ ነው ብለው የሚያምኑ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከፍተኛ የማህበራዊ ሚዲያ ውግዘቶች ፣ የሚዲያ ነቀፌታዎች አለፍ ሲልም ለዛ ቢስ “ሜሞች”ን ጨምሮ የስፖርተኛው ስም በመጥፎ ሲነሳ ከርሟል፡፡

እውነት ነው፤ በመጨረሻው ጨዋታ በ44ኛው እና በ50ኛው ደቂቃ ላይ የተቆጠሩብን ግቦችን ላይ ላዩን ለተመለከተ (Face Value) ሙሉ ስህተቱ የተጨዋቹ እንደሆነ ይረዳል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ግን ጉዳዩን ሥራዬ ብሎ ስር ሰዶ ለመረመረ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስን ለፈተሸ ምን አልባትም ለተሰሩት ጥፋቶች ፋሲል ገ/ሚካኤል አንድ ሺህኛ ወይም ሁለት ሺህኛ ተጠያቂ አድርጎ ሊያስቀምጠው ይችላል፡፡

በእርግጥ በግብ ዘቡ የተሰራውን ስህተት አቃሎ ማየት ተገቢ አይደለም፡፡ “ዴቪድ ዴህያም እኮ ይሳሳታል በእርሱ አልተጀመረም”፣ “አሊሰንም ከዚህ የባሰ ጎል ተቆጥሮበት የለ”፣ “ግብ ጠባቂ የተፈጠረው ለመሳሳት ነው” በማለት ተጨዋቹን በእወደድ ባይነት ስሜት መከላከልም ሆነ መሸንገል ተገቢ አይደለም፡፡

ሆኖም ግን የእነዚህ ግብ ጠባቂዎች ስህተት “ግላዊ” ጥፋቶች ሲሆኑ የፋሲል ግን “ስርዓታዊ” (Systemic) ሆኖ የእግር ኳሱ ስህተት የወለዳቸው ፣ የክለቦች አስተዳደር የፈጠሯቸው እና ከደካማ የእግር ኳስ አመለካከት የተቀዱ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ በምትካፈልባቸው ትላልቅ መድረኮች ላይ መሰል የግብ ጠባቂዎች ስህተቶች ጎልተው የሚወጡት፡፡

ከ32 ዓመታት በኋላ ለመድረክ በበቃንበት የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ጀማል ጣሰው የሰራውን ስህተት ተከትሎ በቀይ ካርድ እና በቃሬዛ ከሜዳ ሲወጣ ያላዘነበት እና ያልወቀሰው አልነበረም። ኳስ ተጨዋቹ ወደ “ኩንግ ፉ” ስፖርተኛነት ተቀየረ ተብሎ ብዙዎች ተዘባብተውበታል፡፡ በቃሬዛ ላይ ሆኖ እንኳን የተንሰፈሰፈለት ውስን ሰው ነበር፡፡ እርሱን ተከትሎ ደግሞ የዛሬ 6 ዓመት አካባቢ ኢትዮጵያ በጋና ስትሸነፍ ለአምስት ጊዜያት ያህል ግቡ የተጎበኘው አቤል ማሞ “ለሽንፈታችን 50 ከመቶ ኃላፊነት ይወስዳል” የሚል ሪፖርት በአሰልጣኞቹ ቀርቦበታል፡፡ ሀገር እንደ ሀገር ባልሰራችው ፣ ክለብ እንደ ክለብ ባላጎለበተው ፣ ባለሙያ እንደ ባለሙያ ባላራቀቀው ሥልጠና ውስጥ የሚያልፉት ግብ ጠባቂዎች ዘወትር የድክመታችን ሁሉ ማላከኪያ (Escape Goat) የስንፍናችን መሸሸጊያ ሆነው ይቀርባሉ፡፡

\"\"

እነዚህን ሁለት ሲኒየር ተጨዋቾችን ተከትሎ የመጣው እና የእዚሁ ሽክርክሮሽ ሰለባ የሆነው ደግሞ ተክለማሪያም ሻንቆ ነው፡፡ ጀማል እና አቤል የጦስ ዶሮዎች ከሆኑ ዓመታት በኋላ በሌላ የጋና ጨዋታ ጥፋት የሰራው ተክለማሪያም የ”ሜመሮች” መለማመጃ ሊሆን በቅቷል፡፡ ኢትዮጵያ የጋናውን ጨዋታ እጅግ አስገራሚ በሆነ ብቃት መጀመሯ እና ውጤት ይዛ ትወጣለች የሚለውን ዕምነት የተክለማሪያም ስህተት ውሀ ቢቸልስበት ጊዜ ብዙዎች አዘኑበት፡፡ ተክለማሪያም ከዚህ ስህተቱ አገግሞ በአፍሪካ ዋንጫው የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ከፍተኛ ብቃት ቢያሳይም በሦስተኛው የቡርኪናፋሶ ጨዋታ ላይ የተቆጠረበት ግብ ከብሔራዊ ቡድኑ እንዲርቅ አስችሎታል፡፡

እነዚህ ተጨዋቾች በስህተት ውስጥ ያገኙት ልምድ እና ትምህርት ከፍተኛ ቢሆንም፣ የገጠሟቸው አያሌ ብሔራዊ ቡድኖች እና አጥቂዎች ቁጥር በርከት ቢልም ፣ በተለያዩ ውድድሮች ላይ ያገኟቸው ልምዶች ቢገዝፉም ፣ የተፋለሟቸው ዓለም አቀፍ አጥቂዎች ቢበዙም ዛሬ ላይ የብሔራዊ ቡድኑ ቁጥር አንድ ተመራጭ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ይኸው አሁን ደግሞ አዙሪቱ ቀጥሎ ባለተራው ፋሲል ገ/ሚካኤል ሆኗል፤ የዘራውን ሳያጭድ የለፋበትን ሳይለቅም ከብሔራዊ ቡድኑ የሚቀነስበትን ነጋሪት እየጎሰምን ነው፡፡ አንዱን ፋሲል አጥፍተን ሌላውን ፋሲል የመናፈቅ አባዜ ውልብ እያለን ነው፡፡

ግብ ጠባቂ የማደን ፈተና

ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና ረዳቶቻቸው ጋር ለመስራት ዕድል ባገኘሁባቸው ትንሽ አጋጣሚዎች እንደተረዳሁት ከሆነ ከተጨዋቾች ምርጫ ሁሉ ራስ ምታት የሚሆንባቸው እና ውስን ምርጫ ከሚያገኙባቸው የመጫወቻ ቦታዎች አንዱ እና ዋንኛው ግብ ጠባቂ ነው፡፡ አሰልጣኙ ወደ ብሔራዊ ቡድን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በሰባት ከፍተኛ ውድድሮች ላይ ሲሳተፉ በእነዚህ ውድድሮች ላይ ከዝግጅት ጀምሮ ጥሪ ያደረጉላቸው የግብ ጠባቂዎች ብዛት ካልተሳሳትኩ 15 ደርሰዋል፡፡ ጀማል ጣሰው ፣ አቤል ማሞ ፣ ተክለማሪያም ሻንቆ ፣ ፋሲል ገ/ሚካኤል ፣ ምንተስኖት አሎ ፣ ፍሬው ጌታሁን ፣ ፅዮን መርዕድ ፣ ሰዒድ ሐብታሙ ፣ በረከት አማረ ፣ ባህሩ ነጋሽ ፣ አልዓዛር ማርቆስ ፣ ዳግም ተፈራ ፣ ዳንኤል ተሾመ፣ ይድነቃቸው ኪዳኔ እና ታምራት ናቸው፡፡

በብሔራዊ ቡድን ለመታቀፍ የሚበቁ ግብ ጠባቂዎች እጅግ ደረጃቸው ጣራ የነካ እና ብዙም የማያጨቃጭቁ መሆን ሲገባቸው የእኛ ሀገር ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች ግን ለዚህ አልታደሉም፡፡ ግብ ጠባቂ ማለት ደግሞ በአንድ ጨዋታ ከ3- 5 ያለቀላቸው ግቦችን ማዳን የሚችል ሁነኛ የቡድን አካል መሆኑን ተከትሎ በትላልቅ ውድድሮች ላይ እሩቅ ለመጓዝ ካስፈለገ በዚህ ደረጃ የሚገኝ የግብ ዘብ ማዘጋጀት ያስፈልገናል፡፡ ሞሮኮ በዓለም ዋንጫው ሩቅ ስትጓዝ የቡድኑ አንደኛ ግብ ጠባቂ ያሲን ቦኑ እና በቤልጂየሙ ጨዋታ ላይ በድንገቴ የገባው ሁለተኛ ግብ ጠባቂ ሙኒር ሞሀመዲ የግብ ጠባቂ ከፍታ ምንኛ አስፈላጊ እንደሆነ አሳይተዋል፡፡ የአለም ዋንጫ ሻምፒዮኗ አርጀንቲናም በሜሲ ምትሀታዊ እግሮች ትታጀብ እንጂ ያለ ግብ ጠባቂዋ ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝ ህልሟ ባልተሳካ ፤ ሜሲም የወርቅ ካባውን ባልደረበ ነበር፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዚህ ደረጃ ያሉ እና ትላልቅ ጨዋታዎች ላይ ይዘውን የሚወጡ ግብ ጠባቂዎችን ማፍራት እንዴት ተሳናት ? እስከመቼ በተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ እንቆያለን ? እነርሱን ከማውገዝ ወጥተን ወደ ማግነን (Idioloze) እንዴት እንሸጋገራለን ? የሚለው ጥያቄ በእግር ኳስ ቤተሰቡ ውስጥ ዘወትር የሚመላለስ ነው፡፡ እንደ እኔ ግን ተጨዋቾቹ ላይ ከመረባረባችን በፊት የሚከተሉት ሦስት ነጥቦች ላይ አፅንኦት መስጠት እንዳለብን ላስረዳ፡፡

1 የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች ሥልጠና

የኢትዮጵያ እግር ኳስን ከተጠናወተው መጥፎ ባህሪ አንዱ እና ዋንኛው በቀኝ ጆሮ ሰምቶ በግራ ጆሮ ማፍሰስ ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ ወይ የሚያስረዳው ሰው በቅጡ አያስረዳም አልያም የሚሰማው በአግባቡ አያዳምጥም/ አይረዳም/ አይፈልግም እንጂ የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች ሥልጠና ፈቃድ በብዙ ማይክ እና በብዙ መድረክ ብዙ የተባለለት ጉዳይ ነው፡፡ እኔ እስካለኝ ዕውቀት እና መረዳት ድረስ የእግር ኳስ አሰልጣኝ ፈቃድ እንጂ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ፈቃድ ያለው አሰልጣኝ የለም (ከአጫጭር ሥልጠናዎች በስተቀር)፤ ሥርዓቱም አልተዘረጋም፡፡

በተዘረጋው የአሰልጣኞች ሥልጠና ስርዓት ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች ከመደበኛው CAF A፣ CAF B ፣ CAF C ሥልጠና ውጪ ተከታታይነት ያለው የውስን ዘርፍ (Speciality) ሥልጠና አላገኙም፤ ለዚህ የተለየ የሥራ ዘርፍ የሚውል የተለየ ፈቃድ አልተሰጣቸውም፡፡ በሀገሪቱ የተዘረጋው የአሰልጣኞች ሥልጠና/ ትምህርት ሰንሰለት (Coaching Path Way) ሁሉንም አሰልጣኞች በአንድ ዐይን የሚያይ ፣ ለተለየ ሥራ የተለየ ስልጠና የማይሰጥ ነው፡፡ በአንድ ክለብ ውስጥ ያሉ አሰልጣኞች ዋናውም፣ ምክትሉም፣ የግብ ጠባቂውም፣ የአካል ብቃቱም፣ የታዳጊዎቹም ሆነ ሌሎች ተመሳሳይ ስልጠና እና የካፍ ላይሰንስ ወስደው የተለያየ ሥራ ላይ ሲሰማሩ ይስተዋላል፡፡ ይህ አሰራር መስተካከል እንዳለበት አዲሱ የአሰልጣኞች ሥልጠና ሰንሰለት ሲዋቀር በፅሁፍም ሆነ በቃል ተደጋግሞ ቢነገርም የማስረዳት ይሁን የመረዳት ችግሩ በውል ሳይታወቅ ሳይተገበር ቀርቷል፡፡ እውነት ነው ሥልጠናውስ ተሰጥቶ ፣ የፈቃድ ሥርዓቱስ ተዘርግቶ ለውጥ ይመጣል ወይ የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ፡፡

2 የግብ ጠባቂዎች ሥልጠና

ሌላው መሰረታዊ ችግራችን የግብ ጠባቂዎች ሥልጠናችን ነው፡፡ ለእግር ኳሱ ቅርብ እንደመሆኔ እና በተለያዩ አጋጣሚዎች ልምምድ ሜዳዎች ላይ እንደመገኘቴ የግብ ጠባቂዎች ሥልጠናችን አለመዘመን በተጨዋቾቹ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ተጨዋቾች ከስህተታቸው እየተማሩ እንዳይሄዱ ፣ ባላቸው ልምድ ላይ እንዳይጨምሩ ፣ በትላልቅ ጨዋታዎች ላይ ያገኙት ልምድ ዉሃ ተቸልሶበት እንዳይቀር የሚያደርጉ የሚያሳብቡ እንጂ የማያቀነጭሩ ሥልጠናዎች ያስፈልጋቸዋል፡፡

እግር ኳስ ሜዳ ላይ ካሉ ተጨዋቾች ውስጥ አብዛኛው ሥራዎቹን በሌሎች ተጨዋቾች ውሳኔ ላይ ተንተርሶ የሚሰራ ተጨዋች ቢኖር ግንባር ቀደሙ ግብ ጠባቂ ነው፡፡ በየትኛውም መመዘኛ የፈለገውን ለማድረግ የተገታ ሰው ቢኖር ግብ ጠባቂ ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ የተጋጣሚዎቹን አጥቂ እንቅስቃሴ፣ አቋቋም እና ውሳኔ ተከትሎ ከመቅፅበት ውሳኔ የሚወስን የሜዳ ተጨዋች ቢኖር እንደ ግብ ጠባቂ የለም፡፡

በተለይም በክለብ ላይ የሚደረጉ ሥልጠናዎች ዓመቱን ሙሉ የሚቆዩ እንደመሆናቸው ከብሄራዊ ቡድን ሥልጠናዎች በተለየ መልኩ ሊታዩ እና በተጨዋቾች ዕድገት ላይ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ በተገባ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አብዛኛዎቹ ሥልጠናዎች የበረኛን አካል በመገንባት አዕምሮን ደግሞ በማዛል (Detrain) (መግደል የሚለውን ቃል ላለመጠቀም ነው) ላይ የተጠመዱ ናቸው፡፡ ነጮቹ Feet Train and Brain Drain የሚሉት ዓይነት ሥልጠናዎች በየቦታው በትላልቅ ደረጃ ሳይቀር በሰፊው ይስተዋላሉ፡፡

ሙሉ የአንድ ሰዓት ከሰላሳ ደቂቃ ልምምድ ፍፁም ከአዕምሮ የራቀ እና እውነተኛውን የጨዋታ ችግሮች መሰረት ያላደረገ ሆኖ ማየት በእጅጉ የተለመደ ነው፡፡ ተጨዋቹ እንዲወስን፣ እንዲገምት፣ እንዲያሰላስል፣ እንዲረዳ ከሚያስችሉ ልምምዶች ይልቅ ከመውደቅ እና መነሳት ጋር ብቻ የተቆራኙ፣ ‹‹ወደ ቀኝ ነው የምመታብህ ወደ ቀኝ ውደቅ››፣ ‹‹አሁን ላዘልልህ ነው ዝለል›› ዓይነት ልምምዶች ታጭቀው የተጨዋቹን አዕምሮ በማይፈትኑ ድሪሎች ሙሉ ሥልጠናው ሲጠናቀቅ ይታያል፡፡ እነዚህ ሥልጠናዎች የራሳቸው የሆነ ጥቅም ቢኖራቸውም ተመጣጥነው ሊሰጡ በተገባ ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ግብ ጠባቂዎችን ማዕከል ያደረገ እና ለእነርሱ በሚል ብቻ የሚዘጋጁ የውስን ሜዳ ጨዋታዎች (Small Sided Games) እምብዛም አያጋጥመኝም፡፡ ልምምድ እና ጨዋታዎች በቪዲዮ ተቀርፀው የራስን እንቅስቃሴ የመገንዘብ ፣ የመረዳት እና ኃላፊነት የመውሰድ ሥልጠናዎች ለምን ያህሉ ግብ ጠባቂዎች እንደተሰጡ መረጃው የለኝም፡፡ ሦስት የተለያየ ጥንካሬ እና ድክመት ያላቸውን ተጨዋቾች ወደ ሥልጠና ሜዳ አምጥቶ ሙሉ ለሙሉ ልሙጥ የሆነ ልምምድ መስጠት የተለመደ ነው፡፡

ይህ ቦታ ከምንም በላይ የአዕምሮ ብስለት (Intelligence) ፣ የአዕምሮ ግንዛቤ (Perception) ፣ እይታ (Spatial Ability) ፣ መረጃ አሰባሰብ (Information Processing) ፣ ቅፅበታዊ ውሳኔ (Reaction Time) ፣ ግምታዊ አረዳድ (Anticipation) ፣ ማህደረ ትውስታ (Working Memory) እና ሌሎችም ከአዕምሮ ጋር የተያያዙ አቅሞችን የሚጠይቅ በመሆኑ ለወትሮው ወጣ ያሉ መሰል አቅሞችን የሚያዳብሩ ልምምዶችን ጊዜ እና በጀት ተይዞላቸው ሜዳ ላይ እና ከሜዳ ውጭ ሊሰሩ ይገባል፡፡

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ደግሞ አሁን በተያዘው የሊግ ፎርማት ምክንያት ከልምምድ ሜዳዎች አለመመቸት የተነሳ ድንጋይ እየለቀሙ፣ መሬት እየተመሩ፣ አቧራ እፍ…እፍ… እያሉ የሚሰሩ ‹‹የቁጩ ልምምዶች›› ተበራክተዋል፡፡ በአንድ አጋጣሚ በአንድ ከተማ ላይ ፕሪሚየር ሊጉ መሰናዳቱን ተከትሎ ክለቦች የተሰጣቸው የልምምድ ሜዳ ፍፁም አመቺ ባለመሆኑ ግብ ጠባቂዎች ‹‹ቮሊ- ቮሊ›› የሚመስል ልምምድ ሰርተው ወደ ሰርቪሳቸው ሲገቡ ተመልክቻለሁ፡፡ እውነት ነው አራት እና አምስት ሚሊዮን ብር የሚያወጣን ግብ ጠባቂ እዛ ዓይነት ሜዳ ላይ ማሰራት ፌይር አይደለም ፤ ኮብል ስቶን ላይ አይዲ- 4 ኤሌክትሪክ መኪናህን እንደማመላስ ማለት እኮ ነው፡፡

\"\"

3 የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች ቅጥር

ስለ ግብ ጠባቂዎች ሳስብ ዓይኔ ላይ ድቅን ከሚሉ ችግሮች ውስጥ ዋንኛው ያሉትንም አሰልጣኞች የምንጠቀምበት መንገድ አስተዛዛቢ መሆኑ ነው፡፡ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት ሥራ በማንም ሰው የሚሰራ፣ እጅግ ቀላል፣ ብዙም እውቀት አይፈልግም ዓይነት ስሜት ባለው መነሻ የሚደረጉ ቅጥሮች በብዛት ይስተዋላሉ፡፡ የቀድሞ ተጨዋችን ለማገዝ ሲባል ብቻ በበረኛ አሰልጣኝነት ሲመደቡ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ለክለቡ ቅርበት ያለውን እና በሌላ የስራ መደብ የሚገኝን ሰው ጓንት አስጠልቆ ፣ ፊሽካ አስይዞ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ማድረግ የደግነት፣ የሩህ ሩህነት እና ‹‹የመልካም አስተዳደር›› ውጤት አድርጎ መውሰድም ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡

ከዚህ የከፋው ደግሞ ባለሙያዎችን አወዳድሮ ከመቅጠር ይልቅ መደቡን ‹‹ለአካባቢ ተወላጅ›› የተተወ ክፍት የሥራ መደብ አድርጎ መውሰድ ሀገራዊ እና ክለባዊ ፋሽን ሆኗል፡፡ የምስራቅ ተወላጅ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ደቡብ ያሉ ክለቦች አድነው ካልቀጠሩት፤ ደቡብ የተወለደ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ሰሜን ላይ ካልተፈለገ፤ ሰሜን ያፈራችው ባለሙያ ምዕራብ ላይ ቦታ ከሌለው፤ የምዕራቡ በመሀል ከተማ ካልተፈለገ ሙያው እና ሙያተኛው እንዳልተገናኙ ማመላከቻ ናቸው፡፡

ግብ ጠባቂ ከምዕራብ አፍሪካ ለማምጣት ያልከበደው ክለብ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ፍለጋ ከሰፈሬ እና አውራጃዬ አልወጣም ሲል ማየት ዓለም ላይ ካሉ ነገሮች ሁሉ እርስ በእርሱ የሚጣረዝ እና ግንባር ቀደም አስቂኝ ነገር (Ironic) ነው፡፡

ዲፕሎማሲያዊ መደምደሚያ

እውነት ነው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ግብ ጠባቂነት በራሱ እንደስራ የማይታይበት ጊዜ እሩቅ አልነበረም፡፡ እነ ቢኒ ዳና እንኳን በቀልዳቸው ‹‹መጋዘን ጠባቂ 300 ብር እየተከፈለው እንዴት ይህቺን ትንጥዬ በር እየጠበቀ ሺህ ቤት ይከፈለዋል›› እያሉ ወጋ ወጋ ያደርጉ ነበር፡፡

‹‹እርሱ እኮ በረኛ ነው፤ ታኬታ ምን ያደርግለታል›› የሚሉ አስተዳዳሪዎች የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነበሩ፡፡ አሁን በአንፃራዊነት ለበረኛ ጓንት ግዢ ብቻ ከ15 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ ክለቦች እና አስተዳዳሪዎች ተፈጥረዋል፡፡ ‹‹ቆሞ ነው የሚውለው፤ ሙዝ ምን ያደርግለታል›› የሚሉ አመራሮች በአንፃራዊነት አሁን አሉ ብዬ አላምንም፡፡ ከበረኛ አልፎ ስለ በረኛ አሰልጣኝ የምናስብበት ጊዜም መምጣቱ ተመስገን ነው፤ ነገር ግን የእኛ የመሰልጠን (ስልጡን መሆን) ፍጥነት የዓለም እግር ኳስ ከሚሄድበት ፍጥነት አንፃር እጅግ ዝግ ያለ ነው እና ሁሌም ቢሆን ለመቅደም ስንቸገር ይስተዋላል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ጊዜ እንደመፍትሄ ተደርጎ የሚወሰደው ‹‹የውጭ ሀገር ግብ ጠባቂዎችን የማገድ›› የክልከላ ሥርዓት ላይ ወደ ፊት በዚሁ በሶከር ኢትዮጵያ ላይ የማቀርበው ፅሁፍ እንዳለ ሆኖ ይህ ኢ-እግር ኳሳዊ ፣ አግላይ እና የእግር ኳስን ዓለም አቀፍ ባህሪ የሚፃረር ጥንስስ ባይፀድቅ እወዳለሁ (ደግሞ የተጨዋቾች ደላላ ነው በሉኝ!)፡፡

በፅሁፉ ላይ የተነሱ ሀሳቦች የፀሀፊው የግል ዕይታዎች መሆናቸውን ለመግለፅ እንወዳለን !