ዋልያዎቹ ቀጣይ የሜዳ ላይ ጨዋታቸውን ሀገር ውስጥ አያደርጉም

በመጋቢት ወር ከጊኒ ጋር ወሳኝ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች የሚጠብቀው ዋልያው የሜዳ ላይ ጨዋታውን በሀገር ቤት እንደማይከውን እርግጥ ሆኗል።

\"\"

በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የአህጉሪቱ ብሔራዊ ቡድኖች የምድብ የማጣሪያ ፍልሚያቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ። ከግብፅ፣ ማላዊ እና ጊኒ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በሁለት ጨዋታዎች ሦስት ነጥብ በማግኘት በግብ ልዩነት ቀዳሚ ደረጃን የያዘ ሲሆን በመጋቢት ወር ባለው የብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ደግሞ የምድብ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታ ከሜዳው ውጪ እና በሜዳው ለማድረግ መርሐ-ግብር ተይዟል። ታዲያ በሀገራችን የካፍን መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም ባለመኖሩ ለስደት የተዳረገው ቡድኑም ቀጣይ ጨዋታውን በደጋፊው ፊት እንደማያደርግ ተረጋግጧል።

\"\"

በዛሬው ዕለት በተገኘው መረጃ መሠረት ሀገራት የምድብ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታቸውን የሚያደርጉበት ስታዲየምን ሲታወቅ ሀገራችን ኢትዮጵያ መስፈርቱን የሚያሟላ መጫወቻ ሜዳ ባለማስመዝገቧ በመጋቢት ወር የሚደረገው ጨዋታ ከሀገር ውጪ እንደሚደረግ ታውቋል።

በወጣው ዝርዝር የደርሶ መልስ ተጋጣሚያችን ጊኒም እንደ ኢትዮጵያ ፍቃድ ያለው ስታዲየም ባለማስመዝገቧ በሜዳዋ የምታደርገውን ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ የምታደርግ ይሆናል። ይህንን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከጊኒ ጋር የምታደርገው የደርሶ መልስ ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ እንደሚደረግ ይጠበቃል።