በለገጣፎ ጉዳይ ዙሪያ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሀፊ ሀሳባቸውን አጋርተውናል

👉\”ዝውውር ተፈቅዶ ቴሴራ ያሟላን ተጫዋች አትወዳደርም ልትለው በፍፁም አትችልም\”

👉\”እንደ ፌዴሬሽን በሆደ ሰፊነት ብዙ ነገሮችን ለማየት ሞክረናል\”

👉\”እንደ የበላይ አካል ህግን እናስከብራለን\”

ለገጣፎ ለገዳዲ እና መቻል ሊያደርጉት የነበረው የትናንት ምሽት የ15ኛ ሳምንት ጨዋታ ለገጣፎ ለገዳዲ በሁለተኛው ዙር የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ያስፈረማቸውን ተጫዋቾች የአንደኛው ዙር የሊጉ ውድድር ሳይጠናቀቅ መጠቀም አይችልም በሚል ውዝግቦች ተነስተውበት የጣፎ የቡድን አባላት ወደ ሜዳ መግባት ሳይችሉ ቀርተው እንነበር ይታወሳል። የመቻል ተጫዋቾች እና የዕለቱ ዳኞች ግን ወደ ሜዳ በመግባት 30 ደቂቃ ከቆዩ በኋላ ጨዋታው በፎርፌ ውጤት እንዲጠናቀቅ ተደርጓል። ከፍተኛ ውዝግብ ያስነሳውን ጉዳይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንዴት እንደሚመለከተው ለማወቅ የጽሕፈት ቤት ሀላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁንን አግኝተን ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል።

\"\"

በቅድሚያ ለገጣፎ ለገዳዲ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በዝውውር መስኮቱ በህጋዊነት ያስፈረማቸውን ተጫዋቾች ለአክሲዮን ማኅበሩ እንዲያሳውቅለት በጠየቀው ጥያቄ መሰረት ፌዴሬሽኑ ለሊጉ አስተዳደር በደብዳቤ ማሳወቁን የገለፁት የጽሕፈት ቤት ሀላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን አንድ ተጫዋች አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ በህጋዊነት ፈርሞ ቴሴራ ካገኘ እንዳይጫወት የሚያግደው ህግ እንደሌለ አመላክተዋል።

\”ዝውውር ተፈቅዶ ቴሴራ ያሟላን ተጫዋች አትወዳደርም ልትለው በፍፁም አትችልም\” የሚል ሀሳብ ያነሱት አቶ ባህሩ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ከተጫዋች ተገቢነት ጋር የተገናኘ ሥራ መስራት እንደማይችል ከገለፁ በኋላ እንደ እግርኳስ ፌዴሬሽን ህግ እና ሥርዓትን ማስከበር ግዴታቸው እንደሆነ ገልፀው ነገሩን በጥንቃቄ እንደሚመለከቱ ተናግረዋል። ከትናንቱ ጨዋታ በፊትም ፌዴሬሽኑ የሚመለከተውን አካል የመምከር እና የማስረዳት ሥራ መስራቱን አውስተው ህጉ ለለገጣፎ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ክለቦች እንደሚሆን አስረድተዋል።

እንደ አቶ ባህሩ አገላለፅ የትናንቱ ጨዋታ ተከናውኖ የተጫዋች ተገቢነት ክስ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቀርቦ ጉዳዩ መታየት የነበረበት ቢሆንም ከዚህ ባፈነገጠ መልኩ ሚና እና ስልጣንን ባለማወቅ የተፈጠረውን ነገር ፌዴሬሽኑ እንደማይታገስ አስቀምጠዋል። ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንትም በድሬዳዋ እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ የቀረበውን የተጫዋች ተገቢነት ክስ በተመለከተ ተጠይቀው ማብራሪያ እንደሰጡ አመላክተዋል።

\"\"

ዋና ፀሐፊው \”እንደ ፌዴሬሽን በሆደ ሰፊነት ብዙ ነገሮችን ለማየት ሞክረናል። በቀጣይም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በህጉ መሰረት ህግ የማስከበር ስራ ይከውናል። ይህ ማለት ጣልቃ የመግባት እና ነገሮችን የመበጥበጥ ጉዳይ አይደለም ፤ ህጉን የማስከበር እንጂ። ስህተቱን የማረሚያ ብዙ ጊዜያት ነበሩ። እነዛ ጊዜያት ግን ታልፈዋል። ስለዚህ ከዚህ በኋላ ነገሩን በደንብ አይተን ክፍተቱ የቱ ጋር እንደሆነ እናስቀምጣለን። እንዳልኩት ደግሞ እንደ የበላይ አካል ህግን እናስከብራለን።\” በማለት ሀሳባቸውን ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል።