መረጃዎች | 61ኛ የጨዋታ ቀን

በሦስተኛ ቀን የ15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የሚደረጉ ሁለት መርሐ-ግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰባስበናል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ሲዳማ ቡና

ምንም እንኳን በመካከላቸው የስምንት ነጥብ ልዩነት ቢኖርም በደረጃ ሰንጠረዡ የወራጅ ቀጠና ላይ የሚገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሲዳማ ቡና የመጀመሪያውን ዙር በድል በመቋጨት ሰፊ ስራ ለሚጠብቃቸው የሁለተኛ ዙር ውድድር ስንቅ የሚሆን ውጤት ለማግኘት የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል።

በ14 ሳምንታት የሊጉ ቆይታ አንድ ድል ብቻ ያሳኩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ባለፉት 10 ጨዋታዎች በድምሩ ከአራት ነጥብ በላይ ማግኘት ተስኗቸው አደገኛው ቀጠና ላይ ተቀምጠዋል። እርግጥ ቡድኑ በመጥፎ የውጤት ጎዳና እየተጓዘ ቢገኝም በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ግን ብዙ ለትችት የሚዳርገው ብቃት አያሳይም። በዋናነት ግን በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች በተለይ ደግሞ በራሱ የግብ ክልል ክፍተቶች ያሉበት ሲሆን በአንፃራዊነት ከሚቀርበው ሲዳማ ላለመራቅ የጠቀስነውን ችግሩን ደፍኖ ነገ ወደ ሜዳ መግባት ይገባዋል።

\"\"

ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ የተረቱት ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው በአንፃራዊነት ሽንፈቶች ባይበረክትባቸውም በተቃራኒው አመርቂ የሚባል ድል እያገኙ አይገኝም። ከተደጋጋሚ ሽንፈት መውጣታቸው ጥሩ ቢሆንም ካሉበት አደገኛ ቀጠና አንፃር እንደ ለገጣፎው ጨዋታ ማሸነፍ አለባቸው። በተለይ ደግሞ በየጨዋታው የሚያስተናግዱትን ግብ መቀነስ ይገባቸዋል። በዚህም የቡድኑ የፊት መስመር የሚያስቆጥረውን ግብ የሚያስጠብቅ አስተማማኝ የኋላ መስመር መገንባት ይጠበቅባቸዋል። በጣፎውም ጨዋታ ይህ በጥሩ ሁኔታ ስለታየ በነገው ጨዋታ የኋላውን አደረጃጀት አስጠብቆ መምጣት ያስፈልጋል።

በኢትዮ ኤሌክትሪክም ሆነ በሲዳማ ቡና በኩል ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና እንደሌለ ከክለቦቹ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ቡድኖቹ እስካሁን 18 ጊዜ ተገናኝተው ኤሌክትሪክ 6 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ሲዳማ 4 አሸንፎ በ 8 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ኤሌክትሪክ 15 ሲዳማ በበኩሉ 16 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

በነገው ዕለት ዳንኤል ይታገሱ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ሲመራ እሰባለው መብራቱ እና ሚፍታህ ሁሴን ረዳት እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በበኩሏ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተመድበዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ፋሲል ከነማ

የጨዋታ ሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ እንደሆነ የሚታሰበው የኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከነማ መርሐ-ግብር ጥሩ ፉክክር እንደሚደረግበት ይገመታል። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች አምስቱን ብቻ በተመሳሳይ ያሳኩት ቡና እና ፋሲል ወደ ወጥ ብቃት በመመለስ በደረጃ ሰንጠረዡ ሽቅብ ለመውጣት የነገውን ጨዋታ ይፈልጉታል።

በጊዜያዊ አሠልጣኙ ዮሴፍ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና ከሦስት ጨዋታዎች ያለማሸነፍ ጉዞ በኋላ አዳማ ከተማን ያሸነፈ ቢሆንም ያንን መልካም ውጤት ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ማስቀጠል አልቻለም። እርግጥ ውጤቱ ማሸነፍ ባይሆንም ሳይሸነፍ በሜዳ ላይ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ግን መልካም ነበር። በከባዶቹ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና መቻል ጨዋታም ተጋጣሚን የፈተነ ብቃት ሲያሳዩ ተስተውሏል። ይህ የእንቅስቃሴ እድገት በውጤት እንዲታጀብ ከጣሩ ደግሞ ነጥባቸውን ሀያዎቹ ውስጥ በማስገባት እስከ አራተኛ ደረጃ ሊመነደጉ ይችላሉ።

\"\"

በአዲሱ አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመራ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር የታረቀበትን ውጤት ያገኘው ፋሲል ከነማ ሦስት ነጥብ ባሳካበት ፍልሚያ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር እንዲሁም አጠቃላይ ጨዋታውን በመቆጣጠሩ ረገድ መሻሻል አሳይቷል። እርግጥ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች በአንፃራዊነት ጫናዎች በዝቶባቸው የነበረ ቢሆንም ከአዲስ አሠልጣኝ መቀጠር ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የውጤት ፌሽታ ጊዜ ማስቀጠል ይገባቸዋል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች የአስራት ቱንጆን ግልጋሎት ነገም ሲያጡ ፋሲል ከነማዎች በበኩላቸው የፍቃዱ ዓለሙ መድረስ እና አለመድረስ አጠራጣሪ ሆኖባቸዋል። 

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን አስር ጊዜ የእርስ በእርስ ጨዋታዎች አድርገዋል። በውጤቱ ፋሲል ከነማ አራት ጊዜ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ሦስት ጊዜ ሲያሸንፉ ቀሪ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ፈፅመዋል። በጎሎች ረገድ ደግሞ ሁለቱም እኩል አስራ አንድ አስራ አንድ ጎሎችን አስቆጥረዋል።

የምሽቱን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ ከረዳቶቹ ዳንኤል ጥበቡ እና መሐመድ ሁሴን እንዲሁም አራተኛ ዳኛው ሰለሞን አሸብር ጋር በጋራ ይመሩታል።