የለገጣፎ ለገዳዲ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ሀሳብ…

👉\”አሁንም በዚህ መልኩ የሚቀጥሉ ከሆነ እና መፍትሔ ካላገኘን ቀጣዩን ጨዋታም ለመጫወት እንቸገራለን\”

👉\”ይህ ጉዳይ በህግ እንዲፈታ ከንቲባው እና የክልሉ አመራሮች ባሉበት እንደ ቦርድ ቁጭ ብለን ወስነናል ፤ ጉዳዩንም ለጠበቃ ሰጥተነዋል\”


👉\”ይህንን ነገር ፌዴሬሽኑ እልባት ይሰጠዋል ብለን እናስባለን ፤ እልባት ካላገኘ እኛ ሊጉ ውስጥ ለመቆየት እንቸገራለን\”

በለገጣፎ ለገዳዲ ዙሪያ በተነሳ የተጫዋች ተገቢነት ክስ በትናንትናው ዕለት ሊደረግ የነበረው የመቻል ጨዋታ ሳይከናወን እንደቀረ ይታወቃል። ከጨዋታው በፊትም ሲነሳ የነበረው ይህ በሁለተኛ ዙር የዝውውር መስኮት የፈረሙ ተጫዋቾች ጉዳይ በትናንትናው ዕለትም ተነስቶ ክለቡ አዲሶቹን ተጫዋቾች ለመጠቀም በአሰላለፉ ቢያካትም የሊጉ የበላይ አካል የመጀመሪያው ዙር ሳይጠናቀቅ መጠቀም አይችልም በማለቱ ጨዋታው በፎርፌ ውጤት መጠናቀቁ ይታወቃል። ከፍተኛ ውዝግብ ያስነሳውን ጉዳይ ለማጥራት ሶከር ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበርን አመራሮች ያናገረች ሲሆን የጉዳዩ ቀጥተኛ ባለቤት የሆነው ለገጣፎን በተመለከተ ያለውን ሀሳብ እንዲያጋሩን ደግሞ ሥራ አስኪያጁን አቶ ገዛኸኝ አውርተናል።

\"\"

ዝውውሩን ካደረጉ በኋላ የመጀመሪያው ዙር ውድድር ሳይጠናቀቅ ተጫዋቾቹን መጠቀም አትችሉም የሚል ትዕዛዝ ሲተላለፍላቸው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር አመራሮችን በስልክ እና በአካል አውርተው አካሄዱ ልክ እንዳልሆነ እንደገለፁ የተናገሩት የክለቡ ሥራ-አስኪያጅ \”ይህን ነገር እኛ ከመጀመሪያውም በጥንቃቄ ልንይዘው ፈልገን ነበር። የሊግ ካምፓኒውን አመራሮች አግኝተን በአግባቡ ይህ ነገር በደንብ ቢጤን ጥሩ ነው ብለን በደንብ ገልፀንላቸዋል። የሚገርመው ለአቶ ክፍሌ ዝውውሩ ጥር 18 ሊዘጋ አንድ ቀን ቀድሞ ጥር 17 ምሽት 11፡30 ላይ ደውልኩለት ፤ እሱ ደብዳቤ ፅፎ ለጠፈ። ይህ ነገር ልክ አይደለም ስንለው በፍጹም ሊሰማን አልቻለም። በአካልም ሄደን ጠይቀን የሰጠኝ ምላሽ \’እኛ የዝውውር መስኮት ስንከፍት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለቻን ውድድር ሲሄድ ይቺን ዕድል እንጠቀም ብለን በቀና ሀሳብ ነው የከፈትነው እንደዚህ ዓይነት ነገር ያመጣብናል የሚለውን ነገር አላሰብንም\’ የሚል ነው። ይሄንን ሲለን አራት ሰው ማረጋገጫ አለ።\” ብለዋል።

\”ለለገጣፎ ለገዳዲ ተብሎ የሚከፈት ሁለተኛ የዝውውር መስኮት የለም ፤ ስለዚህ ይህን ዕድል መጠቀም ደግሞ ግዴታችን ነው\” የሚሉት አቶ ገዛኸኝ ቡድኑን ከመውረድ ለመታደግ 18 ተጫዋቾችን ቀንሰው በዝውውር መስኮቱ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን እንዳስፈረሙ ተናግረዋል።

ሥራ አስኪያጁ ቀጥለው \”ሊግ ካምፓኒው እንደ ክለቦች ተወካዮች ሳይሆን እንደ አንድ የግል ድርጅት ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው። የማይመለከተውን የፌዴሬሽኑን ስልጣን ሲወስድ እኔ በራሴ ሄጄ አናግሬዋለሁ። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ነገር ልክ አይደለም የኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ መጥፎ ተፅዕኖ አለውና ይህን ነገር አስተካክሉ ስንል በማን አለብኝነት ጉዳዩን ወደ ጎን ትተው ባለፈውም አሁንም በፖሊስ ከልክለው ጨዋታውን እንዳናደርግ አድርገውናል። እኛ የምናውቀው ቲሴራ የቀበሌ መታወቂያ አይደለም። ህጋዊ የሆነ የአንድ ሀገር ፌዴሬሽን ህጋዊ ካደረገን በኋላ ሊግ ካምፓኒው አትጫወትም ብሎ ህግ የማውጣት ስልጣን ደግሞ የለውም። የእኛ ወኪል ነው ፤ ለእኛ መከራከር ሲገባ የክለብ ወኪል እንዳልሆነ እንደዚህ ዓይነት ሴራ ሲሠራብን እንደ ስፖርቱ ቤተሰብ በጣም ተሰምቶናል። ጉዳዩንም ለጠበቃ ሰጥተነዋል። አንደኛ ከፌዴሬሽኑ ህግ የሚጻረር ነው ሁለተኛ ከፊፋ ህግ ጋር የሚጻረር ነው። ይህ ጉዳይ በህግ እንዲፈታ ከንቲባው እና የክልሉ አመራሮች ባሉበት እንደ ቦርድ ቁጭ ብለን ወስነናል\”

\"\"

በመጨረሻ \”አሁንም በዚህ መልኩ የሚቀጥሉ ከሆነ እና መፍትሔ ካላገኘን ቀጣዩን ጨዋታም ለመጫወት እንቸገራለን። ምክንያቱም ስድስት ነጥብ ቀላል አይደለም። ይህንን ነገር ፌዴሬሽኑ እልባት ይሰጠዋል ብለን እናስባለን። እልባት ካላገኘ እኛ ሊጉ ውስጥ ለመቆየት እንቸገራለን። እኛ የምንለው ህግ ይከበር ነው። ሊግ ካምፓኒው እጁን ያውጣ እና የሚመለከተውን ይሥራ ፌዴሬሽኑም የሚመለከተውን ይሠራል። ስለዚህ ሊግ ካምፓኒው ከተግባሩ እና ከስልጣኑ ውጪ ሄዶ የሚሠራቸው ነገሮች የኢትዮጵያን እግርኳስ ይጎዳሉ።\” የሚል ሀሳባቸውን ሰጥተውናል።

ሶከር ኢትዮጵያ የሦስቱንም አካላት ሀሳብ ለማስተናገድ የሞከረች ሲሆን በጉዳዩ ዙሪያ የሚኖሩ አዳዲስ ነገሮችን እየተከታተለች እንደምታቀርብ ለመግለፅ ትወዳለች።