መረጃዎች | 62ኛ የጨዋታ ቀን

የአንደኛው ዙር ማጠናቀቂያ የሆኑትን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ድሬዳዋ ከተማ

በ 29 ነጥቦች በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ቅዱስ ጊዮርጊሶች 13ኛ ደረጃ ላይ ካሉት ድሬዳዋ ከተማዎች ጋር የሚያገናኘው ጨዋታ ለፈረሰኞቹ የዋንጫ ግስጋሴ ለብርቱካናማዎቹ ደግሞ ወደ አሸናፊነት ተመልሶ ከወራጀ ቀጠናው ለመራቅ ብርቱ ፍልሚያ ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በሊጉ እስካሁን አንድ ጨዋታ ብቻ ተሸንፈው ከሁሉም ቡድኖች በበለጠ ከፍተኛውን ግብ (30) አስቆጥረው በአንጻሩ ዝቅተኛ ግብ(8) ያስተናገዱት ፈረሰኞቹ በእንቅስቃሴ ደረጃ ተበልጠውም ውጤት ይዘው የሚወጡበት መንገድ ለዋንጫ ቅድሚያ ግምት እንዲሰጣቸው የሚያደርግ ሲሆን ያለው የቁጥር ማስረጃ  ቡድኑ ዘንድሮ ምርጥ ብቃት ላይ እንዳለ የሚያሳይ ነው። በድሬዳዋ የመጀመሪያ ቆይታቸውን በሦስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች መጠነኛ መንገራገጭ አጋጥሟቸው የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ቀጣይ ካደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ግን አራቱን መርታት ችለዋል። ይህም ለነገው ጨዋታ ትልቅ መነሳሳትን እንደሚፈጥርላቸው ይጠበቃል።

\"\"

በመቀመጫ ከተማቸው ስኬታማ አጀማመር ማድረግ ችለው የነበሩት ድሬዎች ከተማቸው ላይ ከመጀመሪያዎቹ አራት የጨዋታ ሣምንታት ከጠንካራ እንቅስቃሴ ጋር በሦስቱ አሳማኝ ድል ተቀዳጅተው ነበር። ይሁን እና ቡድኑ ቀስ በቀስ እየተዳከመ ሄዶ ያለፉት ሦስት ጨዋታዎች ላይ አንድም ነጥብ ካለማሳካቱ በላይ ከአንድ ግብ በላይ አለማስቆጠሩ ደግሞ ቡድኑ ፈታኝ ወቅት ላይ መሆኑን ያመላክታል። ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ብቻ ርቀው የሚገኙት ብርቱካናማዎቹ የደረጃውን አናት ለመቆጣጠር በትልቅ ተነሳሽነት ከሚገቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጋር የሚጠብቃቸው ፈተናም ቀላል እንደማይሆን ይጠበቃል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ከወጣቱ ሻይዱ ሙስጠፋ በቀር አዲስ የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን ድሬዎች በአንጻሩ የቻርለስ ሙሲጌ እና የሱራፌል ጌታቸውን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት አያገኙም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ20 ጊዜያት ተገናኝተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ 13ቱን በመርታት ቀዳሚ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 3ቱን አሸንፏል። ቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ፍፃሜያቸውን አግኝተዋል።

ባህርዳር ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

በአንደኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ በአምስት ደረጃዎች እና በስድስት ነጥቦች ልዩነት 3ኛ እና 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት የጣና ሞገዶቹ ከጦና ንቦቹ ጋር ሲገናኙ ሁለቱም ቡድኖች ፕሪሚየር ሊጉ ለቻን ከመቋረጡ በፊት በድሬዳዋ ቆይታቸው ከፍተኛውን ነጥብ (17) በዕኩል ማሳካት ችለው የነበረው ሲሆን ባለፈው የጨዋታ ሣምንት ያላሳኩትን ሙሉ ሦስት ነጥብ በማግኘት ባህርዳሮች ከደረጃ ሠንጠረዡ መሪዎች ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ወላይታ ድቻዎችም ከመሪዎቹ ላለመራቅ ብርቱ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከአንድ ወር በፊት የሊጉ የወቅቱ ምርጥ ቡድን የነበረው ባህርዳር ከተማ ዓምና ከነበረበት የውጤት ማጣት ችግር አንጻር ዘንድሮ ሳይታሰብ ለዋንጫ ቢጠበቅም ቡድኑ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ማሸነፉ የነበረውን ግለት እያቀዘቀዘበት መጥቷል። በሊጉ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጥል ዝቅተኛ ሽንፈት (2) ያስተናገዱት የጣና ሞገዶቹ  በየጨዋታዎቹ መኃል ሜዳው ላይ እና በመስመር የማጥቃት እንቅስቃሴ ብልጫ ቢወስዱም ሁነኛ አጥቂ አለማግኘታቸው ድል እንዳያደርጉ ትልቅ መሰናክል የሆነባቸው ይመስላል። ከዋናው አጥቂያቸው ኦሴ ማውሊ ጋር በዲስፕሊን ምክንያት የተለያዩት ባህርዳሮች ይህ ክስተት የዝውውር መስኮቱ ከተዘጋ በኋላ የተከሰተ ከመሆኑ አንጻር ወደፊት በምን መንገድ ይቀጥላሉ የሚለው የሚጠበቅ ነው።

\"\"

ከተቀዛቀዘው የሊግ ጅማሪያቸው በፍጥነት በማገገም በድሬዳዋ ከተደጋጋሚ ድሎች ጋር የታረቁት ወላይታ ድቻዎች ከሚታወቁበት ጠጣር የመከላከል አጨዋወት እየወጡ ይመስላል። በተለይም ቡድኑ ከተቆጠረበት (13) ግብ ስድስት የሚሆኑት (46.15%) ግቦች የተቆጠሩት ባለፉት አራት ጨዋታዎች መሆኑ ደሞ ይህንን ይደግፋሉ። ድቻዎች ባለፈው ሣምንት በወልቂጤ ከተማ 1ለ0 ሲሸነፉ ያሳዩት የማጥቃት እንቅስቃሴ እና የፈጠሩት የግብ ዕድል ግን ተስፋን የሚሰንቅ ነው። በነገው ዕለትም በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ለመውሰድ አቅደው ከሚገቡት ባህርዳሮች ጋር በምን መንገድ ይቀርባሉ የሚለው የሚጠበቅ ነው።

በወላይታ ድቻ በኩል ጉዳት ላይ የሰነበቱት አንተነህ ጉግሳ እና ደጉ ደበበ ቀለል ያለ ልምምድ ቢጀምሩም ለነገው ጨዋታ የማይደርሱ ሲሆን ከእነሱ በተጨማሪም በኃይሉ ተሻገር ባጋጠመው መጠነኛ ጉዳት ሌላው የነገው ጨዋታ የሚያልፈው የድቻ ተጫዋች ነው። በአንጻሩ በባህርዳር ከተማ በኩል ሁሉም ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው ተጠቁሟል።

ባህር ዳር ከተማ እና ወላይታ ድቻ እስካሁን በሊጉ በስድስት አጋጣሚዎች ተገናኝተዋል። በአራቱ ግንኙነታቸውን አቻ ሲለያዩ አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈዋል። በጨዋታዎቹ እኩል አምስት አምስት ግቦችንም አስቆጥረዋል።