ሪፖርት | ተጠባቂው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

የቡናማዎቹ እና ዐፄዎቹ ጨዋታ በአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች ባለፈው ሳምንት ከመቻል ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ ዐፄዎቹ በበኩላቸው ሀድያን ካሸነፈ ስብስብ ሀብታሙ ገዛኸኝን ብቻ በአስቻለው ታመነ ቀይረው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ሁለቱም ቡድኖች የመሀል ሜዳ የበላይነት ለመውሰድ በምያደርጓቸው ጥረቶች የጀመረው ጨዋታው በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥር ረገድ የቡናማዎቹ ብልጫ የታየበት ነበር። ሆኖም ብልጫው ለብዙ ደቂቃዎች ሳይቀጥል ዐፄዎቹ የኃይል ሚዛኑን ቀልብሰው ሁለት የግብ ዕድሎች ፈጥረው አንዱን ወደ ግብነት ቀይረዋል። በዚህም የመጀመርያው ሙከራ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ቡናዎች የኳስ አመሰራረት ስህተት ያገኛት ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ ስትሆን በአስራ አምስተኛ ደቂቃ ደግሞ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ሱራፌል ዳኛቸው ከቆመ ኳስ ያሻማውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። በግቡ ሂደት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ግልፅ የቆመ ኳስ መከላከል ስህተት ተስተውሏል።

ብዙ ጥፋቶች(13) በተስተዋሉበት አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥቂት ሙከራዎች እና ጥቂት የግብ ዕድሎች የፈጠሩበት ነበር። በሰላሳ አራተኛው ደቂቃም ኢትዮጵያ ቡናዎች በአምበሉ አማኑኤል ዮሐንስ አማካኝነት የፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥረው አቻ መሆን ችለዋል። ቡናዎች ከግቧ በኋላም ሙከራ ማድረግ ችለዋል ፤ ሙከራውም መስፍን በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ካደረገው ሮቤል የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ኳስ ነበረች። ወደ ሙከራነት አልተቀየሩም እንጂ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ የተሻለ የነበሩ ዐፄዎቹ በመጨረሻው የአጋማሹ ደቂቃ በዓለምብርሃን ይግዛው አማካኝነት ጥሩ ዕድል ፈጥረው ነበር።

ኢትዮጵያ ቡናዎች ጫና ፈጥረው የጀመሩት ሁለተኛው አጋማሽ በመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች በርካታ ሙከራዎች ተደርገውበታል። በዚህም ቡናማዎቹ በብሩክ አማካኝነት ያደረጉት የግንባር ሙከራ እና ራምኬል ከመዓዘን የተሻገለውን ኳስ አግኝቶ ወደ ላይ ያወጣው አጋጣሚ እጅግ ወርቃማ ዕድል የነበሩና ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ ኳስ ከመቆጣጠር ይልቅ ወደ ቀጥተኛ እና የመስመር አጨዋወት ያዘነበሉት ፋሲል ከነማዎች በሀምሳ ሰባተኛው ደቂቃ በግቡ ባለቤት ናትናኤል አማካኝነት መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ሙከራውም ሱራፌል ዳኛቸው በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ኳስ ለናትናኤል አቀብሎት አጥቂው ግብ ጠባቂውን አታሎ ያመከነው ድንቅ አጋጣሚ ነበር። ዐፄዎቹ ከደቂቃዎች በኋላም በሱራፌል ዳኛቸው በኩል ሳጥን ውስጥ ጥሩ ሙከራ አድርገው በግብ ጠባቂው ተመልሶባቸዋል።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ በጥራት የተሻሻለ የማጥቃት ሽግግር ያስመለከቱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በጥሩ አጨዋወት ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም መሐመድኑር በጥሩ ሽግግር የመጣውን ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ ለአብዱልከሪም አመቻችቶለት አማካዩ ያደረገው ሙከራ ጥሩ ለግብ የቀረበ ነበር። ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ካደረጉ በኋላም ጫና ፈጥረው የተጫወቱ ሲሆን በመስፍን እና አማኑኤል እጅግ ለግብ የቀራቡ ሌሎች ሙከራዎች አድርገዋል። መስፍን በመስመር ተከላካይነት የተሰለፈው ጫላ ያሻገረለትን ኳስ በምያስደንቅ የአክሮባቲክ ምት ሞክሮት ሳማኪ በጥሩ መንገድ ወደ ውጭ ሲያወጣው አምበሉ አማኑኤልም ከአብዱልከሪም አንድ ሁለት ተቀባብሎ ያገኘውን ኳስ መቶ በዛብህ መለዮ በምያስደንቅ ሸርተቴ ቡድኑን ታድጓል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩት እና የዳኛውን ፊሽካ በሚጠበቅበት ቅፅበት መስፍን ከኃ\\ሚካኤል ጥሩ ኳስ አግኝቶ ከተከላላዮች ጀርባ በመሮጥ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ በማይታመን መልኩ ወደ ግብነት ሳይቀይረው ቀርቷል። ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁ ተከትሎም ኢትዮጵያ ቡናዎች በተከታታይ አቻ የወጡበት ውጤት አስመዝግበዋል።

ከጨዋታው በኋላም የሁለቱ ቡድኖች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በቅድምያ ሀሳባቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ቡናው ጊዜያዊ አሰልጣኝ ዮሴፍ \”ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ ቡድናችን እየተሻሻለ ነው። ቡድናችን ከገባበት በኋላ ነው የሚነቃቃው ፤ ይህንን ችግርም መፍታት ይጠበቅብናል \” ሲሉ በተከታታይ ጨዋታዎች መጀመርያ ላይ ግብ የማስተናገድ ችግራቸው እንደሚቀርፉ ገልፀዋል። ቀጥለውም \”በሦስቱም ጨዋታዎች ማሸነፍ ነበረብም\” ሲሉ በሦስቱም ጨዋታዎች ሙሉ ዘጠኝ ነጥብ ይገባቸው እንደነበር ጠቁመዋል።

\"\"

ቀጥለው አስተያየታቸው የሰጡት የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ አሸናፊ \”ፍ.ቅ.ም ከተቆጠረብም በኋላ ብዙ መሻሻል ያለባቸው ችግሮች ተስተውለንበታል \” ካሉ በኋላ ተጋጣሚያቸውን \”ቡና እየተሻሻለ ነው ፤ በዚህ አጋጣሚ አሰልጣኙ ሳላደንቅ አላልፍም\” በማለት አድንቀዋል። በመጨረሻም ስለወጣቱ አጥቂ የተጠየቁት አሰልጣኙ ናትናኤል የቡድኑን ክፍተት በጥሩ ሁኔታ እንደሸፈነ ገልፀዋል።