ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ወሳኝ ተከታታይ ድል አስመዝግቧል

በከባድ ዝናብ ምክንያት ተቋርጦ ከ18ኛው ደቂቃ ጀምሮ ዛሬ በተደረገው ጨዋታ ሲዳማ ቡና በሳላዲን ሰይድ ብቸኛ ግብ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1ለ0 መርታት ችሏል።

10፡00 ሲል ቅዳሜ ዕለት በከባድ ዝናብ ምክንያት 18ኛው ደቂቃ ላይ ለመቋረጥ የተገደደው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የሲዳማ ቡና ጨዋታ ሲደረግ ኤሌክትሪኮች በ14ኛው ሣምንት በፋሲል ከነማ 2-1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ሚኪያስ መኮንን በ ናትናኤል ሰለሞን ተክተው ሲጀምሩ ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው በ 14ኛው ሣምንት ለገጣፎ ለገዳዲን 2-0 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ አቤል እንዳለን አስወጥተው ቴዎድሮስ ታፈሠን አስገብተው ጀምረዋል።

\"\"

ጨዋታው ከቆመበት 18ኛ ደቂቃ ላይ መደረጉ ሲቀጥል የሲዳማው የመስመር ተከላካይ መሃሪ መና ከጨዋታው በፊት በነበረው የሟሟቂያ ጊዜ ባስተናገደው ጉዳት ጨዋታውን ባለመቀጠሉ በሰለሞን ሀብቴ ተተክቶ ወጥቷል። በሁለቱም ቡድኖች በሚታየው ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ጥሩ ፉክክር ባስመለከተን የመጀመሪያ አጋማሽ በመጀመሪያ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡናዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝቶ በመግባት በተሻለ ሁኔታ ተጭነው ሲጫወቱ የመጀመሪያው ሙከራ ግን 31ኛው ደቂቃ ላይ በኢትዮ ኤሌክትሪኮች ተደርጓል። ልደቱ ለማ በጥሩ ክህሎት ጊት ጋትኩትን አታልሎ በማለፍ ከሳጥን አጠገብ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቶበታል።

ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን በተደጋጋሚ እንደመድረሳቸው የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ሲዳማዎች በአጋማሹ የተሻለውን ሙከራ 33ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ሳላዲን ሰዒድ ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብጠባቂው ዘሪሁን ታደለ መልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ አስደናቂ አጀማመር ያደረጉት ሲዳማዎች ለበርካታ ደቂቃዎች ቆይታቸውን በተጋጣሚ የግብ ክልል ሲያደርጉ 51ኛው ደቂቃ ላይም ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ቴዎድሮስ ታፈሰ በግራ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት በግሩም ዕይታ ለሳላዲን ሰይድ አመቻችቶ ሲያቀብል ኳሱን በጥሩ የጊዜ አጠባበቅ ያገኘው ሳላዲንም በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ በስኬታማ የኳስ ቅብብል መኃል ሜዳው ላይ ብልጫ እየወሰዱ የመጡት ኤሌክትሪኮች በተሻለ ሁኔታ ወደፊት ተጭነው ቢጫወቱም የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ይባስ ብሎም 77ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስተናገድ ተቃርበው ነበር። ይገዙ ቦጋለ ከግራ መስመር ወደኋላ በመመለስ ያቀበለውን ኳስ ከተጋጣሚ ሳጥን አጠገብ ያገኘው ቴዎድሮስ ታፈሰ አክርሮ በመምታት ያደረገውን ሙከራ ግብጠባቂው ዘሪሁን ታደለ በጥሩ ቅልጥፍና መልሶበታል።

የአቻነት ግብ ለማስቆጠር መታተራቸውን የቀጠሉት የአሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ ተጫዋቾች 79ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ምቹ አጋጣሚ አግኝተው ነበር። ጌቱ ኃይለማርያም ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ በአብነት ደምሴ እና በጊት ጋትኩት ተገጭቶ ያገኘው ኢብራሂም ከድር በደካማ አጨራረስ በግንባሩ በመግጨት ያደረገውን ሙከራ የኳሱ ኃይል የለሽነት ተጨምሮበት ሳላዲን ሰዒድ ተደርቦ መልሶበታል።

የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ባላቸው ኃይል በሚያደርጉት የማጥቃት እንቅስቃሴ ከኋላ ትተውት የሚመጡትን ክፍት ቦታ በመልሶ ማጥቃት መጠቀም የቀጠሉት የአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ተጫዋቾች በርካታ የግብ ዕድሎችን ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በተለይም ከይገዙ ቦጋለ እና ከሳላዲን ሰዒድ በሚነሱ ኳሶች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የነበራቸውን የግብ ዕድል ባይጠቀሙበትም የያዙትን የ 1-0 መሪነት አስጠብቀው በመውጣት ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች ድል ያደረጉት የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ የዛሬው ድል ለሁለተኛው ዙር ከፍተኛ መነሳሳት እንደሚፈጥርላቸው እና ተጫዋቾች ለማሸነፍ ያደረጉትን የማጥቃት እንቅስቃሴ አድንቀዋል። የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ በበኩላቸው በጨዋታው ከፊትና ከኋላ መስመር ያለባቸው ክፍተት ጎልቶ መታየቱን ሲገልጹ አዲስ ያስፈረሟቸውን ተጫዋቾች መጠቀም ሲጀምሩ ውጤታቸው ይሻሻላል ብለው እንደሚያስቡ ያላቸውን ሀሳብ ሰጥተዋል።