ሪፖርት| ፈረሰኞቹ ተጠባቂውን ጨዋታ በድል ተወጥተዋል

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተጠባቂው ጨዋታ ተከታያቸውን ኢትዮጵያ መድን በማሸነፍ መሪነቱን አስፍተዋል።

በ15ኛው ሳምንት ቡድኖቹ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ በተመሳሳይ የሦስት ተጫዋቾችን ቅያሪ በማድረግ ነበር ለጨዋታው የቀረቡት። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ድሬዳዋን ከረቱበት ስብስብ አማኑኤል ተርፉ ፣ ሱለይማን ሀሚድ እና አማኑኤል ገብረሚካኤልን በምኞት ደበበ ፣ ሔኖክ አዱኛ እና ቸርነት ጉግሳ ሲተኩ ኢትዮጵያ መድኖችም ከሀድያው ጨዋታ ጉዳት በገጠመው አብዱልከሪም መሐመድ ምትክ ቻላቸው መንበሩን ፣ አሚር ሙደሲርን በዮናስ ገረመው እንዲሁም ሀቢብ ከማልን በብሩክ ሙሉጌታ ለውጠዋል።

\"\"

መድኖች ያስጀመሩትን ኳስ ፈረሰኞቹ በፍጥነት ከነጠቁ በኋላ የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ወደ ራሳቸው በማድረግ ለመንቀሳቀስ የሞከሩበትን በአንፃሩ ኢትዮጵያ መድኖች በበኩላቸው የኋላ መስመራቸውን በመዝጋት ጥንቃቄ አዘል አጨዋወትን ተጠቅመው ሊጫወቱ ሲጥሩ በተለይ የመጀመሪያዎቹን ሀያ ደቂቃዎች ላይ ማስተዋል ብንችልም አስቀድሞ ከጨዋታው ተጠባቂነት አንፃር ከጎል ጋር ቡድኖቹ የሚያገናኛቸውን ዕድሎች ለመታዘብ አልታደልንም። ነገር ግን ጨዋታው ሀያውን ደቂቃ ሲሻገር ኳሶቻቸው ሲቆራረጡ ስናስተውል ያየናቸው መድኖች 21ኛው ደቂቃ ላይ ከቆመ ኳስ የጨዋታውን ቀዳሚ አጋጣሚ ፈጥረዋል።

በተጠቀሰው ደቂቃም ከቀኝ የቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ አቅጣጫ ቻላቸው መንበሩ ያሻማትን ቅጣት ምት ሔኖክ እና ፍሪምፓንግ በግንባር ጨራርፈው የሰጡትን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ በቀጥታ መቶ ቻርለስ ሉኩዋንጎ ሲመልሳት አጎሮ በረጅሙ ከራሱ የግብ ክልሎ ያራቃትን ኳስ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በፈጣን መልሶ ማጥቃት ቸርነት እግር ስር ኳሷ ደርሳ ተጫዋቹም ለበረከት አቀብሎት ነፃ ቦታ ላይ ለተገኘው አቤል ያለው አማካዩ ቢሰጠውም በቀላሉ ወደ ጎልነት የመስመር አጥቂው ለወጠው ተብሎ ሲጠበቅ አቡበከር ኑራ በጥሩ ቅልጥፍና መድኖችን ታድጓቸዋል። በቀሩት ቀጣይ ደቂቃዎች በእንቅስቃሴ የታጀቡ ቅብብሎችን በመድኖች በኩል ማየት ብንችልም የጊዮርጊስን አጥር ለማስከፈት በመቸገራቸው የሚያገኟቸውን ኳሶች ከርቀት በመምታት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ጥራት ያላቸውን ግልፅ ዕድሎች ሳናስተውል አጋማሹ 0ለ0 ተገባዷል።

ሁለተኛውን አጋማሽ ተረጋግተው የጀመሩት መድኖች ደቂቃው ብዙም ሳይጓዝ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል። 52ኛ ደቂቃ ከራሳቸው የግብ ክልል ባሲሩ ዑመር በረጅሙ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳ ክፍል ሲያሻግር ኪቲካ ወደ ሳጥኑ ውስጥ በጥሩ ዕይታ የላካት ኳስ ምኞት ደበበ ለማውጣት በሚጥርበት ወቅት ያመለጠችውን ኳስ ሲሞን ፒተር ሉክዋንጎ መረብ ላይ አሳርፏት ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። ጎል ካስተናገዱ በኋላ በፍጥነት ወደ ጨዋታ ለመመለስ ሁለት ደቂቃ ብቻ የፈጀባቸው ጊዮርጊሶች ኦሮ አጎሮ ያረጋጋለትን ኳስ ከሳጥኑ ጠርዝ ቢኒያም በላይ አክርሮ ወደ ጎል ሲመታ አቡበከር ኑራ በሚገርም ብቃት ኳሷን ባዳነበት ሒደት ጥቃትን ጀምረዋል።

በሁለቱ የመስመር ኮሪደሮች ብርቱካናማ ለባሾቹ ያደረጉት ቀዳዳ ፍለጋ 62ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። ቢኒያም በላይ ከማዕዘን ምት ሲያሻማ ከጠባብ አንግል ላይ ፍሪምፖንግ ሜንሱ በግራ እግሩ ደገፍ በማድረግ በአቡበከር መረብ ላይ ቀላቅሎታል። የአቻ ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ እየተቀዛቀዙ የመጡትን መድኖችን ጫና ውስጥ ለመክተት በረከት እና ቸርነትን በአማኑኤል ገብረሚካኤል እና ጋቶች ለውጠው ይበልጥ የማጥቂያ በራቸውን ያሰፉት ጊዮርጊሶች 71ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ሸዋለም በሰራው ስህተት እስማኤል ኦሮ አጎሮ ከሳጥን ውጪ በግሩም ሁኔታ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር ቡድኑን ከተመሪነት ወደ መሪነት አሸጋግሯል።

ከጥቂት ደቂቃዎች መልስ አቤል ያለው ሦስተኛ ልትሆን የምትችል ዕድልን አግኝቶ በቀላሉ ከሳታት በኋላ ከቆሙ ኳሶች የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች መድኖች በሀቢብ መሐመድ የግንባር እና በተካልኝ ደጀኔ የቅጣት ምት ኳሶች እንዲሁም በኪቲካ ጀማ ተጨማሪ ዕድል ያለቀላቸውን አጋጣሚዎች ቢፈጥሩም አስራ አንድ ቢጫ ካርዶችን ያስመለከተን ተጠባቂ ጨዋታ 2ለ1 በሆነ ውጤት በፈረሰኞቹ አሸናፊነት ተደምድሟል።

\"\"

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ጨዋታው ጥሩ እና ጠንካራ እንደ ነበር ከጠቆሙ በኋላ ቀድመው ገምተው የነበረውን ፉክክር ከተጋጣሚያቸው እንዳገኙ እንዲሁም ከየትኛውም ቡድን ጠንካራ ከሆነው ቡድን ጥሩ ውጤት በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረባቸውን ስህተት በሁለተኛው አጋማሽ ታክቲካል ለውጥ አድርገው በማረም ማግኘት እንደቻሉ አብራርተው በመቀጠል ገብቶበት የሚያገባ ቡድን ስላላቸው አሸንፈው መውጣታቸውን ተናግረዋል። የመድኑ አቻቸው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በበኩላቸው የጠበቁትን ፉክክር እንዳገኙ ገልፀው ስህተት ተጠቀሞ ማሸነፍ በሚችል ቡድን ስህተት በመስራታቸው ተጋጣሚያቸው ያገኘውን ዕድል በመጠቀም ማሸነፉን ተናግረው ቡድናቸው ግን በአጠቃላይ በጨዋታው ጥሩ ስለመጫወቱም አውስተዋል።