ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | የ15ኛ ሣምንት ጨዋታዎች ሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሣምንት ዛሬ ሲጠናቀቅ አዲስ አበባ ከተማ ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጋጣሚዎቻችውን መርታት ችለዋል።

አዲስ አበባ ከተማ 1-0 ቦሌ ክ/ከ

ረፋድ ላይ የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ቀዝቀዝ ባለ እና ለጨዋታ ምቹ በሆነ የዓየር ሁኔታ ሲደረግ ጥሩ ፉክክር ባስመለከተን የመጀመሪያ አጋማሽ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝቶ በመድረስ ቦሌዎች የተሻሉ ነበሩ። ሆኖም በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎቸ ውስጥ ቃልኪዳን ንቅበሸዋን በጉዳት ለመቀየር ሲገደዱ ትከሻዋ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስተናገደችው ቃልኪዳንም ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ሆስፒታል አምርታለች። በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉት ሁለት የግብ ዕድሎችም 34ኛው ደቂቃ ላይ በቦሌዎች በኩል ሲፈጠሩ ምርጥነሽ ዮሐንስ በቀኝ መስመር አሻግራው ሜላት ጌታቸው ሳታገኘው ቀርታ የግብ ዕድሉን ሳትጠቀምበት ስትቀር ንግሥት በቀለም ግብ ለማስቆጠር ተቃርባ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ተረባርበው መልሰውባታል።

\"\"

በአዲስ አበባዎች በኩል የመጀመሪያው የተሻለ ሙከራ 54ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ ኪፍያ አብዱልራህማን ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ ትብቃ ፈንቴ አስወጥታዋለች። በሜላት አሊሙዝ ፣ ሜላት ጌቻቸው ፣ ትርሲት ወንደሠን እና ንግሥት የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው የነበሩት ቦሌዎች በተለይም ፊት መስመር ላይ የንግሥት በቀለን የአጨራረስ ብቃት እጅጉን እንደሚሹ በግልጽ ሲታይ እና ጨዋታውንም የተቆጣጠሩት ቢመስሉም ቀስ በቀስ ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ 91ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ተቆጥሮባቸዋል። መሠረት ማሞ ከቅጣት ምት ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ትብቃ ፈንቴ ስትመልሰው ያገኘችው ንግሥት ኃይሉ በቀላሉ በማስቆጠር አዲስ አበባን የ1-0 ድል እንዲቀዳጅ አስችላለች።

\"\"

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3-1 አዳማ ከተማ

08፡00 ሲል በተጀመረው ጨዋታ ለተመልካች አዝናኝ የሆነ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ አዳማዎች በአጋማሹ የመጀመሪያ እና የመጨረሻ ደቂቃዎች በተቀሩት ደቂቃዎች ደግሞ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ብልጫውን ወስደዋል። በርካታ የግብ ዕድሎች በተፈጠሩበት አጋማሽ የተሻለው የመጀመሪያ ሙከራ 20ኛው ደቂቃ ላይ በንግድ ባንኮች ተደርጓል። አረጋሽ ካልሳ እየገፋች በሳጥኑ የግራ ክፍል ይዛው የገባችውን ኳስ ወደ ውስጥ ስታሻግር ያገኘችው መዲና ዐወል ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ መሠረት ባሜ መልሳባታለች። 24ኛው ደቂቃ ላይም የአዳማ ተከላካዮች ከጨዋታ ውጪ ናት ብለው በተዘናጉበት ቅፅበት ሎዛ አበራ ወደ ግራው የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ላይ በግራ አግሯ አክርራ በመምታት መረቡ ላይ ማሳርፍ ችላ ባንክ ጨዋታውን መምራት እንዲጀምር ስታስችል ወደ ዕረፍት ለማምራት የዋና ዳኛዋ ሲሣይ ራያ ፊሽካ ሲጠበቅ አዳማዎች የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ሳባ ኃ/ሚካኤል ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ንግሥት መዓዛ ስትመልሰው ያገኘችው ሔለን እሸቱ በግንባሯ በመግጨት አስቆጥራዋለች።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ግብ አያስቆጥሩ እንጂ በጥሩ የኳስ ቅብብል የማይታሙት አዳማዎች እጅግ ተቀዛቅዘው ሲቀርቡ አይበገሬዎቹ ንግድ ባንኮች ጨዋታውን መቆጣጠር ችለዋል። 52ኛው ደቂቃ ላይም መዲና ዐወል ከቀኝ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ያገኘቸው የአዳማዋ ተከላካይ ሰናይት ሸጉ በግንባሯ ገጭታ ለማስወጣት ስትሞክር ኳሱ አቅጣጫ ቀይሮ የራሷ መረብ ላይ አርፏል።

አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለጊዜ የሰው ሜዳ ላይ ያሳለፉት ባንኮች መሪ ከሆኑ በኋላም በተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲቀጥሉ 55ኛው ደቂቃ ላይ መዲና ዐወል ከሰናይት ቦጋለ በተቀበለችው ኳስ ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ መሠረት ባሜ በእግሯ ስትመልስባት በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም ሎዛ አበራ ያለቀለት ኳስ ብታገኝም ከሷ በማይጠበቅ የአጨራረስ ድክመት ሳትጠቀምበት ቀርታለች። ጨዋታው እየተቀዛቀዘ ሲሄድም አረጋሽ ካልሳ 71ኛው ደቂቃ ላይ በተረጋጋ አጨራረስ ቺፕ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3-1 እንዲጠናቀቅ አስችላለች።

\"\"

ኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-0 አርባምንጭ ከተማ

10፡00 ላይ የሣምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር የሆነው ተጠባቂው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የአርባምንጭ ከተማ ጨዋታ በበርካታ ተመልካቾች ታጅቦ ሲደረግ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ለመውሰድ ብርቱ ፉክክር ሲደረግበት የግብ ዕድሎች ግን በተጠበቀው ልክ አልተፈጠሩም ነበር። በአጋማሹ የተሻለውን ሙከራ ለማስመልከትም 30 ደቂቃ ፈጅቶበታል። የአርባምንጯ ለምለም አስታጥቄ ከሳጥን ውጪ ያደረገችው ሙከራ የግቡን የላይ አግዳሚ ታክኮ ሲወጣ በሴኮንዶች ልዩነት የኤሌክትሪኳ ሰላማዊት ጎሣዬ በቀኙ የሜዳ ክፍል በወሰደችው ኳስ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችላ ነበር። 41ኛው ደቂቃ ላይም የኤሌክትሪኳ ትንቢት ሳሙኤል ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ ቤተልሔም ዮሐንስ መልሳባታለች።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥልም 67ኛው ደቂቃ ላይ ትንቢት ሳሙኤል ግብ አስቆጥራ ኤሌክትሪክን መሪ አድርጋለች። 77ኛው ደቂቃ ላይ በትንቢት ሳሙኤል ተቀይራ የገባችው የኤሌክትሪኳ ሽታዬ ሲሣይም ለጥቂት ደቂቃዎች ባሳየችው እንቅስቃሴ ከተመልካች አድናቆት ተችሯታል። ወደ ጨዋታው ለመመለስ በነበራቸው ጉጉት ባልተረጋጋ የማጥቃት እንቅስቃሴ የቀጠሉት አርባምንጮች በሕይወት ዳንጊሶ የቡድኑን ሚዛን የመጠበቅ ብቃት የሚታገዙትን ኤሌክትሪኮችን አልፈው የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ጨዋታውም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።