በኢትዮጵያ ምድብ የምትገኘው ማላዊ ዝግጅቷን ሳውዲ አረቢያ ላይ እያደረገች ትገኛለች

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዋልያዎቹ ባሉበት ምድብ የምትገኘው ማላዊ ዝግጅቷን ሳውዲ አረቢያ ላይ እያደረገች ሲሆን በነገው ዕለትም የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ትከውናለች።

ባለንበት ዓመት በሚደረገው የአህጉራችን ትልቁ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ብሔራዊ ቡድኖች በ12 ምድቦች ተከፋፍለው የማጣሪያ ፍልሚያቸውን እያከናወኑ የሚገኝ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያም ከማላዊ፣ ግብፅ እና ጊኒ ጋር ተደልድላ ምድቧን እየመራች ትገኛለች።

\"\"

ከኢትዮጵያ በግብ ክፍያ አንሳ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ማላዊ ከግብፅ ጋር በቀናት ልዩነት የሚደረግ የደርሶ መልስ ጨዋታ የሚጠብቃት ሲሆን ለዚህ ፍልሚያ ዝግጅቷን ወደ ሳውዲ በማቅናት እየከወነች ትገኛለች።

20 ተጫዋቾችን (ቀሪ ተጫዋቾች ቡድኑን ዘግየተው እየተቀላቀሉ ነው) ይዞ ከትናንት በስትያ ሳውዲ የደረሰው ልዑካኑም በሚሌኒየም ማዲና ኤርፖርት ሆቴል መቀመጫውን አድርጎ በፕሪንስ መሐመድ ቢን አብዱላዚዝ ስፖርት ሴንተር ልምምዱን እያከናወነ ይገኛል። እስካሁንም ቡድኑ ሦስት የልምምድ መርሐ-ግብሮችን እንደከወነ ተመላክቷል።

\"\"

ቡድኑ ለአንድ ሳምንት ሳውዲ የሚቆይ ሲሆን በነገው ዕለትም ከባንግላዴሽ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ ይዟል።