የከፍተኛ ሊግ አጫጭር የዝውውር መረጃዎች እና ዜናዎች…

በከፍተኛ ሊጉ ያሉ ዝውውሮች እና አጫጭር አዳዲስ መረጃዎችን በተከታዩ ጥንቅር አቅርበንላችኋል።

የዝውውር መረጃዎች

አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ

በአሰልጣኝ ይልቃል የሚመራው አዲስ ከተማ ተከላካዩ ጥላሁን ካሳን ከቡራዩ ከተማ እና የቀድሞው የስሑል ሽረ እና ደደቢት የመስመር አጥቂ ሙሉጌታ አምዶሞን አስፈርሟል።

ሀላባ ከተማ

በምድብ \’ሀ\’ የሚገኘው ሀላባ ከተማ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል። አቦነህ ገነቱ አማካይ ከቦዲቲ ከተማ ፣ አላዛር ዝናቡ አጥቂ ከሀሞበሪቾ ዱራሜ እና ምትኩ ባንዳ የመስመር አጥቂ ከጋሞ ጨንቻ የክለቡ የዝውውር አካሎች ናቸው።

የካ ክፍለ ከተማ

በአሰልጣኝ ባንተይርጋ ጌታቸው የሚመራው የካ ክፍለ ከተማ የቀድሞው የደደቢት እና መቐለ አማካይ የነበረውን ክብሮም ግርማይ ፣ የቀድሞው የአውስኮድ ፣ መቐለ እና ፋሲል አማካይ የነበረውን ወልዳይ ገብረስላሴ እና በስሑል ሽረ ጅማ አባ ጅፋር እና ወልዋሎ የተመለከትነው አማካዩ ብሩክ ገብረአብን አስፈርሟል።

\"\"

ቡራዩ ከተማ

በከፍተኛ ሊጉ የሁለተኛ ዓመት ተሳትፎው ላይ የሚገኘው ቡራዩ ከተማ በደደቢት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቐለ ተጫውቶ ያሳለፈውን ተከላካዩ ዳንኤል አድሀኖም እና በአጥቂ ስፍራ ላይ በደደቢቶ እና መቐለ ቆይታ የነበረውን ክብሮም አፅብሀን አስፈርሟል።

እንጅባራ ከተማ

በአሰልጣኝ አዲሶ ዶይሶ የሚመራው እንጅባራ ከተማ ዳዊት ታደለ አጥቂ ከጂንካ ከተማ ፣ የሽዋስ በለዉ አጥቂ ከከአዲስ ከተማ እና ሐብታሙ ደንጊሶ አማካይ ከጎባ ከተማ በድምሩ ሦስት ተጫዋቾችን የግሉ አድርጓል።

ቂርቆስ ክፍለ ከተማ

የአሰልጣኝ ዘላለም ፀጋዬው ቂርቆስ አምስት ተጫዋቾችን አስፈረመ። የአቡበከር ናስር ታላቅ ወንድም የሆነው አማካዩ ጅብሪል ናስር ፣ የቀድሞው የመቐለ አማካይ አሸናፊ ሀፍቱ ፣ በአማካይ ስፍራ በመቐለ የምናውቀው ፍፁም ተክለማርያምን ጨምሮ ፣ ሀብታሙ ሀይሌ ፣ ቢንያም ትዕዛዙ እና ተመስገን ዘዉዱ የተባሉ ተጫዋቾችን ክለቡ አስፈርሟል።


አጫጭር ዜናዎች

-የከፍተኛ ሊግ የሁለተኛው ዙር የዝውውር መስኮት ቀደም ብሎ ከየካቲት 1 እስከ መጋቢት 1 ድረስ ለአንድ ወራት ያህል እንዲካሄድ ፌድሬሽኑ ይፋ አድርጎ የነበረ ሲሆን ክለቦችም የተቀመጠውን ቀነ ገደብ ተከትለው ዝውውር ሲፈፅሙ ቆይተዋል። ሆኖም አንዳንድ ክለቦች ባቀረቡት የይራዘምልን ጥያቄ መሠረት ዝውውሩ ሦስት ተጨማሪ ቀናት ተከናውኖበት ተጠናቋል።

-የ2015 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር በሦስት ምድቦች ተከፍሎ እየተደረገ አንደኛው ዙር የተጠናቀቀ ሲሆን ሁለተኛው ዙርም ከፊታችን መጋቢት 10 ጀምሮ በአሰላ ፣ ባቱ እና ሀዋሳ ከተሞች እንደሚጀምር የወጣው መርሀግብር ያሳያል። ከተጠቀሱት ከተሞች መካከል ምድብ \’ሀ\’ የሚደረግበት አሰላ ከተማ ከልምምድ ሜዳ እና የሆቴል አቅርቦት በቂ አለመሆን ጋር ተያይዞ የምድቡ ክለቦች ቅሬታ ያሰሙ ሲሆን ፌድሬሽኑም ከሰሞኑ ከክለቦች ጋር ባደረገው ውይይት ይህ ጉዳይ ተነስቶ በአፋጣጭ አማራጭ ከተማ ሊዘጋጅ እንደሚችል ተነግሮ የነበረ ቢሆንም አፋጣኝ ምላሽ አለመሰጠቱን ክለቦች አሳውቀውናል።

-በሦስቱ ምድቦች የሚገኙ ሦስት በመሪነት ያጠናቀቁ ክለቦችን ወደ ትልቁ የሊግ ዕርከን የሚያሳድገው እና በተመሳሳይ ከሦስቱም ምድቦች አስራ አምስት ክለቦች ወደ አንደኛ ሊግ የሚወርዱበት የከፍተኛ ሊግ ውድድር ከዳኝነት ጋር በተያያዘ በርካታ ክለቦች ቅሬታን ለዝግጅት ክፍላችን ሲያቀርቡ ሰንብተዋል። ባሳለፍነው ቅዳሜ ፌድሬሽኑ የክለብ ተወካዮችን ጠርቶ የኳስ አቅርቦት ችግሮች መኖራቸውን ፣ የተባለው የቀጥታ ስርጭት ከአስተላላፊው አካል ጋር በተፈጠረ ችግሮች እንደማይኖር በተነገረበት ውይይት ላይ የዳኝነት ስህተት በመበራከቱ ክለቦች ጥያቄን አንስተው እንደሚሻሻል የተገለፀላቸው ቢሆንም ሁለተኛው ዙር ጠንካራ እና ትኩረት የሚፈልግ በመሆኑ ውድድሩን ከአንደኛው ዙር በተሻለ አወዳዳሪው አካል ትኩረት መስጠት እንዳለበት እና የተሻሉ ዳኞችን ሊመድብ እንደሚገባ ለሶከር ኢትዮጵያ ሀሳባቸውን የገለፁ ክለቦች ጠቁመዋል።

\"\"

-በከፍተኛ ሊጉ የሚገኙ ክለቦች ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ቅሬታቸውን እያሰሙ ይገኛል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ከዓመታት በፊት የሊጉ የተጫዋቾች ወርሀዊ ደመወዝ ሀያ ሺህ ብር ይሁን በማለት ገደብ ማስቀመጥ ቢችልም ክለቦች ከተባለው ክፍያ በላይ እየፈፀሙ መገኘታቸው ለችግሩ በዋናነት የተጠቀሰው ጉዳይ እንደሆነ ቢገለፅም ከተባለው በታች የሚከፍሉ ክለቦችም ይህ ችግር ሲስተዋልባቸው መታየቱ አግራሞትን አጭሯል። ከዚህም ጋር በተያያዘ በፌድሬሽኑ ዕግድ ተላልፎባቸው የነበሩ ክለቦች በተጫዋቾች ዝውውር ላይ ለመሳተፍ ወደ ፌዴሬሽን ደጃፍ ቢያመሩም ፌድሬሽኑ ሳያስተናግዳቸው ቀርቷል። በችግሩም የተነሳ ወደ ሦስት የሚጠጉ ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው ደመወዝ ባለመክፈላቸው እስከ አሁን ልምምድ አልጀመሩም።