የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | የ17ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሣምንት ዛሬ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ሲጀምር ድሬዳዋ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል።

\"\"

ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ 0-0 ቦሌ ክ/ከ

የግብ ዕድሎች ባልተፈጠሩበት የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ  ቦሌዎች ብልጫውን ወስደዋል። ሁሌም በሚታወቁበት አልፎ አልፎ በሚያሳዩት እጅግ ማራኪ የኳስ ቅብብል ከተመልካቾች አድናቆት የማይለያቸው ቦሌዎች በአጋማሹ የተሻሉትን ሁለት የግብ ሙከራዎችም አድርገዋል። በቅድሚያም 33ኛው ደቂቃ ላይ ሜላት አሊሙዝ ከሳጥን ውጪ ያደረገችው ሙከራ በላዩ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ሲወጣባት ወደ ዕረፍት ሊያመሩ የዳኛ ፊሽካ ሲጠበቅ ደግሞ አንበሏ ትርሲት ወንደሰን ከቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ያሻማችው ኳስ በንፋስ ስልኮች ሲመለስ ያገኘችው ምርጥነሽ ዮሐንስ ያደረገችው ሙከራ የግቡን የላይ አግዳሚ ታክኮ ወጥቶባት የግብ ዕድሉን ሳትጠቀምበት ቀርታለች።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በንፋስ ስልኮች በኩል 55ኛው ደቂቃ ላይ በሬዱ በቀለ  በቦሌዎች በኩል 64ኛው ደቂቃ ላይ ንግሥት በቀለ ከቅጣት ምት የሞከሩት እና የግቡን አግዳሚ ታክኮ የወጣባቸው ኳስ ተጠቃሽ ነበር። ሆኖም ጨዋታው ያለግብ ተጠናቋል።

ድሬዳዋ ከተማ 2-1 ይርጋጨፌ ቡና

ከምሳ መልስ በድሬዳዋ ከተማ እና በይርጋጨፌ ቡና በተደረገው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በአጋማሹ የመጀመሪያ እና የመጨረሻ ደቂቃዎችን ድሬዳዋ ከተማዎች ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ይርጋጨፌ ቡናዎች የበላይነት በወሰዱበት የመጀመሪያ አጋማሽ ድሬዎች ገና በ5ተኛው ደቂቃ በሊና መሐመድ ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ቀስ በቀስ ግን ይርጋጨፌዎች በተረጋጋ የማጥቃት እንቅስቃሴ በተለይም በግራ መስመራቸው ተጠናክረው በመቀጠል 20ኛው ደቂቃ ላይ በመስታወት አመሎ ግብ አቻ መሆን ችለዋል። በአምስት ደቂቃዎች ልዩነትም ጨዋታውን መምራት የሚችሉበት ትልቅ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ ፍሬሕይወት ተስፋዬ ከግራ መስመር ከግብጠባቂዋ ከፍ አድርጋ ያደረገችው ሙከራ የግቡን የግራ ቋሚ ታክኮ ወጥቶባታል። ቀስ በቀስ ብልጫ የተወሰደባቸው ድሬዎች 42ኛው ደቂቃ ላይ ግን ጨዋታውን በድጋሚ መምራት ጀምረዋል። ሜላት ደመቀ በግራ መስመር ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ ምሕረት ተሰማ ስትመልስባት ያገኘችው ትዝታ ፈጠነ በቀላሉ አስቆጥራዋለች።

ከዕረፍት መልስ ይርጋጨፌዎች ተሻሽለው በመቅረብ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ አጋማሹን በድሬዳዋ የግብ ክልል ቢያሳልፉም ግብ ለማስቆጠር ግን ተቸግረዋል። በተለይም 61ኛው ደቂቃ ላይ አበራሽ አበበ በተካላካዮች ስህተት ባገኘችው ኳስ ከግብጠባቂ ጋር ብትገናኝም ሳትጠቀምበት ቀርታለች። በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ድሬዳዋ ሳጥን መድረስ ችለው የነበሩት ይርጋጨፌዎች 71ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል በ ስመኝ ተስፋዬ በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ደሞ ሠሚራ ከድር ከረጅም ርቀት ባደረጉት ሙከራም የተሻለ ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ አድርገዋል። በኳስ ቁጥጥሩ ከፍተኛ ብልጫ የተወሰደባቸው ድሬዎች በአጋማሹ 85ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው ወርቅነሽ ሚልሜላ ከረጅም ርቀት ከመታችውና በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ከወጣው ሙከራ ውጪ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ባያደርጉም ጨዋታውን በማረጋጋት እና ውጤቱን አስጠብቀው በመውጣት 2-1 መርታት ችለዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ሀዋሳ ከተማ

የዕለቱ የመጨረሻ መርሐግብር ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሀዋሳ ከተማ አገናኝቷል። ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ባልነበረበት እና በተደጋጋሚ በሚቋረጡ ቅብብሎች በታጀበው የመጀመሪያ አጋማሽ የጊዮርጊሷ አምበል ሶፋኒት ተፈራ 14ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ርቀት ያደረገችው እና ግብጠባቂዋ ፍሬወይኒ ገብሩ የያዘችው ኳስ በአጋማሹ የተሻለው ሙከራ ነበር።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተሻለ ግለት ሲቀጥል እንስት ፈረሰኞች በዕለቱ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ እና በድንቅ ቦታ አያያዝ ኮከብ በነበረችው አምበላቸው ሶፋኒት ተፈራ በሚመራው የአማካይ መስመራቸው ላይ ብልጫውን መውሰድ ሲችሉ 60ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳዋ እሙሽ ዳንኤል በሁለት ቢጫ ከሜዳ መወገዷ ደግሞ የነበረባቸውን ጫና እጅግ ቀንሶላቸዋል።

ከዕረፍት መልስ ሲሣይ ገብረዋህድን ቀይረው በማስገባት በተረጋጋ የኳስ ቅብብል የማጥቃት ኃይላቸውን ማጠናከር ጀምረው የነበሩት ኃይቆቹ የተጫዋች ቁጥር ብልጫ ከተወሰደባቸው በኋላ ግን በጨዋታው እጅግ ተፈትነዋል። ጊዮርጊሶች በወሰዱት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመታገዝም 70ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። ሶፋኒት ተፈራ ከቀኝ መስመር ያሻገረችን ኳስ ከጥቂት ንክኪዎች በኋላ ያገኘችው በዕለቱ ከሶፋኒት በመቀጠል የተሳካ ቀን ያሳለፈችው አይናለም ዓለማየሁ መረቡ ላይ አሳርፋዋለች። ከግቧ መቆጠር በኋላም ጠንካራ ፉክክር አስመልክቶን ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"