መረጃዎች | 69ኛ የጨዋታ ቀን

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ነገ የሚያስተናግዳቸውን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እነሆ።

ፋሲል ከነማ ከ ወላይታ ድቻ

የምሽቱ መርሃግብር በአንድ ነጥብ ልዩነት 9ኛ እና 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማን ያገናኛል።

ከሰንጠረዡ ወገብ በታች ላይ በ21 ነጥቦች የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ በአዳማ ከተማ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠሩባቸው ሁለት ግቦች በሽንፈት ለመጀመር የተገደዱ ሲሆን በነገው የወላይታ ድቻ ጨዋታ ግን ወደ ድል ለመመለስ ጠንክረው እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

ከጨዋታ ጨዋታ ወጥ የሆነ የሜዳ ላይ ብቃትን ለማሳየት እየተቸገሩ የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች በሊጉ የተሻለ ስፍራን ይዘው ለመፈፀም በየጨዋታው ወጥ የሆነ ብቃትን ወደ ማሳየት መምጣት ይኖርባቸዋል።

ፋሲሎች በነገው ጨዋታ ላይ ከአዳማ ጋር ሲጫወቱ በቀይ ካርድ የተሰናበተውን ሱራፌል ዳኛቸውን የማያገኙ ሲሆን የከፍተኛ አስቆጣሪያቸው ፍቃዱ ዓለሙ ከጉዳት ቢያገግምም ለነገው ጨዋታ የማይደርስ ሲሆን ተከላካዩ መናፍ ዐወል ግን ከቅጣት የሚመለስ ይሆናል።

\"\"

ከተጋጣሚያቸው ፋሲል ከነማ በአንድ ነጥብ እና ደረጃ ከፍ ብለው የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች ሁለተኛውን ዙር ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለ ግብ ነጥብ በመጋራት ነበር የጀመሩት።

በሊጉ ከለገጣፎ ለገዳዲ ቀጥሎ 12 ግቦችን ብቻ በማስቆጠር 2ኛው ደካማ የማጥቃት መስመር ባለቤት የሆነው ቡድኑ በመጨረሻ ባደረጓቸው ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ምንም ዓይነት ግብ ማስቆጠር ያልቻሉ ሲሆን ዕድሎችን በመፍጠር ረገድም ያለባቸው ውስንነት እጅግ አሳሳቢ ነው ለአብነትም በመጨረሻው የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በሙሉ ዘጠና ደቂቃ ያደረጉት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ መጠን አንድ ብቻ መሆኑ በጣም አስገራሚ ነው።

ወላይታ ድቻዎች አንጋፋው ተከላካይ ደጉ ደበበ ከጉዳት ሲመለስላቸው አንተነህ ጉግሳ እና በኃይሉ ተሻገር ግን አሁንም ጉዳት ላይ ይገኛሉ።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ ዙር በተገናኙበት ጨዋታ ወላይታ ድቻ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ማሸነፍ የቻለ ሲሆን በድምሩ በሊጉ ካደረጓቸው አስራ አንድ ግንኙነቶች ፋሲል ከነማዎች ስድስት እንዲሁም ወላይታ ድቻዎች ደግሞ አራት ጊዜ በድል መወጣት ሲችሉ ቀሪዋ አንድ ጨዋታ ደግሞ ነጥብ በመጋራት የተፈፀመ ነበር።

ቢኒያም ወርቅገኘሁ በመሀል ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ለመጀመሪያ ጊዜ ከከፍተኛ ሊጉ ያደገው ሰብስቤ ጥላሁን በረዳትነት ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ በአራተኛ ዳኝነት ለዚህ ጨዋታ ተመድበዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በ 35 ነጥቦች የሊጉ አናት ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶችን በ 8 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የሚያገናኘው የምሽቱ ፍልሚያ ፈረሰኞች መሪነታቸውን ለማጠናከር ኤሌክትሪኮች ደግሞ ካሉበት የወራጅ ቀጠና ለማንሠራራት ጥሩ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በ16ኛው ሣምንት ተከታያቸው ኢትዮጵያ መድንን ከመመራት ተነስተው ድል ያደረጉት ፈረሰኞቹ ከፍተኛ ፉክክር ይገጥማቸዋል ተብሎ በተጠበቀው ጨዋታ ያሳኩት ጣፋጭ ድል ለቀጣይም ትልቅ መነሳሳት እንደሚፈጠርላቸው ይገመታል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሊጉ ላይ ዝቅተኛውን ግብ(10) ማስተናገዳቸው እንደ ጥሩ ጎን ቢታይም አልፎ አልፎ የራሳቸው የሜዳ ክፍል ላይ በውሳኔ እና በጊዜ አጠባበቅ ስህተት የሚታይባቸውን ድክመት በጊዜ ሊቀርፉት አደጋ ላይ ሊጥላቸው ይችላል።

በሜዳ ላይ ከሚያሳዩት ጠንካራ እንቅስቃሴ አንጻር የድል ፅዋን ለመጎንጨት የተራራ ያህል የከበዳቸው ኤሌክትሪኮች በተለይም በመጨረሻ ጨዋታቸው ባህርዳር ከተማን ሲመሩ ቆይተው ወሳኝ ተጫዋቻቸውን አብነት ደምሴን በሁለት ቢጫ ካጡ በኋላ የተፈጠረባቸውን የተጫዋች ቁጥር ብልጫ መቆጣጠር ባለመቻላቸው ለሽንፈት ተዳርገዋል። የቡድኑ ሚዛን ጠባቂ አብነት ደምሴ በቅጣት ምክንያት ነገም አለመሰለፉ ደግሞ ትልቅ ፈተና እንደሚሆንባቸው ሲጠበቅ ከለገጣፎ ለገዳዲ (38) እና ሲዳማ ቡና (29) ቀጥሎ ሦስተኛው ከፍተኛ የግብ መጠን(26) ያስተናገዱ በመሆናቸው በኢስማኤል ኦሮ-አጎሮ የሚመራውን የፈረሰኞቹን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመመከት የተለየ የጨዋታ ስልት ይዘው ወደሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በነገው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አማኑኤል ገብረሚካኤል በጉዳት የማይኖር ሲሆን ኤሌክትሪኮች ደግሞ ከላይ እንደተጠቀሰው አብነት ደምሴን በሁለት ቢጫ ካርድ አብዱርሀማን ሙባረክን ደግሞ በጉዳት የሚያጡ ይሆናል።

በመጀመሪያው ዙር በተገናኙበት ጨዋታ ጊዮርጊሶች በፍሪምፖንግ ሜንሱ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ማሸነፋቸው የሚታወስ ሲሆን በአጠቃላይም ሁለቱ ቡድኖች 39 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 27 በማሸነፍ  የበላይነትን ሲይዝ ኤሌክትሪክ 3 አሸንፎ በ9 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 66 ግቦች ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ በበኩሉ 28 አስቆጥሯል።

ለነገ ምሽቱ ጨዋታ ባህሩ ተካ በዋና ዳኝነት ለጨዋታው መመደብ ሲችል ፣ አንጋፋው ረዳት ዳኛ ካሳሁን ፍፁም እና ለዓለም ዋሲሁን ረዳቶች ፣ ዳንኤል ግርማይ አራተኛ ዳኛ ሆነው ለጨዋታው ተመርጠዋል።

\"\"