ሪፖርት| ለገጣፎ እና ኤሌክትሪክን ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተገባዷል

ሁለት ላለመውረድ እየተፋለሙ የሚገኙትን ክለቦች ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ለገጣፎ ለገዳዲ ባለፈው ሳምንት ከተሸነፈው ስብስብ ያሬድ ሃሰን እና ሱራፌል ዐወልን በመዝገቡ ቶላ እና አስናቀ ተስፋዬ ለውጠው ገብተዋል። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው ባለፈው ሳምንት አቻ ከተለያየው ስብስብ ጌቱ ኃይለማርያም ፣ አብዱልራህማን ሙባረክ ፣ አብነት ደምሴ እና ማታይ ሉይን በታፈሰ ሰርካ ፣ ተስፋዬ በቀለ ፣ ጎሜዝ ፓውል እና ልደቱ ለማ ተክተው ገብተዋል።

\"\"

ሁለቱም ላለመውረድ የሚጫወቱ ክለቦች ያገናኘው ይህ ጨዋታ ደካማ የማጥቃት አጨዋወቶች እና እጅግ ጥቂት የጠሩ ሙከራዎች የታየበት ነበር። ሁለት ተመሳሳይ በረዣዥም ኳሶች የግብ ዕድል ለመፍጠር የሚጥሩ ቡድኖች የታየበት ጨዋታው ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። በሙከራ ረገድ በአንፃራዊነት የተሻሉ የነበሩት ለገጣፎዎች አማኑኤል በሁለት አጋጣሚዎች ከርቀት ያደረጋቸው ሙከራዎች እና አስናቀ ከቅጣት ምት ባደረገው ሙከራ ዕድሎች መፍጠር ችለው ነበር።


በጨዋታው በተደጋጋሚ ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ዕድሎች ያባከኑት ኤሌክትሪኮችም በአዲሱ ሴኔጋላዊ አጥቂ ጎሜዝ ፓውል እና ስንታየሁ ወለጬ አማካኝነት ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በተለይም ስንታየሁ ወለጬ ያደረጋት ሙከራ ለግብ የቀረበች ነበረች። በዮናስ እና ናትናኤል ያገኟቸውን ኳሶችም በተጫዋቾቹ ደካማ ውሳኔ ምክንያት ወርቃማ ዕድሎች ባክነዋል።


መሐመድ አበራ በግንባር ባደረገው ሙከራ የጀመርያው አጋማሽ ጥቃታቸው የጀመሩት በአጋማሹ የተሻሉ የነበሩት ለገጣፎዎች በአማኑኤል እና ሱራፌል ጥሩ መናበብ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ኳስ እና መረብ ማገናኘት አልቻሉም። ቡድኑ በመጨረሻው ደቂቃ በአማኑኤል አማካኝነት ከርቀት ያደረገው ሙከራም ሌላ ግሩም ሙከራ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ደካማ እንቅስቃሴ ያደረጉት ኤላክትሪኮች አላዛር ካደረገው ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል የጠራ ሙከራ ሳይፈጥሩ ነበር ሁለተኛውን አጋማሽ ያገባደዱት።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ በተሰጠ የአሰልጣኞች አስተያየት የለገጣፎ ለገዳዲ አሰልጣኝ ዘማርያስ ወ\\ጊዮርጊስ \”ጨዋታው ጥሩ ነበር። የኳስ ቁጥጥራችን ውጤታማ አልነበረም ፤ በማጥቃቱ በኩል በተለይ ስል አልነበርንም። የአቻ ውጤቱ ፍትሀዊ ነው።\” ሲሉ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ምክትል አሠልጣኝ ስምዖን አባይ በበኩላቸው \”ጉጉት እና የትኩረት ማጣት ችግሮች ነበሩብን። ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገናል።በትኩረት ማጣት ያልተጠቀምንባቸው ዕድሎች ነበሩ ፤ ግብ ለማስቆጠር ያደረግነው ጥረትም አልተሳካም \” ካሉ በኋላ ስለ ቀጣይ እርምጃቸው ተጠይቀው \”መጨናነቅ እና ጫና አለ ፤ ጫናውን ለመቋቋም የቻልነውን እናደርጋለን\” ብለዋል።