መረጃዎች | 81ኛ የጨዋታ ቀን

ነገ በሊጉ 20ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን በሚደረጉት ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን መረጃዎች አሰናድተናል።

ኢትዮጵያ መድን ከ መቻል

የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር የሚደረግበት እንደሚሆን ይጠበቃል። ባሳለፍነው ሳምንት ሦስት ነጥብ ማሳካት ያልቻሉት መድን እና መቻል አንደኛው ከዋንጫ ፉክክሩ ላለመራቅ ሌላኛው ከተከታታይ ሽንፈት ለመዳን ውጤቱን አጥብቀው ይፈልጉታል።

ኢትዮጵያ መድን ከለገጣፎው የጎል ፌሽታ መልስ ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ለመጋራት ተገዷል። ይህ መሆኑ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ በጥቂቱ ሸርተት እንዲል እና ከመሪው ጋር ያለው ልዩነት ወደ አምስት እንዲሰፋ ያደረግው ሲሆን ተጨማሪ ነጥቦችን መጣል አይኖርበትም። በድቻው ጨዋታ ከውጤት ባለፈ ቡድኑ መሀል ሜዳ ላይ በእጅጉ ተቸግሯል። ጠንካራ ጎኑ የሆነው የአማካይ ክፍሉ እንቅስቃሴ በተጋጣሚው ነፃነት ያጣ በመሆኑ አጠቃላይ የማጥቃት ሂደቱ ተፈትኗል። በእርግጥ በሁለተኛው አጋማሽ የተደረጉ ማስተካከያዎች አነቃቅተውት ቢታዩም ሙሉ ውጤት ለማሳከት በቂ አልነበረም። ከዚህ አንፃር የነገው ፍልሚያ መድኖች 39 ግቦችን ሲያስቆጥሩ ዋና ጥንካሪያቸው የነበረው የመሀል ሜዳ ብልጫ እና ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎች የመፍጠር አቅማቸውን መልሰው ለማግኘት የሚያደርጉት ጨዋታ እንደሚሆን ይገመታል።
\"\"
በተፈላጊው ደረጃ ተዋህዷል ባይባልም ከተጋጣሚው የማይተናነስ የአማካይ ክፍል ስብስብን የያዘው መቻል በተመሳሳይ ሁኔታ በፋሲሉ ጨዋታ ቀላል ጊዜ አልገጠመውም። ተጋጣሚው የኳስ መቀባበያ ክፍተቶችን በቶሎ በመዝጋት ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል መግባት ቀላል እንዳይሆንለት አድርጎታል። በተመሳሳይ በመስመሮች በኩል ዕድሎችን ለመፍጠር ያደረገው ጥረትም ሳይሳካ በጠባብ ውጤት ለመሸነፍ ተገዷል። በአንፃራዊነት ክፍት ሊሆን እንደሚችል በሚገመተው በነገው ጨዋታ ግን ቡድኑ ከወገብ በላይ የተሻለ አፈፃፀም ሊኖረው እንደሚችል ይታሰባል። ከፋሲል ቀደም ብሎ በአርባምንጭ ከተማ እና አዳማ ከተማ ተከታታይ ሽንፈቶችን ያስተናገዱት መቻሎች የነገው ጨዋታ ፈፅሞ ነጥብ የሚያጡበት እንዳይሆን ያላቸውን እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

በጨዋታው መቻል ፍፁም ዓለሙን እና ዳግም ተፈራን በጉዳት ምክንያት ሲያጣ ሰሞኑን ቡድናቸውን በህመም ምክንያት እየመሩ ያልነበሩት የመድኑ ዋና አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ወደ ሜዳ እንደሚመለሱ ይጠበቃል።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ ዙር ያደረጉትን ጨዋታ ኢትዮጵያ ሙድን 2-1 ማሸነፍ ችሎ ነበር።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በዋና ዳኝነት ፣ ዳንኤል ጥበቡ እና መሐመድ ሁሴን በረዳትነት ፣ አዳነ ወርቁ በበኩሉ አራተኛ ዳኝነት ለዚህ ጨዋታ ተመድበዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ወላይታ ድቻ

ምሽት 12:00 ላይ በሚከናወነው ጨዋታ ተከታታይ ድሎችን ማስመዝገብን የሚያለመው ሀዲያ ሆሳዕና ወደ ድል ለመመለስ ከሚጫወተው ወላይታ ድቻ ይገናኛሉ።

ነብሮቹ ባለፉት ጨዋታዎች ከግብ ጋር የታረቁ ይመስላል አምስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ያለግብ ተጉዘው የነበረበትን ጊዜ በሚያስረሳ መልኩ በመጨረሻ ጨዋታዎቻቸው በተከታታይ ግብ አስቆጥረዋል። ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱን ብቻ በድል የመጨረሻቸው ነገር ግን አሁንም በማስቆጠሩ ረገድ ይበልጥ እንዲሻሻሉ የሚያሳስብ ነው። በነገውም ጨዋታ ቡድኑ በተለይም በቀኙ ወገን በሚሰነዝራቸው ፈጣን ጥቃቶች የግብ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ሲጠበቅ በወቅታዊ አቋም ረገድ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው አማካዩ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀንን በቅጣት ማጣቱ የሚጎዳው ቢሆንም የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ የተሻለ አፈፃፀም ይጠበቅባቸዋል።
\"\"
ወላይታ ድቻ በቅርብ ጨዋታዎች ከብርቱ መከላከል ባለፈ ከመሀል ሜዳ በሚጀምር ጫና ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ለመሰንዘር የሚያስችል ብቃትም እንዳለው እያሳየ ይገኛል። እንደ አበባየሁ አጂሶ ያሉ አማካዮችን የያዘው ድቻ ለተጋጣሚዎቹ ግምት ውጪ በፈጣን ቅብብሎች የተመሰረተ ጥቃት ሲፈፅም የሚታይ ሲሆን ይህ በጥሩ የመጨረስ ብቃት ቢታገዝ ቡድኑ የተሻለ ውጤት ሊያስመዘግብ እንደሚችል የሚገመት ነው። ከዚህ የቡድኑ ባህሪ እና ከሀዲያ ሆሳዕና የማጥቃት እሳቤ አንፃርም ጨዋታው ጥሩ ምልልስ የሚታይበት ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ይቻላል።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ በሰባት አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን ዕኩል ሦስት ጊዜ ድል ቀንቷቸው ቀሪውን አንድ ጨዋታ በአቻ ውጤት ደምድመዋል።

ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በመሐል ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና ታምሩ አደም በረዳትነት ፣ ዮናስ ካሳሁን በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።