ሪፖርት| አዳማ ከተማ ወደ ድል ተመልሷል

አዳማ ከተማዎች በሁለቱ የመስመር ተከላካዮቻቸው ግቦች ኢትዮ ኤሌክትሪክን ሁለት ለባዶ በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።

አዳማ ከተማዎች ባለፈው ሳምንት ከፈረሰኞቹ ጋር ከተጠቀሙበት ቋሚ ስብስብ አድናን ረሻድ ፣ አዲስ ተስፋዬ እና አሜ መሐመድን በቢንያም አይተን ፣ ደስታ ዮሐንስ እና ኤልያስ ለገሰ ተክተው ገብተዋል። ኤሌክትሪኮችም ከባለፈው ሳምንት ቋሚ አሰላለፍ ስንታየሁ ዋለጬ ፣ ናትናኤል ሰለሞን ፣ ዮናስ ሰለሞን እና ልደቱ ለማን በአብነት ደምሴ ፣ አብዱራህማን ሙባረክ ፣ ፀጋ ደርቤ እና ፍፁም ገብረማርያም ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

\"\"

ጀሚል በተሰለፈበት የቀኝ መስመር ላይ የተመሰረተ የማጥቃት አጨዋወት የነበራቸው አዳማዎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው የጠሩ ዕድሎችም ፈጥረዋል። ጀሚል ወደ ሳጥን አሻግሮት ኤልያስ ለገሰ በግሩም ሁኔታ የሞከረው ኳስም ተጠቃሽ ነው። ቦና ዓሊ ከሳጥኑ ጠርዝ ገባ ብሎ ያደረገው ሙከራም ሌላ የሚጠቀስ የግብ ዕድል ነው። በሀያ አራተኛው ደቂቃም በዮሴፍ አማካኝነት መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ሆኖም አጥቂው አክርሮ የመታው ኳስ ቋሚውን ለትሞ ሲመለስ በድጋሜ የተመለሰውን ኳስ በግንባሩ ሙክሮ የኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ እንደምንም አውጥቶታል።


በጨዋታው ደካማ የማጥቃት አጨዋወት የነበራቸው ኤሌክትሪኮችም በፀጋ ደርቤ እና ተቀይሮ በገባው ተካልኝ ያደረጓቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። በተለይም ፍፁም አመቻችቶት ተካልኝ የሞከረው ሙከራ እጅግ ለግብ የቀረበ ነበር።


እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ አዳማዎች ብልጫ በወሰዱበት ሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ጥቂት ሙከራዎች ነበር ያስመለከተን። በአዳማዎች በኩል መስዑድ መሐመድ ከሳጥኑ ጠርዝ መቶ ያደረገው ሙከራ ቀዳሚ ነበር። በሰባ አንደኛ ደቂቃም የግራ መስመር ተከላካዩ ደስታ ዩሀንስ ግብ አስቆጥሮ አዳማን መሪ ማድረግ ችሏል። ተከላካዩ ከተቃራኒ አቅጣጫ የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ግብ በማስቆጠር ነበር ቡድኑን መሪ ማድረግ የቻለው።


ከግቧ መቆጠር አምስት ደቂቃዎች በኋላም አዳማዎች በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ባደረገው ጀሚል አማካኝነት ግብ አስቆጥረው መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል። ተከላካዩ ተቀይሮ የገባው ነቢል ያመቻቸለት ኳስ ነው አክርሮ በመምታት ያስቆጠረው። ዮሴፍ ታረቀኝ በጨዋታው መገባደጃ ያደረገው ለግብ የቀረበ ሙከራም የቡድኑ ሦስተኛ ግብ ለመሆን ተቃርቦ ነበር። ኤሌክትሪኮች በአጋማሹ ይህ ነው የሚባል አደገኛ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ተጠኗቋል።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የአዳማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ \”ጨዋታው ከባድ ነበር። በአጨዋወታችን ከቀጠልን ግብ እንደምናስቆጥር የታወቀ ነበር። የደስታ ጎል ትልቅ መነሳሳት ፈጥሮብናል ፤ ትልቅ ተጫዋችም ነው። በአዳማ ከተማ የቀሩትን ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ ወሳኝ ነው\” ሲሉ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ምክትል አሰልጣኝ ስምዖን አባይ በበኩላቸው \”ቅያሬዎች እንደፈለግነው አልሄደም። የቀየርናቸው ተጫዋቾች ውጤታማ ነበሩ ለማለት አይቻልም። ጭንቀቶች አሉ ፤ እግር ኳስ እስከሆነ ድረስ ነገሮች ለማስተካከል እንሄዳለን\” ብለዋል።