መረጃዎች | 82ኛ የጨዋታ ቀን

በ20ኛ ሳምንት ሦስተኛ ቀን የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

አዳማ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

09፡00 ሲል በ14 ነጥቦች እና በ 5 ደረጃዎች ተበላልጠው 10ኛ እና 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን አዳማ እና ኤሌክትሪክ የሚያገናኘው ጨዋታ ሲደረግ አዳማዎች ከገጠማቸው ተከታታይ ሁለት ሽንፈት ለማገገም ኤሌክትሪኮች ካሉበት የወራጅ ቀጠና ለማንሠራራት ብርቱ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የመቀመጫ ከተማቸውን ቆይታ መቻልን በመርታት የጀመሩት አዳማ ከተማዎች ባለፉት ሁለት የጨዋታ ሳምንታት ግን በሀዋሳ ከተማ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ተሸንፈዋል። ሆኖም ቡድኑ ሜዳ ውስጥ የሚያሳየው እንቅስቃሴ እና ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች በአምስቱ የተጋጣሚን መረብ መድፈር መቻሉ የአሰልጣኝ ይታገሡ እንዳለን ተስፋ ያለመለመ ነው። በተቃራኒው ቡድኑ  ባደረጋቸው ሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች በሙሉ ግብ ማስተናገዱ ግን የኋላ መስመሩ በጥልቅ መፈተሽ እንዳለበት ይጠቁማል። ነገም ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ነጥቦችን የመሰብሰብ ግዴታ ውስጥ ካሉት ኤሌክትሪኮች የሚገጥማቸው ፈተና ቀላል አይሆንም።

\"\"

በአራተኛው የጨዋታ ሳምንት ለገጣፎ ለገዳዲ ላይ ከተቀዳጁት ድል ውጪ ሦስት ነጥብ ለማሳካት እጅግ የተቸገሩት ኤሌክትሪኮች ከወራጅ ቀጠናው ከፍ ብሎ ካለው ቡድን በ11 ነጥቦች ርቀው መቀመጣቸው ወደ ፊት የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ እንዲገቡ አስገድዷቸዋል። ከተከታታይ አራት ሽንፈቶች በኋላ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች የአቻ ውጤት በማስመዝገብ በጥቂቱ ለማገገም ዕድል ያገኘው ቡድኑ ሜዳ ውስጥ የሚያሳየውን እንቅስቃሴ ወደ ውጤት ለመቀየር መሥራት ይጠበቅበታል። በነገው ዕለትም በመቀመጫ ከተማው እየተወዳደረ ከሚገኘው አዳማ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር እንደሚገጥመው ይታመናል።

የአዳማ ከተማን የቡድን ዜና ማግኘት ባንችልም በኤሌክትሪክ በኩል አብነት ደምሴ ከአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት እንደሚመለስ ሲጠበቅ ከጌቱ ኃይለማሪያም ውጪ የቡድኑ ቀሪ ስብስብ ለጨዋታው ዝግጁ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ነገ ለ37 ጊዜ ይገናኛሉ። እስካሁን 50 ግቦች ያስቆጠረው አዳማ ከተማ 19 ድሎችን ሲያሳካ አስር ጊዜ መርታት የቻለው ኤሌክትሪክ ደግሞ 44 ጎሎች አሉት።

ጨዋታውን ተካልኝ ለማ በዋና ዳኝነት አሸብር ታፈሰ እና አስቻለው ወርቁ በረዳትነት ሀብታሙ መንግሥቴ በበኩላቸው በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

ሲዳማ ቡና ከ ወልቂጤ ከተማ

በምሽቱ መርሐግብር ዕኩል 21 ነጥብ በመያዝ በግብ ልዩነት ተበላልጠው 14ኛ እና 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን ሲዳማን እና ወልቂጤን የሚያገናኘው ጨዋታ ሁለቱም ሜዳ ውስጥ ከሚያሳዩት እንቅስቃሴ አንፃር ከናፈቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ ብርቱ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ካደረጓቸው የመጨረሻ አራት ጨዋታዎች ሁለቱን አቻ በመውጣት ሁለቱን የተሸነፉት ሲዳማዎች ወጥ የሆነ ብቃት ለማሳየት እየተቸገሩ ይገኛሉ። በእነዚህ ጨዋታዎች ላይ አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው ቡድኑ ከሚታወቅበት አስፈሪ የማጥቃት እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ እየወጣ ለመሆኑ ምስክር ነው። ሲዳማ ቡና የቡድኑን ሁነኛ አጥቂ ይገዙ ቦጋለን በጉዳት ባለመጠቀሙ ያጣውን የተጋጣሚ ሳጥን ቁልፍ ተጫዋቹ ነገም የማይሰለፍ ከሆነ በሌሎች አማራጮች ይጠቀም ዘንድ ያገደዳል። በነገው ዕለትም በተመሳሳይ ነጥብ የመውረድ አደጋ ካንዣበበባቸው ወልቂጤ ከተማዎች ለሚገጥማቸው ፈተና በደንብ መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።

ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ነጥብ በመጋራት በአራቱ የተሸነፉት ሠራተኞቹ ሜዳ ላይ ከሚያሳዩት ጠንካራ እንቅስቃሴ አንጻር ድል እንዳይቀዳጁ በእነዚህ ጨዋታዎች 13 ግብ ያስተናገደው የተከላካይ መስመራቸው ድክመት እንደ ምክንያት ይቆጠራል። ሆኖም ይህንን ክፍል ካስተካከሉ በአጥቂያቸው ጌታነህ ከበደ በሚመራው የአጥቂ ክፍላቸው በመታገዝ ወደ ውጤት ለመምጣት ብዙም የሚቸገሩ አይመስሉም። በነገው ዕለትም ከራቃቸው ውጤት ጋር ለመታረቅ ብርቱ ፈተና ይጠብቃቸዋል።

\"\"

በሲዳማ ቡና በኩል አጥቂው ይገዙ ቦጋለ በጉዳት በነገው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር ነገ በመጨረሻ የህክምና ውጤቱ ላይ ተንተርሶ የሚወሰን ሲሆን ወልቂጤ ከተማ ብዙአየሁ ሰይፈን በቅጣት አፈወርቅ ኃይሉን እና አንዋር ዱላን ደግሞ በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አያገኝም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለአምስት ጊዜያት ተገናኝተው ሲዳማ ቡናዎች አራቱን ጨዋታ በተመሳሳይ 1-0 ሲያሸንፉ አንዱ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

የምሽቱን መርሐግብር ለመምራት ኤፍሬም ደበሌ በመሐል ዳኝነት ዳንኤል ጥበቡ እና ሶርሳ ዱጉማ በረዳትነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።