ጎፈሬ እና ዳሽን ባንክ ለአምስት የታዳጊ ፕሮጀክቶች የትጥቅ ድጋፍ አድርገዋል

ሀገር በቀሉ የስፖርት ትጥቅ ብራንድ ጎፈሬ እና አንጋፋው ዳሽን ባንክ በመዲናችን አዲስ አበባ ለሚገኙ 5 የእግርኳስ ፕሮጀክቶች 700 ሺ ብር የሚያወጣ የትጥቅ ድጋፍ አድርገዋል።

\"\"

ኢትዮጵያዊው የስፖርት ትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ ከፋይናንስ አጋሩ ዳሽን ባንክ ጋር በመሆን የእግርኳስ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ የተለያዩ ስራዎችን እየከወነ እንደሚገኝ ይታወቃል። ሁለቱ ተቋማት አብረው ከሚሰሯቸው ስራዎች መካከል ደግሞ የታዳጊ እግርኳስ ፕሮጀክቶችን የመደገፍ ስራ አንዱ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በአዲስ አበባ ለሚገኙ አምስት ፕሮጀክቶች በአይነቱ ልዩ የሆነ የሙሉ ትጥቅ አቅርቦት ድጋፍ አድርገዋል።


አዲሱ ገበያ አካባቢ በሚገኘው የጎፈሬ ዋና ሾ-ሩም በተከናወነው ሥነ-ስርዓት ላይ የጎፈሬ እና ዳሽን ባንክ የበላይ አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው ታላላቅ እንግዶች፣ የብዙሃን መገናኛ አባላት እና የፕሮጀክቶቹ ተወካዮች እንዲሁም በፕሮጀክቶቹ የታቀፉ ታዳጊዎች ተገኝተዋል። የትጥቅ ርክክቡ ከመከናወኑ በፊት የጎፈሬ መስራች እና ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን እንዲሁም የዳሽን ባንክን የማርኬቲንግ ዲቪዥን ሀላፊ አቶ አደራው ጥላሁን ስነድጋፉ መጠነኛ ገለፃ አድርገዋል።

መድረኩን ቀድመው የተረከቡት አቶ አደራው \”እግርኳሱን ለመደገፍ ከአጋራችን ጎፈሬ የትጥቅ አምራች ተቋም ጋር በጋራ በመሆን በመዲናችን የሚገኙ አምስት ፕሮጀክቶችን በመምረጥ ፕሮጀክቶቹ የሚደገፉበትን መንገድ ቀይሰን ይህንን ድጋፍ አድርገናል። እንደሚታወቀው ዳሽን ባንክ በብዙ አማራጮች ማኅበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ የሚገኝ ትልቅ ባንክ ነው። ይሄም የትጥቅ ድጋፍ ከበርካቶቹ የማኅበራዊ ሀላፊነቶቻችን አንዱ ነው። ከፕሮጀክቱም ባለፈ በፕሪምየር ሊጉ ከሚሳተፉት ክለቦች ጋር ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን።\” ብለዋል።


አቶ ሳሙኤል በበኩላቸው በስፍራው የተገኙ እንግዶችን እና የብዙሃን መገናኛ አባላትን እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ የዛሬው መርሐ-ግብር ከዚህ በፊት ካከናወኗቸው በርካታ ስራዎች በአይነቱ ልዩ እንደሆነ ተናግረዋል።\”ይህንን ተግባር ለየት የሚያደርገው ድጋፉ ለታዳጊዎች መሆኑ፣ ተግባሩ በሁለት ተቋማት በጥምረት ተከናውኖ መሬት መውረዱ እና የፋይናንስ ሴክተሩን ወደ እግርኳስ እንዲመጣ ማድረጉ ነው። ይህ ተግባር እየሰራን ከምንገኘው ስራ በጣም ትንሹ ነው። ከዚህም በኋላ በዚሁ መልኩ መጠነ ሰፊ ስራዎችን እንሰራለን።\” ያሉ ሲሆን ተግባሩ እንደ ድጋፍ ሳይቆጠር ግዴታቸውን እንደተወጡ ተደርጎ እንዲታሰብ አስረድተዋል።

የትጥቅ ድጋፉ ራዕይ፣ አንድነት፣ ኮልፌ ተስፋ፣ አንድሮ ሜዳ እና 4-3-3 ለተባሉ ፕሮጀክቶች የተደረገ ሲሆን በአጠቃላይ ወደ 700,000 የሚጠጋ ብር የሚፈጁ ሙሉ ትጥቆች በድጋፍ መልክ በነፃ ተሰጥቷል። ፕሮጀክቶቹ ከ12 ዓመት በታች ጀምሮ እስከ 20 ዓመት በታች ድረስ ታዳጊዎችን የያዙ ሲሆን በድጋፉም በአጠቃላይ ከ700 በላይ ሰልጣኞች፣ አሠልጣኞች እና አመራሮች ትጥቆችን የሚያገኙ ይሆናል።


ከገለፃው በኋላ የትጥቅ ርክክብ የተከናወነ ሲሆን የፕሮጀክቶቹ ተወካዮች እና ሰልጣኝ ታዳጊዎች ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አድርሰው ይህ ድጋፍ ለቀጣይ ትልቅ ስንቅ እንደሚሆናቸው ተናግረዋል። በመጨረሻም የፎቶ የመነሳት ስነ-ስርዓት ተከናውኖ መርሐ-ግብሩ ተጠናቋል።

\"\"