ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ20ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ20ኛ የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች በአንፃራዊነት ደምቀው የወጡ ተጫዋቾችን በምርጥ ቡድናችን አካተናል።

አሰላለፍ 4-4-2 ዳይመንድ

ግብ ጠባቂ

ፍሬው ጌታሁን – ድሬዳዋ ከተማ

ድሬዳዋ ከተማ ከሀዋሳ ላይ ሦስት ነጥብ ሲሸምት የግብ ጠባቂው ሚና የላቀ ነበር። በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ሀዋሳዎች በዓሊ ሱለይማን ሁለት አጋጣሚዎችን ፈጥረው ወደ ጎልነት እንዳይለወጡ ከማድረጉ በዘለለ መረቡን ሳያስደፈር በመውጣቱ ከውብሸት ጭላሎ ጋር ተወዳድሮ በምርጥነት ሊካተት ችሏል።

\"\"

ተከላካዮች

ጀሚል ያዕቆብ – አዳማ ከተማ

በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኘው ይህ የቀኝ መስመር ተከላካይ የአዳማ ከተማዎች ዋነኛ የማጥቃያ መሳርያ በመሆን ድንቅ ሳምንት አሳልፏል። አዳማ ኤሌክትሪክን ሲረታ አንድ ግብ አስቆጥሮ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠሩ በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።

እያሱ ለገሠ – ድሬዳዋ ከተማ

ለወትሮ መረጋጋት የማይታይበት የብርቱካናማዎቹ የኋላ መስመር ከሲዳማ ቡናው የፎርፌ ውጤት ውጪ ባሳለፍነው ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ ግቡን ሳያስደፍር ወጥቷል። በዚህ ሂደት ደግሞ የእያሱ ሚና ቀላል አልነበረም። ፈጣኖቹን የሀዋሳ አጥቂዎች ከአጋሩ መሳይ ጳውሎስ ጋር በሚገባ ሲቆጣጠሩ ባሳየው መልካም እንቅስቃሴ በምርጥ ቡድናችን ውስጥ ተካቷል።

ፈቱዲን ጀማል – ባህር ዳር ከተማ

ባህር ዳር ከተማ ለገጣፎን ሲረታ የመሐል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ በተጋጣሚያቸው የማጥቃት መነሻን በሚፈጥሩበት ወቅት በቀላሉ ወደ ሦስተኛ የሜዳው ክፍል እንዳይገቡ ፈቱዲን ወደ ፊት ሳብ በማለት ጭምር ሲያደርገው በነበረው የመከላከል አስተዋፅኦ እና ኳስን ሲያገኝ ወደ አጥቂ ክፍሉ በማሻገር ይፈጥር ከነበረው ተፅዕኖ አንፃር የስብሰባችን አካል ሆኗል።

ዳዊት ማሞ – መቻል

መድኖች በተደጋጋሚ በመስመሮች በኩል ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ ዳዊት በተሰለፈበት የግራ መስመር ኳስ ሲያስጥል ውሏል። ወደ ፊት ተስቦ በመጫወትም ለቡድኑ የማጥቃት ጉልበትን ሲጨምር ያስተዋልን ሲሆን ጨዋታው ሊገባደድ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ከቅጣት ምት ያስቆጠራት ድንቅ ጎል መቻሎች ሦስት ነጥብ እንዲያገኙ አስፈላጊ ነበረች።

\"\"
አማካዮች

አለልኝ አዘነ – ባህር ዳር ከተማ

የአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ቁልፉ ተጫዋች እንደሆነ እያስመሰከረ የሚገኘው አለልኝ ከተሰጠው የአማካይ ተከላካይ ሚናው በተዝናኖት ኳስን አቅልሎ ወደ ፊት እየተሳበ በተከታታይ ድንቅ ጎሎችን እያስቆጠረ ይገኛል። ለገጣፎን ሲያሸንፉ ካደረገው እንቅስቃሴ ባለፈ ድንቅ ጎልን ከመረብ ማገናኘት በመቻሉም የምርጥ ቡድናችን አካል አድርገነዋል።

ኤልያስ አህመድ – ድሬዳዋ ከተማ

የአጥቂ አማካዩ ኤልያስ ቡድኑ በጥቅሉ የተሻለ በተጫወተበት የሀዋሳ ፍልሚያ በግሉ ጎልቶ የወጣበትን ምሽት አሳልፏል። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ የቡድኑን የኳስ ቁጥጥር በላይኛው ሜዳ ለማድረግ አደገኛ የፊትዮሽ ኳሶችን ሲልክ የተስተዋለው ተጫዋቹ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ግብም የግል ጥረቱን ተጠቅሞ አመቻችቶ አቀብሏል።

አብስራ ተስፋዬ – ባህር ዳር ከተማ

ባህር ዳር ከተማ የዋንጫ ግስጋሴውን አጠናክሮ ለመቀጠሉ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ወሳኝነት አያጠራጥርም። ከቡድን አጋሮቹ ጋር መሀል ሜዳውን በአግባቡ እየተቆጣጠረ ለአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች ኳስን በምቾት የሚያቀብለው ያብስራ ባህር ዳር አምስተኛ ተከታታይ ድሉን በእጁ ሲያስገባ ሜዳ ላይ ጥሩ ጊዜን ከማሳለፉ በተጨማሪ አንድ ጎል በማስቆጠሩ የምርጥ ስብሰባችን አካል ሊሆን ችሏል።

መስዑድ መሐመድ – አዳማ ከተማ

አዳማ በአማካይ ክፍል ላይ ያለው መረጋጋት እና ብልጫ አንዱ ምክንያት ይህ ተጫዋች ነው። በጨዋታው ወትሮ እንደሚያደርገው በተደጋጋሚ ተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ በመግባት ዕድሎች የፈጠረው እና ሙከራዎች ያደረገው አማካዩ በእንቅስቃሴ ደረጃ የነበረው ጥሩ ብቃት በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።

አጥቂዎች

አቤል ያለው – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች ለአስፈሪው የፈረሰኞቹ የማጥቃት ክፍል ያለው አበርክቶ በጉልህ ያሳየበትን ሳምንት አሳልፏል።
ተጫዋቹ ዐፄዎቹን በገጠሙበት የሳምንቱ ትልቅ ጨዋታ አጎሮ ላስቆጠራት ወሳኝ ግብ አመቻችቶ በማቀበሉ እና ጥሩ እንቅስቃሴ በማሳየቱ በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ተኳታል።

እስማኤል ኦሮ አጎሮ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ለወትሮው በግብ አነፍናፊነቱ ብቻ የሚታወቀው አጎሮ በዚህ ሳምንት ወደ ኋላ ተስቦ በመጫወት በቡድኑ እንቅስቃሴ ውስጥ ጥሩ ድርሻ ሲወጣ ታይቷል።
በተጠባቂው ጨዋታ ግብ ጠባቂውን አልፎ ግሩም ግብ ያስቆጠረው ቶጓዊው አጥቂ ከግቡም በተጨማሪ ያሳየው እንቅስቃሴ ቡድኑን እንዲያሸንፍ ትልቅ አስተዋፆ ነበረው።

\"\"

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ

ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዋንጫ ግስጋሴ ውስጥ እንዳለ ቡድን ኮስተር ባለ አቀራረቡ ቀጥሏል። በዚህ ሳምንት ፋሲል ከነማን በገጠመበት ጨዋታ ቡድኑ በእንቅስቃሴ የበላይ ሆኖ ከተጠባቂው ፍልሚያ ሙሉ ነጥብ ይዞ የወጣበት መንገድም አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ ብለን እንድንመርጣቸው አድርጓል።

ተጠባባቂዎች

ውብሸት ጭላሎ – መቻል
ቶማስ ስምረቱ – መቻል
ካሌብ በየነ – ሀዲያ ሆሳዕና
ደስታ ዮሐንስ – አዳማ ከተማ
በረከት ወልዴ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ዳዊት እስጢፋኖስ – ድሬዳዋ ከተማ
ዮሴፍ ታረቀኝ – አዳማ ከተማ