መረጃዎች | 84ኛ የጨዋታ ቀን

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት በመጀመሪያ ቀን የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር በ 11 ደረጃዎች እና በ 20 ነጥቦች ተበላልጠው 16ኛ እና 5ኛ ደረጃ ላይ ያሉት ለገጣፎ ለገዳዲ እና ሀዲያ ሆሳዕና ሲገናኙ ጣፎዎች ካሉበት የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ውስጥ ተስፋን የሚሰንቅ ውጤት ለማግኘት ሆሳዕናዎች ያስመዘገቡትን ተከታታይ ድል ለማስቀጠል ጥሩ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

\"\"

በ17ኛው የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን 2-1 በመርታት የተሻለ መነቃቃት ውስጥ የተጠበቁት ለገጣፎዎች ከዛ በኋላ ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ግን ሁለቱን ተረተዋል። ይባስ ብሎም በእነዚህ ሁለት ጨዋታዎች ያስተናገዷቸው 10 ግቦች በውድድሩ ዓመቱ የተቆጠሩባቸውን ግቦች 49 አድርሰውታል። ይህም ቡድኑ ትልቅ የአደረጃጀት ክፍተት እንዳለ ይጠቁማሉ። ሆኖም ሜዳ ውስጥ ከሚያሳዩት እንቅስቃሴ አንጻር በየ ጨዋታዎቹ ላይ በሚኖራቸው በራስ መተማመን የሚወሰን ቢሆንም በእንቅስቃሴ ደረጃ በመጠኑም ቢሆን ተስፋን ሰንቀዋል። አሰልጣኙ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የቻልነውን ሁሉ ሞክረን ቡድኑን ከመውረድ ለመታደግ እንተጋለን ብለው የጣሉትን ተስፋ ለመደገፍም ውጤቶችን በቶሎ መሰብሰብ ግድ ይላቸዋል። በነገው ዕለትም በአሸናፊነት መንፈስ ውስጥ ሆነው ከሚገጥሟቸው ሀዲያ ሆሳዕናዎች ብርቱ ፉክክር ይገጥማቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በአዳማ ቆይታቸው ካደረጓቸው አራት ጨዋታዎች በአንዱ አቻ በመለያየት በሦስቱ ድል የተቀዳጁት ሀዲያዎች በእነዚህ ጨዋታዎች ያስተናገዱት አንድ ግብ ብቻ መሆኑ ደግሞ ቡድኑ በውጤት ቀውስ ውስጥ ያሳለፈባቸውን የድሬዳዋ የመጨረሻ  ቆይታዎች የሚያስረሱ ጥንካሬዎቹ ናቸው። በእነዚህ አራት ጨዋታዎች ያስቆጠሯቸው አምስት ግቦች በአምስት የተለያዩ ተጫዋቾች መቆጠራቸው ደግሞ ቡድኑ አንድ ተጫዋች ላይ ጥገኛ አለመሆኑን ሲያመላክት በነገው ዕለትም  ሦስተኛ ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ በወራጅ ቀጠናው ግርጌ ላይ ከሚገኘው ለገጣፎ ለገዳዲ የሚገጥመው ፈተና ቀላል እንደማይሆን ይጠበቃል።

በለገጣፎ ለገዳዲ በኩል ሱለይማን ትራኦሬ ከጉዳት መመለሱ ሲያጠራጥር የኮፊ ሜንሳህ በቅጣት ምክንያት አለመሰለፍ እና የመዝገቡ ቶላ ከቅጣት መመለስ ግን ተረጋግጧል። በሀዲያዎች በኩል ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ከቅጣት ሲመለስ  ቃልአብ ውብሸት እና ቤዛ መድህን ግን በጉዳት ግልጋሎታቸውን አይሰጡም።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት የመጀመሪያ ግንኙነት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ተመስገን ብርሃኑ 99ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ግብ 1-0 መርታታቸው ይታወሳል።

ቀን 9 ላይ የሚጀምረውን ጨዋታ  ሀብታሙ መንግስቴ በመሐል ዳኝነት ፣ አሸብር ታፈሰ እና ታምሩ አደም በረዳትነት ፣ ዮናስ ካሳሁን በበኩላቸው በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

አዳማ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

የምሽቱ መርሐግብር በ 27 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠውን አዳማ ከተማ በ 21 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ሲዳማ ቡና ሲያገናኝ አዳማዎች ተከታታይ ድል አስመዝግበው የተደላደለ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ሲዳማዎች እጅግ ከናፈቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ላይ ድል ማድረግ የቻሉት አዳማዎች ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ግብ ሳያስተናግዱ ሲወጡ በመስመር ተከላካዮቻቸው ያልተገደበ የማጥቃት እንቅስቃሴ በተለይም በቀኙ የማጥቂያ መስመራቸው ከጀሚል ያዕቆብ በሚነሱ ኳሶች የፈጠሯቸው በርካታ የግብ ዕድሎች ለተመልካች ማራኪ ነበሩ። ይህ እንቅስቃሴም ከኳስ ጋር ማሳለፍን የሚመርጠው ቡድኑ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተጨማሪ አጋዥ ስለሚሆነው በነገው ጨዋታም ይህንኑ አጨዋወት በመከተል ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ውጤቶችን የመሰብሰብ ግዴታ ውስጥ ከገባው ሲዳማ ቡና ጋር ጠንካራ ፉክክር ማድረግ ይጠበቅበታል።

ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው 15 ነጥብ 2 ነጥብ ብቻ ያሳኩት ሲዳማዎች ይባስ ብሎም በእነዚህ ጨዋታዎች ላይ ያስቆጠሯቸው ግቦች 2 ብቻ መሆናቸው ቡድኑ ከተጠበቀበት ደረጃ አንጻር እጅግ ከፍተኛ የውጤት ቀውስ ውስጥ ስለመሆኑ ይመሰክራል። በተለይም የሚፈጥሯቸውን የግብ ዕድሎች በማባከን ሙሉ ነጥብ ለማሳካት ቢቸገሩም የራሳቸው የግብ ክልል ውስጥ ባልተደራጀ አቋቋም እና ትኩረት ማጣት የሚያስተናግዷቸው ግቦች ትልቅ ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮቹ ናቸው። ፡ሆኖም በነገው ዕለት በመቀመጫ ከተማው ከሚወዳደረው እና ተከታታይ ድል ለመቀዳጀት ከሚገባው አዳማ ከተማ ጋር ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።

\"\"

የአዳማ ከተማው አጥቂ ዳዋ ሆቴሳ ለሀዋሳው ውድድር ይመለሳል ተብሎ ሲጠበቅ ዊሊያም ሰለሞን እና አብዲሳ ጀማል አሁንም ከቡድኑ ጋር አይገኙም። በሲዳማ በኩል ግን ያኩቡ መሐመድ እና ሙሉአለም መስፍን ከጉዳት መመለሳቸው አጠራጠሪ መሆኑ ታውቋል።

ሁለቱ  ቡድኖች ከዚህ ቀደም በተገናኙባቸው 23 ጊዜያት ሲዳማ 9 አዳማ ደግሞ 5 ጊዜ ድል ሲቀናቸው 9ኙ ጨዋታዎች አቻ የተጠናቀቁ ናቸው። በግንኙነታተቻው ሲዳማዎች 21 አዳማዎች ደግሞ 18 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

የምሽቱን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በዋና ዳኝነት ፣  ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና አብዱ ይጥና በረዳትነት ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።