ታክቲካዊ ትንታኔ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-1 መብራት ሃይል

 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት

እሁድ ህድር 14 2007 ዓ.ም 10፡00

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-1 መብራት ሃይል

ታክቲካዊ ትንታኔ በሚልኪያስ አበራ

 

ቋሚ አሰላለፍ

መብራት ኃይል – 4-4-2

አሰግድ

አወት ገ/ሚካኤል ፣ አዎንዬ ሚካኤል ፣ በረከት ተሰማ ፣ አሳልፈው መኮንን

አዲስ ነጋሽ ፣ አዊካ ማናኮ ፣ ዊልያም ኤሳድጆ ፣ ተሾመ ኦሼ (ማናዬ ፋንቱ)

ራምኬል ሎክ ፣ ፒተር (ጌድዮን ታደሰ)

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ – 4-1-4-1

ዳዊት አሰፋ (ዮሃንስ ሽኩር)

አዲሱ ካሳ ፣ ቢንያም ሲራጅ ፣ አቤል አበበ ፣ አለምነህ ግርማ

ታዲዮስ ወልዴ

ተክሉ ተስፋዬ (ስንታለም ተሻገር) ፣ ሰለሞን ገ/መድህን ፣ አብዱልከሪም ሃሰን ፣ ኤፍሬም አሻሞ

ፊሊፕ ዳውዚ

እንደ መግቢያ …

በአራተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአዲስ አበባ ስታዲየም ያስተናገደው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እና በሊጉ ምስረታ የመጀመሪያ አመታት ስኬታማ የነበረውን የመብራት ኃይል ቡድን ነው ፡፡

በአስልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የሚመራው ንግድ ባንክ ከ15 ቀናት በፊት በዚሁ ሜዳ ሙገር ሲሚንቶ ሲገጥም ይዞት የገባውን 4-1-4-1 አሰላለፍን በዚህኛውም ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠቅሞቦታል ፡፡ በቋሚ አሰላለፉም ላይ ኤፍሬም አሻሞ ሲሳይ ቶሊን ተክቶ ከመግባቱ ውጪ ሌሎቹ ተጫዋቾች ላይ ሌላ ለውጥ አልነበረም ፡፡

ተጋጣሚው የአሰልጣኝ አጥናፉ አባተ መብራት ኃይል በመደበኛው 4-4-2ን (በጨዋታ ሒደት ወደ 4-4-1-1 የሚቀየር) ይዞ ወደ ሜዳ ገብቷል ፡፡ (ምስል 1)

Bank 1-1 Electric (1)

 

የንግድ ባንክ አማካዮች ሁለገብ ሚና (Versatility role)

(4-1-4-1 ፎርሜሽን በተለየም ፍላት 4-1-4-1) ተጠቃሽ ችግር አጥቂው ብቸኛ በመሆኑ በሜዳው ውርድ ከአማካዮቹ የሚነጠልበት (Isllate) ሁኔታ መኖሩ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ የዚህን አሰላለፍ የሚጠቀሙ ቡድኖች ከአማካይ ተከላካያቸው ፊት ያሉትን ሁለት የውስጠኛው የመሃል አማካዮቻቸውን ወደ ፊት በመላክ አጥቂው የጎንዮሽ /ውርድ/ አማራጭ እንዲኖረው ያደርጋሉ፡፡ ይህም አሰላላፍ የፊተኛው መስመር ጠበብ ያለ 4-3-3 እንዲመስል ያደርገዋል፡፡ ይህ አጥቂው በሜዳው የጎንዮሽ አቅጣጫ ኳስ ለማግኘት የሚሸፍነውን ቦታ (Area) ይቀንስለታል፡፡

በዚህ ፎርሜሽን ብቸኛ የፊት መስመር ተላላፊው ወደኋላ እየተመለሰ የተጋጣሚ ቡድንን የመከላከል ቅርፅ ትኩረት ሊወስድ በሚችል መልኩ እና በመሃለኛውየሜዳ ክፍል ለቡድኑ የቁጥር ብልጫ ሊያስያስኝ በሚችል መልኩ (ሀሰተኛ 9 ቁጥር ሚና) ሊጫወት ይችላል፡፡ ወደኋላ ተመልሶ ኳስን በመያዝ ዘግይተው በተጋጣሚ የአደጋ ክልል የሚደርሱ አማካዮችን በማጥቃት ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ያስችላል፡፡ ሆኖም ግን አጨዋወቱ በብቸኛ የአማካይ ተከላካይነት የሚሰለፈው ተጫዋች ላይ ከፍተኛ ጫናን ያሳድራል፡፡ ጫናው ባብዛኛው ተጋጣሚ ቡድን ፈጣን ሽግግር (ከመከላከል – ማጥቃት) ላይ ይታያል፡፡ የተከላካይ አማካዩ ከፊቱ እንዲሁም በጎንዮሽ የሚኖረውን ሰፊ ክፍተት የመሸፈን ሃላፊነት ይወድቅበታል፡፡ ስለዚህም የመስመር ተከላካዮች በዚህ 4-1-4-1 ፎርሜሽን በይበልጥ ወደፊት እየተጠጉ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ከማደረጋቸው ጎን ለጎን ለብቸኛው የአማካይ ተከላካያቸው የጎንዮሽ ጥመርት (Widith Prtnership) መፍጠር ይኖርባቸዋል፡፡

የንግድ ባንኮቹ ኤፍሬም እና ተክሉ ካላቸው የማጥቃት አጨዋወት ባህሪ ጋር በተያያዘ በይበልጥ ወደ መስመሩ ተጠግተው በመጫወት የwide midfielderን ሚና ሲወጡ አምሽተዋል፡፡ ይህ አጨዋወታቸው አጥቂው ፊሊፕ ዳውዚን ኢላማ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶችን ወደ ተጋጣሚ የጎል ክልል እንዲልኩ ከማደረጋቸውም በላይ የተጋጣሚን ፉልባኮች ባሉበት ሆነው ወደፊት እንዳይንቀሳቀሱና የማጥቃት አጨዋወት ላይ ቀጥተኛ እና አይነተኛ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡ ይህን በዘመናዊው እግር ኳስ ላይ ከመስመር አጥቂዎች የሚፈለገውን ሐላፊነት እንዲወጡ አስችሏቸዋል ፡፡ ባንክ ከዚህኛው የመስመር አጥቂዎች እገዛ በ16ኛው ደቂቃ ላይ ከመብራት የግራ የጎል ክልል በተክሉ ተስፋዬ አማካኝነት የተገኘቸውን ኳስ አጥቂው ፊሊፕ ዳውዚ ከመረብ እንዲያሳርፍ አድርጓል፡፡ በእርግጥ ለጎሉ መገኘት ከባንክ ተጫዎቾች ጥረት ባልተናነሰ መልኩ የመብራት የግራ መስመር ተከላካዮችና የሰሩት ስህተትም ተጠቃሽ ሊሆን ይችላል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱ የባንክ የውስጥኛው የመሃል ሜዳ አማካዮች ሰለሞን ገ/መድህን እና አብዱልከሪም ሃሰን (ግራ) ሚዛናዊ የሆነ አጨዋወት (ማጥቃትም መከላከልንም ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረግ) ከቡድኑ ጠንካራ ጎኖች ሊጠቀስ የሚገባው ነው፡፡ ሰለሞን እና አብዱልከሪም በተደጋጋሚ እንደታየው ወደፊት በመጠጋት ፊሊፕ ዳውዚን በማጥቃት አጨዋወት ላይ ወደ ኋላ በመሳብ ኳስ እንዲቀበልና ታዲዎስ ወልዴ በመከላከል በመርዳት የሚያደርጉት አስተዋፆ ሊያስመሰግናቸው ይገባል ፡፡

ከባንክ 2ቱ ፉልባኮቾች አንዱ አዲሱ ካሳ በማጥቃትም ይሁን በመከላከል በቀኝ መስመር በተጋጣሚ ላይ ለሚወስደው የበላይነት ቁልፉ ተጫዋች ነው፡፡ ወደፊት በመጠጋትና በተጋጣሚ የላይኛው ሜዳ ላይ በመገኘት የማጥቃት አንግሎችን በማስፋት የመቀባቢያ አማራጮችን በመፍጠር እንዲሁም ለታዲዎስ የጎንዮሽ ሽፋን በመስጠት የተዋጣ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ ምናልባትም የቡድኑ ጠንካራ ጎን ከተጠቀሰ አዲሱና ሁለገብ ሚናው መነሳቱ የማይቀር ነው፡፡

የመብራት ሃይሎች 4-4-2/4-4-1-1/ እና አተገባባራቸው

በአሰልጣ አጥናፉ አለሙ የሚመራው የሁለት ግዜ የፕሪምየር ሊጉ ቻምፒዮን መብራት ኃይል ከዚህ ቀደም የሚታወቅበትን ወጣቶች በብዛት የማፍራት አካሄድ በመተው ቡድኑን በይበልጥ በተለያዩ ሃገራት ዜጋ ተጫዋቾች አደራጅቶ በፕሪምየር ሊጉ በመሳተፍ ላይ ይገኛል፡፡ በእሁዱ ጨዋታ ቡድኑ በ 4-4-2 ፎርሜሽን ሲገባም የአጥቂው ራምኬል ነፃ ሚና የአሰላለፉን ቅርፅ 4-4-1-1 ምስልን ሲያሰጠው ለማስተዋል ችለናል፡፡ ነገር ግን መብራት ሃይል የተጠቀመበት ፎርሜሽን ያስገኛሉ ተብለው ከሚጠቀሱት መሰረታዊ የ4-4-2 ጠቀሜታዎች ዋነኛ የሆነውን Width (የጨዋታን ወደ መስመሮች ሰጥቶ በሜዳው ወርድ መጠቀም) እና በተጋጣሚ አጨዋወት ላይ የተመሰረተ የፉልባኮችን የማጥቃት ነፃነት ሲጠቀምበት አልተስተዋለም፡፡ በተለይም በግራ የመስመር ተከላካይነት የተሰለፈው የመብራት ሃይሉ አሳልፈው መኮንን ባብዛኛው የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ከመስመሩ ወጥቶ ለመጫወት አለመድፈሩና ከፊት ለፊቱ በመስመር አማካይት የተሰለፈው ተሾመ ኦሼ መስመሩን ጠብቆ መጫወት አለመቻሉ የመብራትን የቀኝ ሙሉ መስመር (በሜዳው ቁመት) ንግድ ባንኮች በነፃነት እንዲጫወቱ እድል ሰቷቸዋል ፡፡ ተሾመ መስመሩን ጠብቆ እንዳይጫወት ያደረገው ምክንያት ሁለቱ የመብራት የተከላካይ አማካዮች ካሜሩናዊው ዊሊያም እና ኡጋንዳዊዉ ካዊካ ማናኮ ለተከላካዮቻቸው ሽፋን ለመስጠት ወደኋላ በመጠጋታቸው እና በተከላካይና በአማካይ መስመሮች መካከል የሚኖረውን ክፍተት ለማጥበብ ባደረጉት ጥረት አጥቂዎቻቸው ተነጥለው ስለታዩ ያኑን ክፍተት ለመሙላት ይመስላል፡፡ በርግጥ የመብራቱ አጥቂ ራምኬ ሎክ በተራራቀው አማካኝና አጥቂ መስመር መካከል በመገኘት ድልድይ ለመፍጠር ያደረገው ጥረት ከፍተኛ ነው፡፡ ተጫዋቹ ከባንክ የመስመር ተከላካዮች ጀርባ በመገኘት የተጋጣሚው ቡድን ላይ ጫና ለማሳደር ጥሩ ተንቀሳቅሷል፡፡ ይህም የባንክን የግራ መስመር የመጥቃት ተሳታፊነት ላይ ሚና እንዳይኖረው ሲያደርግ ታይቷል፡፡ ዊሊያምና ማናኮ ወደ ተከላካዮቻቸው ተጠግተው ከመጫወታቸው በላይ እርስ በርሳቸው ተቀራርበው መገኘታቸው የጎንዮሽ ሰፊ ክፍተት ሲፈጥር ነበር፡፡ ብዙም በመስመር ተከላካዮቻቸው ሲሸፈን ያልታየውን ክፍተት አብዱልከሪምና ሰለሞን በተደጋጋሚ ሲጠቀሙበት ነበር፡፡

ምንአልባት አሰልጣኝ አጥናፉ 4-4-2 ይልቅ 4-2-3-1 መጠቀም መርጠው ቢሆን ኖሮ ውል አልባ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የተስተዋሉት ተጨዋቾቻቸው መጠነኛ መሻሻል ያሳዩ ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተጨማሪም የወንድሜነህ ዘሪሁን በቡድኑ ውስጥ አለመኖር አማካዩን ከአጥቂው ለማገናኘት የሚያስችል እና ለቡድኑ ፈጠራ እንዲኖር የሚያደርግ አማራጭን አሳጥቶታል፡፡ (ምስል 2)

Bank 1-1 Electric (2)

ሁለተኛው አጋማሽ

ባንክ ባደረጋቸው ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች (ከሙገር እና ከመብራት ኃይል) የመጀመሪያው አጋማሽ የሚያሳየውን የበላይነት በሁለተኛው አጋማሽ ሲዘልቅበት ማስተዋል አልቻልንም፡፡ መብራት ኃይሎች በሁለተኛው አጋማሽ 4-4-2ን በተለየ አተገባበር ( 4-1-3-2 የሚመስለውን የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር) ተጫውተዋል፡፡ ይህንንም ለማድረግ ዊሊያምን ከጎንዮሽ አጣማሪው ማናኮ ወደ ፊት ማስጠጋታቸው የኋላ ኋላ ውጤታማ ሆኖላቸዋል፡፡ ዊልያም በሁለተኛው አጋማሽ የመከላከሉንም ሆነ የማጥቃት አጨዋወት ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ሲከውን የአብዱልከሪምን ቀጥተኛ እንቅስቃሴም ገድቧል፡፡ የባንክ የመሃል አማካዮችን ወደፊት በመግፋት ከማጥቃት ወረዳው እንዲርቁም አስተዋፅኦ አበርክቷል አስችሏቸዋል፡፡ ታታሪነቱን ተጠቅሞም በተደጋጋሚ የጎል ሙከራዎችን በማድረግም ባንክ ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡ (ምስል 3 ላይ በድርብ መስመር የተሰመረውን ይመልከቱ)

ራምኬል በተደጋጋሚ ወደኋላ በመመለስ ታዲዎስ ላይ ባሳደረው ጫና ምክንያት አሰልጣኝ ፀጋዬ ተክሉን አስወጥተው ለታዲዎስ እገዛ ሊያደርግ የሚችለውን የተከላካይ አማካይ ስንታለም ተሻገርን አስገብተዋል፡፡ ቅርፁም በሂደት ወደ 4-2-3-1 ሊቀየር ችሏል፡፡ በመብራት ኃይል በኩልም 28 ቁጥሩ ፒተር ወጥቶ ጌድዮን ታደሰ ፣ በጨዋታው ደክሞ የታየው ተሾመ ኦሼ ወጥቶ ማናዬ ፋንቱን በማስገባት አጨዋወታቸውን ወደ 4-3-3/4-1-2-3 በመቀየር ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ (ምስል 3)

ሌላው የመብራት ሃይሎች ተጠቃሽ ለውጥ ይበልጥ በማጥቃት አጨዋወቱ የሚታወቀው አዲስ ነጋሽ አለምነህ ግርማን ባለበት አፍኖ በመያዝ በኤፍሬምና በአለምነህ መካከል ሰፊ እርቀት እንዲኖር አድርጓል፡፡ በዚህም የኤፍሬም የማጥቃት እንቅስቃሴ በእጅጉ ተገድቦ ነበር፡፡ በዚህም ጫና በግራ ማእዘን የተገኘችውን ቅጣት ምት ዊሊያም በጭንቅላቱ አስቆጥሮ ነጥብ ተጋርተው እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል፡፡

Bank 1-1 Electric (3)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *