በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ4ኛ ሳምንት አራት ጨዋታዎች ሁሉም ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል፡፡
መልካ ኮሌ ላይ ሙገርን ያስተናገደው ወልድያ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቆ የመጀመርያ ድሉን ለማግኘት ተጨማሪ ሳምንት ለመጠበቅ ተገዷል፡፡ ሙገር በ11ኛው ደቂቃ በ- – – ድንቅ ግብ አማካኝነት መሪ መሆን ሲችል በሁለተኛው አጋማሽ 59ኛው ደቂቃ ከቅጣት የተመለሰው አብይ በየነ ወልድያን አቻ የምታደርግ ግብ አስቆጥሯል፡፡
በደቡብ ደርቢ አርባምንጭ ላይ የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን ያስተናገደው አርባምንጭ ከነማ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቋል፡፡ ሲዳማ ቡናዎች ጨዋታውን ተቆጣጥረው ቢጫወቱም የግብ እድሎችን በመፍጠር በኩል አርባምንጮች የተሻሉ ነበሩ፡፡ ሲዳማ ጨዋታውን በአቻ ውጤት ቢያጠናቅቅም በ8 ነጥቦች አሁንም የሊጉን መሪነት ተቆናጧል፡፡ በአንጻሩ አርባምንጮች ያደረጓቸውን አራቱንም ጨዋታዎች በአቻ ውጤት አጠናቀዋል፡፡
አዲስ አበባ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመብራት ኃይል አቻ ተለያይተዋል፡፡ ንግድ ባንኮች የመጀመርያውን አጋማሽ በበላይነት ሲያጠናቅቁ ፊሊፕ ዳውዚ በቀድሞ ክለቡ ላይ ባስቆጠራት ግብ ለረጅም ደቂቃዎች መምራት ችለው ነበር፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ንግድ ባንኮች ፍፁም ተዳክመው ሲቀርቡ በአንጻሩ መብራት ኃይሎች የተሻለ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡ በ76ኛው ደቂቃም በእለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው ካሜሩናዊው ዊልያም ኤሳድጆ ከቅጣት ምት የተሸገረውን ኳስ በጭንቅላት በመግጨት መብራት ኃይል ነጥብ ተጋርቶ የወጣበትን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
አዳማ ላይ ዘንድሮ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገው አዳማ ከነማ ሀዋሳ ከነማን አስተናግዶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቋል፡፡
የ4ኛው ሳምንት ቀሪ 3 ጨዋታዎች ማክሰኞ በአዲስ አበባ እና የክልል ከተሞች ሲቀጥል ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራ የሊጉ ግርጌ ላይ የተቀመጠው ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናግዳል፡፡ አዲስ አበባ ስታድየም ደግሞ ደደቢት ወላይታ ድቻን 9፡00 ላይ ሲያስተናግድ 11፡30 ላይ የአምናው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መከላከያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡