የጨዋታ ሪፖርት – ወልድያ 1-1 ሙገር ሲሚንቶ

 

የ4ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እሁድ ሲቀጥል መልካ ኮሌ ስታድየም ላይ አዲስ መጪው ወልድያ ሙገር ሲሚንቶን አስተናግዶ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡

9፡05 ላይ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመርያዎቹ 10 ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች መሃል ሜዳ ላይ ያመዘነ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን በ11ኛው ደቂቃ የሙገሩ 22 ቁጥር ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ የአሰላውን ቡድን መሪ አድርጓል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኋላ ወልድያዎች ጫና መፍጠር የጀመሩ ሲሆን በ17ኛው ደቂቃ የቀድሞው የሙገር አጥቂ በዳሶ ሆራ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ እድሪስ በጭንቅላት በመግጨት ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርጓል፡፡ ከሙከራው በኋላ ግን በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተደራጀ የማጥቃት አጨዋወትና የግብ ሙከራዎች መታየት አልቻሉም፡፡

የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 3 ደቂቃዎች ሲቀሩ ሙገር ሲሚንቶዎች መሪነታቸውን ሊያሰፉበት የሚችሉበት አጋጣሚ ቢያገኙም በግብ ጠባቂው ዘውዱ ጠረት ግብ ሳይሆን ቀርቶ የመጀመርያው አጋማሽ በእንግዳው ቡድን 1-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ አሰልጣኝ ንጉሴ ኃይሉ የተጫዋች ቅያሪ ሲያደርጉ የወልድያን የመጀመርያ የፕሪሚየር ሊግ ግብ ያስቆጠረው አብይ በየነን ቀይረው በማስገባት ከበዳሶ ሆራ ጋር አጣምረዋል፡፡ በሜዳ ላይ ተጫዋቾችን አሸጋሽገው በተለይም በግራ መስመር በኩል ተደጋጋሚ ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡

የሁለተኛውን አጋማሽ አመዛኝ ክፍል ወልድያዎች የተቆጣጠሩ ሲሆን በ59ኛው ደቂቃ ከ40 ሜትር አካባቢ የተመታውን ኳስ ተቀይሮ የገባው አብይ በየነ ጨርፎ ወልድያን አቻ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል፡፡

ከግቡ በኋላ የሙገሩ አሰልጣኝ ግርማ ሃ/ዮሃንስ ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት የተከላካይ ቁጥራቸውን ሲጨምሩ በአንፃሩ ወልድያዎች በዳሶ ሆራን አስወጥተው ሌላውን አጥቂ ታጁዲንን ቀይረው አስገብተዋል፡፡ ወልድያዎች የመጀመርያ ድላቸውን ለማሳካት ጫና ለመፍጠር ቢሞክሩም ይህ ነው የሚባል አስደንጋጭ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጠት ተጠናቋል፡፡

የእለቱ አርቢትር ለ6 (ለወልድያ 4 ለሙገር 2 ) ተጫዋቾች የማስጠንቀቅያ ካርድ ሲያሳዩ በጨዋታው የስታድየም መግብያ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት ወልድያ ከባንክ ጋር የተገኘውን ያህል ተመልካች እንዳልተገኘም ተነግሯል፡፡

ከእለቱ ጨዋታ በኋላ ሙገር ከመሪዎቹ ጎራ ለመቀላቀል የነበረውን እድል ሲያመክን ወልድያ በ2 ነጥቦች በአደጋው ዞን እንዳለ 4ኛውን ሳምንት አጠናቋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *