አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በዕለቱ ዳኝነት ዙሪያ የሰጡት አስተያየት

\”ይህ ጥቅም መስጠት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምንም ነገር የለውም…

\”14 ለ 11 ሆኖ መጫወት ይቻላል ?…

\”…\’በአምላክ ነኝ\’ እያለ ልጆቹን አላጫውት አላቸው…

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በተደረገው 181ኛ ጨዋታ ሲዳማ ቡና በፊሊፕ አጃህ ብቸኛ ጎል ኢትዮጵያ መድንን 1-0 ማሸነፍ ችሏል። ከውጤቱ ባሻገር በጨዋታው ትኩረት ያሳበው ጉዳይ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በጨዋታው ሦስት ቀይ ካርዶችን በመዘዙት ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ የዕለቱ ዳኝነት ዙሪያ የሰጡት አስተያየት ነበር። የሜዳ ላይ ተጫዋቾች ከተመለከቷቸው ሦስቱ ቀይ ካርዶች ውስጥ ሁለቱ የደረሷቸው ኢትዮጵያ መድኖች ስምንት ቢጫ ካርዶችን ሲያስመዘግቡ ምክትል አሰልጣኛቸው ለይኩን ከበደ (ዶ/ር) ቢጫ ካርድ እንዲሁም ዋና አሰልጣኙ ገብረመድኅን ኃይሌም ቀይ ካርድ ተመዞባቸዋል።

\"\"

አሰልጣኝ ገብረመድኅን ከሱፐር ስፖርት ጋር የተለመደውን የድህረ ጨዋታ ቆይታ ሲያደርጉም እንደተጠበቀው ሁሉ ዋነኛ ትኩረት የነበረው የዳኝነቱ ጉዳይ ነበር።

\” እኔ አልገባኝም ! ስምንት ቢጫ ሁለት ቀይ አይገልፀውም\” በማለት ሀሳባቸውን የጀመሩት አሰልጣኙ \”ይህ ጥቅም መስጠት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምንም ነገር የለውም\” ሲሉ አጠቃላይ የዳኝነት ሂደቱን ገልፀውታል። በጨዋታው በጊዜ ጎል መቆጠሩ ቢረብሻቸውም አጨዋወታቸውን ማስተካከላቸውን ያስረዱት አሰልጣኙ ዳኝነቱ በውጤቱ ላይ ስለነበረው ተፅዕኖ \”እውነት ለመናገር መቋቋም አቅቶናል። 14 ለ 11 ሆኖ መጫወት ይቻላል ?\” ብለው በመጠየቅ \”አይቻልም !\” ሲሉ መልሱን ራሳቸው ሰጥተዋል።

በመቀጠል \”ውጪያዊ ጫና ነው የበዛብን ዛሬ\” ካሉ በኋላ እሳቸው ላይ ስለተመዘዘው ቀይ ካርድ ተጠይቀው ሲመልሱ \”እኔ ምንም ያልኩት ነገር የለም ፤ ሪከርድ ቢደረግ እኔ አላውቅም። ምን ተይዞ እንደመጣ አውቀዋለሁ።\” ያሉ ሲሆን የቀይ ካርዱ መነሻ ነው ስላሉት ቅፅበትም እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል \”ቦታው ልክ አይደለም ብቻ እንጂ እኔ ሌላ ኃይለቃል አልተናገርኩም። \’በአምላክ ነኝ\’ እያለ ልጆቹን አላጫውት አላቸው። ለምን \’በአምላክ ነኝ እያልክ ከምታጫውት…\’ስለው በቃ በዛ ነው ያስወጣኝ። ሌላ ምንም ነገር የለውም። ይሄ እንዴት ውጫዊ አይደለም ማለት ይቻላል ?\”

\"\"

አሰልጣኙ በመጨረሻም በቡድናቸው ወቅታዊ አቋም እንዳልተከፉ እና ዳኛው ተጫዋቾቻቸውን ስሜታዊ እንዲሆኑ ቢያደርግም ይህንን ተቋቁመው በጎድሎ ቁጥር ያደረጉትን እንቅስቃሴ አድንቀዋል።