ወደ ፕሪምየር ሊጉ ላደጉት የሲዳማ ቡና ዕንስቶች የገንዘብ ሽልማት ተበረከተ

የ2015 የሴቶች ከፍተኛ ሊግ ሻምፒዮን ለሆነው እና ወደ 2016 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላደገው ሲዳማ ቡና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶለታል።

የኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ከተመሠረተ አንድ አመት በኋላ በ2005 ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ጋር መተዋወቅ የቻለው የሲዳማ ቡና የሴት እግር ኳስ ቡድን በ2010 ለመፍረስ ከተገደደ በኋላ ባሳለፍነው ዓመት በሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ ጥረት ዳግም ተቋቁሞ በኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ ላይ ሲወዳደር ቆይቷል። ቡድኑም በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ዳግሞ ለመወዳደር እንዲረዳው ውድድሩን በበላይነት በማጠናቀቅ የከፍተኛ ሊጉ የዋንጫ ባለቤት በመሆን በ2016 በትልቁ የሊግ ዕርከን ላይ መሳተፉን ማረጋገጡ ይታወሳል።
\"\"
ይህንንም ተከትሎ ክለቡ በትላንትናው ዕለት አመሻሹን ለቡድኑ አባላት የእራት ግብዣ እና የገንዘብ ሽልማትን አበርክቷል። በፕሮግራሙ ላይ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋንታዬ ከበደ ፣ የክልሉ ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ እና የክለቡ ም/ፕሬዝዳት ጃጎ አገኘሁ ፣ የሴቶች እና ወጣቶች ቢሮ ም/ ሀላፊ አክሊሉ አለሙ ፣ የስፖርት ቢሮ ሀላፊ ፍሬው አሬራ ፣ የእግር ኳስ ፌድሬሽኑ ፕሬዝዳንት አንበሴ አበበ እና የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቡሽ አሰፋ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ስፖርተኞች በተገኙበት ነው ስነ ስርዐቱ የተደረገው ፤ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንታዬ ከበደ እና የክለቡ ም/ፕሬዝዳንት ጃጎ አገኘሁ ባደረጉት ንግግር ክለቡ በድጋሚ ተቋቁሞ በአጭር ዓመታት ውስጥ ማደጉ የሚያበረታታ መሆኑን ከገለፁ በኋላ ከቡድኑ ጎን በመሆን አስፈላጊውን ክትልል እና ድጋፍ ለማድረግ ከወዲሁ ስለ መዘጋጀታቸው በዝርዝር አብራርተዋል።
\"\"
በፕሮግራሙ ማጠናቀቂያም ለቡድኑ አጠቃላይ አባላት ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ሽልማት የተበረከተ ሲሆን ለክለቡ እዚህ መድረስ በተለያየ መልኩ ለደገፉ ግለሶች ተቋማት እንዲሁም ድርጅታችን ሶከር ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስጋና የሰርተፍኬት ስጦታ ክለቡ በማበርከት የዋንጫ ዕርክክብም ከተደረገ በኋላ የዕራት ግብዣ መርሀግብር ተከናውኖ ሁነኑ ተጠናቋል።

\"\"