ሪፖርት | የሳምንቱ የመጀመርያ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተገባዷል

አዳማ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታቸውን ያለጎል አጠናቀዋል።

\"\"

አዳማዎች ባለፈው ሳምንት ሽንፈት ካጋጠመው ስብስብ ኩዋሜ ባህ ፣ አማኑኤል ጎበና እና አቡበከር ወንድሙን በሰይድ ሀብታሙ ፣ ጀሚል ያዕቆብ እና ነቢል ኑሪ ተክተው ሲገቡ ፤ አርባምንጮች በበኩላቸው ባለፈው ሳምንት አቻ ከወጣው አሰላለፍ አካሉ አትሞ ፣ ቡታቃ ሸመና እና አሕመድ ሁሴንን በወርቅይታደስ አበበ ፣ አበበ ጥላሁን እና ኤሪክ ካፓይቶ ለውጠው ገብተዋል።

በፈጣን እንቅስቃሴ ታጅቦ በጀመረው ጨዋታ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ጥሩ የማጥቃት ፍላጎት ያሳዩበት ነበር ፤ ንፁህ የግብ ዕድሎችም ፈጥረዋል። በአርባምንጭ በኩል ተመስገን ደረስ መቶት ሰይድ የመለሰበት ኳስ እና በአዳማ በኩል ደግሞ ቦና ዐሊ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከነው ወርቃማ አጋጣሚ ይጠቀሳሉ።

የመጀመርያው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ረገድ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ቢሆንም አዞዎቹ በአንፃራዊነት የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ፈጥረዋል። በተለይም አቡበከር ሻሚ በአንድ ሁለት ቅብብል የመጣውን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ መስመር ጠርዝ ሆኖ መቶት የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ አዞዎቹን መሪ ለመሆን የታቀረቡበት አጋጣሚ ነበር። በፈጣን እንቅስቃሴ ጀምሮ ብዙም ሳይቆይ በሁሉም መለክያዎች የተቀዛቀዘው የመጀመርያው አጋማሽ ያለግብ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ በሙከራዎች ያልታጀበ ደካማ እንቅስቃሴ በታየበት አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የጠራ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የተቸገሩበት ነበር።
አዳማ ከተማዎች ምንም እንኳ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ቀይረው ቢያስገቡም ቅያሪው እምብዛም ለውጥ አላመጣም። 

\"\"

በመጀመርያው አጋማሽ በማጥቃቱ ረገድ አንፃራዊነት የተሻሉ የነበሩት የአዞዎቹም ቢሆኑ ተመስገን ደረስ ካደረገው ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

ሆኖም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የአዳማዎች የበላይነት የታየበት ነበር ፤ ቡድኑም በሦስት አጋጣሚዎች ንፁህ የግብ ዕድሎች ፈጥሯል። በተለይም አቡበከር ከቆመ ኳስ አሻምቷት ከግቡ አጠገብ የነበረው አድናን ወደ ላይ የላካት ኳስ እና በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ገብተው ዮሴፍ ከመምታቱ በፊት ተከላካዮች ተረባርበው ያወጧት ሙከራ የማታ ማታ ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

ከጨዋታው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን የሰጡት አሰልጣኝ ይታገሱ በነበረው የአየር ሁኔታ ምክንያት ጨዋታው እንደፈለጉት እንዳልሄደ እና የነበረው ከፍተኛ ፀሐይ እንደፈለጉ መንቀሳቀስ እንዳገዳቸው ገልፀዋል። የአርባምንጭ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በበኩላቸው በመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ ተንቀሳቅሰው የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት እንዳደረጉ ገልፀው ሁለተኛው አጋማሽ ግን እሱን ለመድገም መቸገራቸው አውስተዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም ከፊት ለፊታቸው መልካም ነገር እንዳለ እና ቀጣይ ጨዋታዎች አሸንፈው ደረጃቸው ለማሻሻል እንደሚጥሩ ገልፀዋል።