የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ዝግጅቷን ጀምራለች

ሰኔ 13 ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ጨዋታ ያለባት ማላዊ በተሟላ ሁኔታ ባይሆንም ዝግጅቷን ጀምራለች።

በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የአህጉራችን ብሔራዊ ቡድኖች የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ የሚገኝ ሲሆን በቀጣዩ ወር ደግሞ የምድብ 5ኛ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በውድድሩ ለመሳተፍ እጅግ የጠበበ ዕድል ያላት ኢትዮጵያ ከማላዊ እና ግብፅ ጋር ቀሪ መርሐ-ግብሮች ያሉዋት ሲሆን ሰኔ አስራ ሦስትም ከማላዊ ጋር ጨዋታዋን ታደርጋለች።
\"\"
ኢትዮጵያ በሜዳዋ መጫወት አለመቻሏን ተለትሎ በሞዛምቢክ በሚደረገው የምድቡ 5 ጨዋታ የኢትዮጵያ ተጋጣሚ ማላዊ ከወዲሁ ዝግጅቷን ጀምራለች። ከሀገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች በተገኘ መረጃ ባሳለፍነው ሳምንት የቅድመ ተጫዋች ምርጫ (30 ተጫዋቾች) ያደረጉት የብሔራዊ ቡድኑ ጊዜያዊ አሠልጣኝ ፓትሪክ ማቤዲ በቋሚነት ዝግጅታቸውን እስኪጀምሩ ድረስ በሀገር ውስጥ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች በሳምንት ሦስት ቀናት እየተሰባሰቡ ልምምድ ሰርተው ጎን ለጎን የክለብ ግዳጃቸውን እንዲፈፅሙ በማድረድ ከትናንት በስትያ ልምምድ ማሰራት ጀምረዋል።
\"\"
በሀገር ውስጥ ከሚጫወቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ በደቡብ አፍሪካ ሊግ ሲጫወት የነበረው ዴኒስ ቼምቤዚም ስብስቡን ተቀላቅሎ ልምምድ መስራት እንደጀመረ ተጠቁሟል። በዚህ ሂደት ቡድኑ ልምምዱን የጀመረ ሲሆን ከቀናት በኋላ በቋሚነት በመሰባሰብ መደበኛ ልምምዱን እንደሚጀምር ተገልጿል።