ሪፖርት | መድን የዓመቱ 14ኛ ድሉን ኢትዮጵያ ቡናን በማሸነፍ አሳክቷል

ኢትዮጵያ መድን ኢትዮጵያ ቡናን 2-1 በመርታት የሀዋሳ ቆይታውን በድል ዘግቷል።

ኢትዮጵያ መድን ከወልቂጤው ሽንፈት በሦስት ተጫዋች ላይ ቅያሪ አስፈልጎታል። ሐቢብ መሐመድ ፣ ዮናስ ገረመው እና ሀብታሙ ሸዋለምን በፀጋሰው ድማሙ ፣ አሚር ሙደሲር እና ወገኔ ገዛኸኝ ሲተኩ ሀድያ ላይ ኢትዮጵያ ቡና ድል ካደረገው ስብስቡ ጉዳት በገጠመው ሬድዋን ናስር ምትክ ጫላ ተሺታን በብቸኝነት ለውጠዋል።

\"\"

ጨዋታውን ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ የጀመሩት ኢትዮጵያ መድኖች በብዙ ረገድ በተሻሉበት የመጀመሪያው አጋማሽ ኳስን የመሐል ክፍሉን ከመስመር አጥቂዎች ጋር በማጣመር በድግግሞሽ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በመግባት ለስህተት ይጋለጡ የነበሩትን የቡና የተከላካይ ክፍል ሲረብሹ ተስተውለዋል። ለዚህም ጨዋታው ተጀምሮ 3ኛው ደቂቃ ላይ ሲሞን ፒተር የግቡ ቋሚ የመለሰበት እና 15ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል የደረሰውን ኳስ ሲሞን በድጋሚ ጥሩ ቦታ ላይ ተገኝቶ የደረሰችውን ኳስ ወደ ግብ ሲመታ በረከት አማረ መልሶበታል። ከራስ ሜዳ በሚደረግ ቅብብል ወደ ተጋጣሚ ለመሻገር ጥረት ያደርጉ የነበሩት ቡናዎች የተከተሉት የጨዋታ መንገድ ፍሬያማ ባለመሆኑ በሒደት ወደ መስፍን ታፈሰ ዘንበል ብለው ለመጫወት ከሞከሩ በኋላ በተወሰነ መልኩ ራሳቸው ማግኘት ችለዋል።

\"\"

በወጥነት ከማጥቃት ያልቦዘኑት መድኖች ባሲሩ እና ወገኔን መሐል ላይ ከሲሞን እና ብሩክ ጋር በማቆራኘት ግብ ለማስቆጠር በብርቱ ታግለዋል። ጥረታቸው ሰምሮ 24ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ከግራ ወደ ውስጥ የሰጠውን ወገኔ ገዛኸኝ ቅልጥፍናውን ጨምሮበት ቆንጆ ጎል በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከጎሉ በኋላ ምላሽ ለመስጠት ቡናማዎቹ በመስፍን ሁለት ጊዜ ሙከራን አድርገዋል። በተለይ 31ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ከግራ ወደ ውስጥ የሰጠውን ብሩክ በየነ ብረት የመለሰበት የምታስቆጨዋ ዕድላቸው ሆናለች። ጨዋታውም መድን እንደ ነበረው ብልጫ አጋማሹ በ1ለ0 ተጋምሷል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ኢትዮጵያ ቡና በይበልጥ ለማጥቃት ያሰቡ የሚመስል ለውጥን አድርገዋል። በቀዳሚው አጋማሽ ተቀዛቅዞ የነበረውን ጫላ ተሺታን በአንተነህ ተፈራ መተካት ቢችሉም ስልነታቸውን በተሻለ አጠናክረው የተመለሱት መድኖች በመስመር በጥልቀት በቀላሉ የሚፈጥሯቸውን ጥቃቶች ገና አጋማሹ እንደተጀመረ ማድረግ ችለዋል።

\"\"

 49ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም መሐመድ ከቀኝ ወደ ግብ ክልል መሬት ለመሬት የላካትን ኳስ ወገኔ ገዛኸኝ መትቶ በረከት ያዳነበት ተጠቃሿ ሙከራ ነች። የመስፍን ግልጋሎት ከቃልአብ ጋር በማገናኘት በሚሻገሩ ኳሶች ቀዳዳ ፍለጋ ላይ ቡናማዎቹ ቢሰማሩም የመጨረሻ ውሳኔዎቻቸው እጅጉን ደካማ ነበር። ለዚህም ማሳያ ቃልአብ ከርቀት መትቶ በተከላካይ ተጨራርፋ ወደ ውጪ የወጣችዋ እና ቃልአብ ከመስፍን ጋር ባደረገው ቅብብል ወደ ውስጥ አሻምቶ ብሩክ ያመለጠችዋ የቡድኑ ደካማ ሙከራዎች ናቸው።

\"\"

ጨዋታውን በራሳቸው ቁጥጥር ስር አድርገው ይንቀሳቀሱ የነበሩት መድኖች ሁለተኛ ጎልን አግኝተዋል። 52ኛው ደቂቃ ብሩክ ሙሉጌታ የግል አቅሙን ተጠቅሞ ተከላካዮች አልፎ ያመቻቸለትን ኳስ ወገኔ ገዛኸኝ ወደ ጎል ሲመታው ኃይለሚካኤል አደፍርስ ተደርቦ ነክቷት በራሱ መረብ ላይ አስቆጥሯል። በወገኔ ፣ ብሩክ እና ሲሞን ለተጨማሪ ግቦች የጣሩት መድኖች 74ኛው ደቂቃ ሲሞን ፒተር ከተጫዋቾች ጋር ታግሎ ከሳጥን ውጪ መትቶ በንቃት በተደጋጋሚ ኳሷን ሲመለስ የነበረው በረከት አሁንም መልሶበታል። የመጨረሻዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ወደ እየነቁ የመጡት ቡናዎች በአንድ ለአንድ ግንኙነት 78ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ በየነ ከአቡበከር ኑራ ጋር ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው በሚገርም ብቃት አስጥሎታል። ከዚህች ሙከራ በኋላ 82ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጎል የተመታች ኳስን አቡበከር በአግባቡ ባለ መቆጣጠሩ ቡናን ወደ ጨዋታ የመለሰች ግብ ሮቤል ተክለሚካኤል ከመረብ አሳርፏታል። ጨዋታው በመጨረሻም በመድን የ2-1 ተቋጭቷል።

\"\"