የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ መድን 2-1 ኢትዮጵያ ቡና

\”ቡድናችን ዛሬ ድክመት ነበረበት።\” – አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ

\”ያለንን አቅም አውጥተን ነው የተጫወትነው።\” – ምክትል አሰልጣኝ ለይኩን ታደሰ

ኢትዮጵያ መድን የሀዋሳ ቆይታውን ኢትዮጵያ ቡና ላይ የ 2-1 ድል በመቀዳጀት ከቋጨ በኋላ የሁለቱም ቡድኖች አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለ ጨዋታው…

\”በመጀመሪያው አጋማሽ በጣም ድካሞች ነበሩ። በተወሰነ መልኩ እነሱ የተሻሉ ነበሩ እና ጥሩ በነበሩ ሰዓት ነው ግቦችን ያገኙት ፤ ከዛ በኋላ ለማስተካከል ብዙ ሞክረናል። ቡድናችን ዛሬ ድክመት ነበረበት ፤ በተለይ መሃል አካባቢ ላይ እነሱ ብልጫውን አግኝተዋል። ከዕረፍት በፊትም ሆነ በኋላ በዛ ለመጠቀም ሞክረዋል።\”

\"\"

ጥሩ ስላልሆኑበት ምክንያት…

\”አንዳንዴ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ይኖራሉ። ድካም ይኖራል የተወሰነ ክፍል ሊበላሽብህ ይችላል። አማካይ ላይ ወይ ተከላካይ ላይ አንዳንዴ በእግርኳስ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ይመጣሉ። ለሚቀጥለው ጨዋታ ራሳችንን አስተካክለን እንመጣለን።\”

ያገኟቸውን የግብ ዕድሎች ስላለመጠቀማቸው…

\”ብዙ መጓጓቶች አሉ። በተለይ ብሩክ በየነ ግብ ይጠበቅበታል እና እሱን ለማሳካት በጣም ስለሚጨነቅ እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎችን ሲያገኝ አይጠቀምም እና ይህም ቡድናችን ላይ ጉዳት አለው። ነገር ግን በድግግሞሽ የሚስተካከል ነው።\”

ምክትል አሰልጣኝ ለይኩን ታደሰ – ኢትዮጵያ መድን

ስለ ጨዋታው…

\”ጨዋታው ጥሩ ነበር። ባለፉት ጨዋታዎች ላይ የጎደለንን የተነሳሽነት ሁኔታ ለመጨመር ተዘጋጅተናል። ተጫዋቾቹም በዛ መሠረት ይህንን ስለተገበሩ ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል።\”

ዛሬ ተሻሽለው ስለቀረቡበት ምክንያት…

\”የመጀመሪያው ምክንያት የሜዳው መሻል ነው። ሜዳው ሲሻሻል ተጫዋቾቹ እንደልብ መጫወት ይችላሉ። ሁለተኛ ከባለፈው ውጤት ቁጭት አለባቸው እና በዛ ምክንያት የተሻለ መነሳሳት ነበራቸው። ከዛ ውጪ ውጤቱ በደረጃው እኛን ወደ ላይ ከፍ አድርጎ የሚያደላድለን ስለሆነ እሱ ተጨማምሮ ነው።\”

\"\"

በመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ስለተፈጠረባቸው ጫና…

\”ውጤቱን ከመፈለግ አንጻር ነው። ጨዋታው የተደረገው 7 ሰዓት ላይ ነው ፤ አቅም ይፈልጋል። ስለዚህ ያለንን አቅም አውጥተን ነው የተጫወትነው። ያንን ስለጠበቅንም ነው ቅያሪዎችን ያደረግነው።\”