መረጃዎች | የጨዋታ ቀን 103

በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት መገባደጃ ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርቧል።

ሀድያ ሆሳዕና ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ሀድያ ሆሳዕና እና መውረዱን ያረጋገጠው እና የአሰልጣኝ ለውጥ ያደረገው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚያደርጉት ጨዋታ 7:00 ላይ ይጀመራል።

ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት አቻ ፤ ሁለት ሽንፈትና አንድ ድል አስመዝግበው ሠላሳ ስድስት ነጥቦች የሰበሰቡት ሀድያዎች በሰንጠረዡ ወገብ ለመቆየት ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ማግኘት የግድ ይላቸዋል። ከተከታታይ ሁለት አቻዎች በኋላ ጠንካራውን ባህር ዳር አሸንፈው በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ቢገጥማቸውም የነገው ጨዋታ ከተጋጣምያቸው አንፃር ሲታይ በተሻለ የሞራል ልዕልና ስለሚገኙ ከወዲሁ ጨዋታውን አሸንፈው ለመውጣት እንደሚያልሙ እሙን ነው።
በውድድር ዓመቱ ከነገው ተጋጣምያቸው ኤሌክትሪክ ጨምሮ በስምንት ጨዋታዎች የባዶ ለባዶ አቻ ውጤት ያለው ቡድኑ በአንፃራዊነት የተሻለ እምብዛም ግብ የማይቆጠርበት (18 ግቦች) ጠንካራ የተከላካይ ክፍል አለው። ሆኖም በአጥቂ ክፍል ላይ ያለው ሰፊ ክፍተት ግቦችን እንዳያስቆጥር ሳንካ ሆኖበታል።

\"\"

በመጨረሻ ካደረጓቸው አስር ጨዋታዎች አስራ ስምንት ግቦች አስተናግደው ስድስት ሽንፈቶች የገጠሟቸው ኤሌክትሪኮች በአዲስ አሰልጣኝ እየተመሩ የነገው ጨዋታቸው የምያደርጉ ይሆናል። ቀድሞ መውረዱ ያረጋገጠው ይህ ቡድን በነገው ጨዋታ ብዙም ለውጦች ያደርጋል ተብሎ አይጠበቅም። ቡድኑ ይፋ ባያደርገውም ከወዲሁ ከበርካታ ተጫዋቾች ጋር መለያየቱ እየተነገረ ይገኛል፤ ይህንን ተከትሎም በነገው ጨዋታ ይዞት የሚቀርበውን አጨዋወት ለመገመት አዳጋች ያደርገዋል።

በሀድያ ሆሳዕና በኩል ፍሬዘር ካሳ በቅጣት፤ ቤዛ መድህን በጉዳት ምክንያት አይሰለፍም፤ ብርሀኑ በቀለም ከጉዳት ቢመለስም የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው።

መቻል ከ ባህር ዳር ከተማ

የሳምንቱ የመጨረሻ መርሀ ግብር የሆነውና ለዋንጫ ፉክክር እና ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ቀጥተኛ ተፅዕኖ ያለው ይህ ጨዋታ በብዙዎች ዘንድ ተጠባቂ ነው።

ቅዱስ ግዮርጊስን ካሸነፉ በኋላ ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦች ብቻ የሰበሰቡት መቻሎች ከወራጅ ቀጠናው ያላቸው የነጥብ ልዩነት አራት ብቻ በመሆኑ አደጋ ውስጥ ላለመግባት ከነገው ወሳኝ ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት ይጠበቅባቸዋል። በአንፃራዊነት የፈጠራ አቅሙ የተሻለ የአማካይ ክፍል ያለው ይህ ቡድን የሁነኛ አጥቂ እጦቱ በሊጉ ላይ እንዲቸገር አድርጎታል፤ በነገው ጨዋታም የተጋጣሚውን ጠንካራ የማጥቃት አጨዋወት ከመመከት ባልተናነሰ የግብ ማግባት ችግሩ መፍታት ከጨዋታው ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ያግዘዋል። መቻል በመጀመርያው ዙር ድሬዳዋ ላይ ባህር ዳርን ሦስት ለሁለት ማሸነፉ ይታወሳል።

\"\"

ከፈረሰኞቹ ጋር በብርቱ የዋንጫ ፉክክር የሚገኙት የጣና ሞገዶቹ ተፎካካርያቸው ቀድሞ ድል በማድረጉ ከፉክክሩ ላለመራቅ ከዚህ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣት ይጠበቅባቸዋል። በሀድያ ሽንፈት ከገጠማቸው በኋላ የመጨረሻው የሊጉ ጨዋታ የተራዘመባቸው የጣና ሞገዶቹ ሰፊ የመዘጋጃ እና የማገገምያ ጊዜ ስለነበራቸው የተለመደው ፈጣን የማጥቃት አጨዋወታቸው ለመተግበር ምቹ ይሆንላቸዋል ተብሎ ይገመታል። ባህር ዳሮች የነገው ተጋጣምያቸው መቻል በአማካይ ክፍሉ ያለው የተሻለ ጥራት ወደ ጨዋታው በተለመደው መንገድ እንዳይቀርቡ እና ውስን የአጨዋወት ለውጥ እንዲያደርጉ ልያስገድዳቸው ይችላል።

በመቻል በኩል ፍፁም ፣ ቹል ፣ ኢብራሂም እና ሳሙኤል በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም።
በአንፃሩ ባህር ዳር ከተማዎች በቅጣትም በጉዳትም የሚያጡት ተጫዋች የለም።