ሪፖርት | ሀድያ ሆሳዕና ከመመራት ተነስቶ ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቷል

ጥሩ ፉክክርን ባስመለከተን የአዳማ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና ጨዋታ አዳማ 3-0 ቢመራም ነብሮቹ ነጥብ መጋራት ችለዋል።

ቡድኖቹ በሀዋሳ የመጨረሻ ጨዋታቸው ወቅት ተጋጣሚዎቻቸውን ከረቱበት አሰላለፍ በተመሳሳይ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። አዳማዎች ቅጣት ባስተናገዱት አድናን ረሻድን እና አቡበከር ወንድሙ ምትክ እዮብ ማቲዮስን እና ቢኒያም አይተንን ሲተኩ ሀድያ ሆሳዕናዎች በበኩላቸው ቃልአብ ውብሸትን በፍሬዘር ካሳ ፣ ተመስገን ብርሀኑን በፀጋዬ ብርሀኑ ለውጠው ቀርበዋል።

\"\"

መሐል ሜዳ ላይ ያመዘኑ የንክኪ ኳሶች በዝተው በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጎልን ያስመለከተን ገና በጊዜ ነበር። 7ኛው ደቂቃ ግርማ በቀለ ከግቡ ትይዩ በግምት 20 ሜትር ርቀት ላይ ቢኒያም አይተን ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምት ዳዋ ሆቴሳ ያሬድ በቀለ መረብ ላይ አሳርፏት አዳማን መሪ ማድረግ ችሏል። ቀጣዮቹን የጨዋታ ደቂቃዎች ሀድያ ሆሳዕናዎች በተሻለ መልኩ ከመሐል ሜዳው ይልው ከመስመር መነሻውን ባደረገ አጨዋወት የሰመረ እና ባዬን ግልጋሎት በመጠቀም በቀላሉ ወደ ተጋጣሚያቸው ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሳይቸገሩ ቶሎ ቶሎ ሲደርሱ ብናስተውልም የሚታይባቸው የመረጋጋት ችግር ያገኟቸውን ዕድሎችን በአግባቡ እንዳይጠቀሙ አድርጓቸው ተስተውሏል።

አማካዮቻቸው ኳስን ሲያገኙ በፍጥነት ለአጥቂዎች በማሾለክ ተጨማሪ ግብን ለማስቆጠር ቀዳዳ ሲፈልጉ ይታዩ የነበሩት አዳማ ከተማዎች ዘለግ ካለ ደቂቃ በኋላ ሁለተኛ ግባቸውን ወደ ቋታቸው ከተዋል። 39ኛው ደቂቃ ላይ ከአማካይ ክፍል የደረሰውን ኳስ ወደ ሳጥን ውስጥ አሜ መሐመድ ይዞ ሲገባ ወጣቱ ግብ ጠባቂ ያሬድ ብርሀኑ ተጫዋቹ ላይ ጥፋት በመስራቱ የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምት ዳዋ ሆቴሳ ለራሱም ሆነ ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አድርጓታል። በእንቅስቃሴ ይሻሉ እንጂ በሰሯቸው ስህተቶች ከቆሙ ኳሶች ግብ ያስተናገዱት ሀድያዎች ጥራት ያላትን ሙከራ 35ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ለፍቅየረሱስ ሰጥቶት አማካዩ ለፀጋዬ ሰጥቶት ተጫዋቹ የሞከራትን ሰይድ ሀብታሙ ያዳነበት እና ፍቅረየሱስ ሀይል አልባ የሆነች ሙከራን አድርጎ በቀላሉ ሰይድ የያዘበት በቡድኑ የተፈጠሩ አጋጣሚዎችን ቢሆኑም ጨዋታው በአዳማ 2ለ0 መራነት ተጋምሷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ተመልሶ ሁለት ደቂቃ ብቻ እንደተቆጠረ ፈጣን ጎል አስመልክቶናል። ከማዕዘን ምት ዮሴፍ አስጀምሮ ለደስታ የሰጠውን የግራ መስመር ተጫዋቹ ወደ ውስጥ ሲያሻማ አዲሱ ተስፋዬ በግንባር የአዳማን ሦስተኛ ግብ አክሏል። ከጎሏ በኋላ ባሉት ደቂቃዎች ራሳቸውን ወደ ጨዋታ ቅኝት በሚገባ እየከተቱ የመጡት ሀድያዎች ቀጥተኛ ኳሶችን በመጫወት ግቦችን ለማግኘት በተለይ ባዬን የትኩረት ማዕከል በማድረግ ለመንቀሳቀስ ከሞከሩ በኋላ 53ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል። ፀጋዬ ብርሀኑ ብረት ከመለሰበት ሙከራው ከአንድ ደቂቃ መልስ ራሱ ፀጋዬ ከቀኝ ወደ ውስጥ የላካትን ኳስ ባዬ ጨርፎ በመጨረሻም ሠመረ ሀፍታይ መረብ ላይ አሳርፏታል።

የሀድያ ሆሳዕናን ቀጥተኛ ኳሶች መመከቱ ላይ ድክመት የሚታይባቸው አዳማዎች ኳስን በሚያገኙበት ወቅት በመልሶ ማጥቃት በመጫወት ጥቂት የማይባሉ ዕድሎችን አግኝተው ነበር። ለዚህም ማሳያው በዚህ የጨዋታ መንገድ 60ኛው ደቂቃ ዳዋ ከግብ ጋር ተገናኝቶ እያሱ ያወጣችበት ተጠቃሿ ሙከራቸው ነበረች። የተጫዋች ለውጥን በሒደት ያደረጉት ሀድያ ሆሳዕናዎች 63ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርሱ ሁለተኛ ጎልን ማግኘት ችለዋል። ሚሊዮን ሰለሞን ተቀይሮ የገባው ተመስገን ብርሀኑ ሳጥን ውስጥ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ባዬ ገዛኸኝ ሰይድ መረብ ላይ ቀላቅለቀታል። ጨዋታውን ወደ ራሳቸው ቁጥጥር ስር እያደረጉ የመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች 83ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ በረጅሙ የደረሰውን ኳስ የሰይድ ሀብታሙ ከራስ ግብ ክልል ለቆ መውጣትን ተመልክቶ ከጠበበ ቦታ ማራኪ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በመጨረሻም 3-3 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሀድያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በመጀመሪያው አጋማሽ መከላከል ላይ አመዝነው በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት አስበው እንዳልተሳካላቸው ገልፀው በሁለተኛው አርባ አምስት የተቀየሩ ተጫዋቾችን ተጠቅመው በማጥቃት ላይ አተኩረው መግባታቸው ነጥብ ይዘው እንዲወጡ እንዳደረጋቸው ጠቁመዋል። የአዳማ ከተማው አቻቸው ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ተንቀሳቅሰው ጎል እንዳስቆጠሩ ከገለፁ በኋላ በሁለተኛው አጋማሽ በተሰሩ ስህተቶች ይመራ የነበረው ቡድን ተነሳሽነታቸው ከፍ ብሎ በመገኘቱ በተፈጠረብን አለመረጋጋት ግቦች ተቆጥረው በአቻ ለመጨረስ መገደዳቸውን በንግግራቸው አውስተዋል።

\"\"