ሪፖርት | ኃይቆቹ ተከታታይ ድል አስመዝግበዋል

ሀዋሳ ከተማ በዓሊ ሱለይማን ግቦች ከሊጉ የወረደውን ኢትዮ ኤሌክትሪክ 2-1 በመርታት ወደ አራተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።

\"\"

ምሽት 12 ሰዓት ላይ የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ ኤሌክትሪኮች በ 27ኛው ሳምንት በሀዲያ ሆሳዕና 2-1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ፍቅሩ ወዴሳ ፣ አማረ በቀለ እና ፍጹም ገብረማርያም በ ጋክፖ ሼሬፍዳይን ፣ ማታይ ሉል እና ሚኪያስ መኮንን ቦታ ተተክተው ገብተዋል። ኃይቆቹ በበኩላቸው በተመሳሳይ ሳምንት ወላይታ ድቻን 3-1 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ሰይድ ሀሰንን አስወጥተው ዳንኤል ደርቤን በማስገባት ለጨዋታው ቀርበዋል።

እጅግ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ያልተደረገበት ነበር። በሀዋሳ ከተማ በኩል 18ኛው ደቂቃ ላይ ሙጅብ ቃሲም ከእጅ ውርወራ ያቀበለውን ኳስ በሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው ተባረክ ሔፋሞ በውጪ እግሩ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ኤፍሬም አሻሞ ሙሉ በሙሉ በግንባሩ ሳያገኘው ቀርቶ ተጨርፎ ሲወጣበት ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ዓሊ ሱሌይማን ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ሳይዘጋጅ ያገኘው ሙጅብ ቃሲም ኳሱ ትከሻውን ገጭቶ ሲወጣበት ቡድኑም ከዚህ የተሻለ የግብ ዕድል ለመፍጠር መቸገሩን ቀጥሏል።

በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ ቢወስዱም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የተቸገሩት ኤሌክትሪኮች 33ኛው ደቂቃ ላይ ሙሴ ከባላ ከረጅም ርቀት ባደረገው ኃይል የለሽ ሙከራ የመጀመሪያውን የግብ ሙከራቸውን ሲያደርጉ በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ግን ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። ዳንኤል ደርቤ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው  ተባረክ ሔፋሞ ያደረገው ሙከራ በተከላካይ ተደርቦ ሲመለስ ያንኑ ኳስ ዓሊ ሱሌይማን ወደ ግብ ቢሞክረውም ግብ ጠባቂው ፍቅሩ ወዴሣ መልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተሻሽሎ ሲቀጥል ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ይቸገሩ እንጂ መሃል ሜዳው ላይ ብልጫ በመውሰድ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ ችለው ነበር። ሆኖም ቀዝቃዛው ጨዋታ 63ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ በሀዋሳዎች አማካኝነት ግብ ተቆጥሮበታል። ኤፍሬም አሻሞ በግራ መስመር የተገኘውን የእጅ ውርወራ በፍጥነት አስጀምሮት ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ለነበረው አዲሱ አቱላ ሲያቀብል ያዐኳስ ከአዲስ አቱላ የተሻገረለት ዓሊ ሱለይማን አስቆጥሮታል።

ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉት ኃይቆቹ የኳስ ቁጥጥሩን ብልጫ በመውሰድ በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። መድሃኔ ብርሃኔ ሳጥን ውስጥ ከዓሊ ሱለይማን ጋር ባደረገው ግሩም ቅብብል ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፍቅሩ ወዴሣ ሲመልስበት ያንኑ ኳስ ያገኘው ዓሊ ሱለይማን በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎት ለራሱም ሆነ ለቡድኑ ሁለተኛውን ግብ አስመዝግቧል።

ኤሌክትሪኮች በሁለት ግቦች ልዩነት ከተመሩ በኋላ ይበልጥ ወደፊት ተጭነው መጫወት ሲችሉ 74ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልራህማን ሙባረክ ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ በቀላሉ ይዞበታል። በሴኮንዶች ልዩነትም ራሱ አብዱልራህማን ሙባረክ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው አብነት ደምሴ ሳይረጋጋ ሞክሮት የግብ ዕድሉን አባክኖታል።

85ኛው ደቂቃ ላይ በዓሊ ሱለይማን ከማዕዘን የተሻገረለትን ኳስ ዓየር ላይ እንዳለ በመምታት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችለው የነበሩት ሀዋሳዎች 87ኛ ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግደዋል። ጌቱ ኃ/ማርያም ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ተከላካዩ ሰለሞን ወዴሣ ሳይቆጣጠረው ቀርቶ ያገኘው አብዱልራህማን ሙባረክ መረቡ ላይ አሳርፎት ቡድኑን ለባዶ ከመሸነፍ አድኖታል። ጨዋታውም በሀዋሳ ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ቅጣው ሙሉ በመጀመሪያው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ደረጃ ጥሩ እንደነበሩ ሲናገሩ የግብ አጋጣሚዎችን አለማግኘታቸው እንጂ የጨዋታ መንገዳቸው ጥሩ እንደነበር በመግለጽ ጎል ካገቡ በኋላ ተጫዋቾች ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገው ያንን ለማስቀጠል ጥረት እንዳደረጉ ጠቁመው የተጫዋቾቹ እንቅስቃሴ ጥሩ እንደነበር ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። በጨዋታው ድል የቀናቸው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በበኩላቸው ጨዋታው ከውጤቱ አስፈላጊነት አንጻር አስቸጋሪ እንደነበር እና ውጤት ለመያዝ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ሲገልጹ አሰላለፋቸውን ወደ 3-4-3 በመቀየር ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ደግሞ ወደ 4-3-3 እንደቀየሩ ጠቁመዋል። ሙጅብን ጎል እስኪያገቡ አጥቂ ላይ ካገቡ በኋላ ቡድኑን ሚዛን ለመጠበቅ አማካይ እንደሚያደረጉት ይህንም ከዚህ በፊት ስለሚያውቁት ብዙ ሚናዎችን እንደሚወጣ እንደሚያምኑ እና ሽፋን መስጠት እንደሚችል መተዋወቃችን ጠቅሞናል ብለዋል።

\"\"