መረጃዎች| 109 የጨዋታ ቀን

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገም ሲቀጥሉ ሁለቱን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን

ዘጠኝ ሰዓት የሚካሄደው እና ሁለት ደረጃቸውን ለማሻሻል የሚፋለሙ ቡድኖችን የሚያገናኘውን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርቧል።

ሳይጠበቅ በለገጣፎ ለገዳዲ ከተሸነፉ በኋላ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ ድል እና አንድ አቻ ያስመዘገቡት አዳማዎች በሠላሳ ነጥብ በአስረኛ ደረጃ ተቀምጠዋል። ቡድኑ ምንም እንኳ ከመውረድ አደጋ ነፃ ቢሆንም ደረጃውን ለማሻሻል ያለው ዕድል ሰፊ በመሆኑ በነገው ጨዋታ ጠንክሮ መቅረብ ይጠበቅበታል።

ድሬዳዋ ከተማን ከማሸነፋቸው በፊት በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ላይ ኳስ እና መረብ ማገናኘት ተስኗቸው ነጥቦችን ለመጣል የተገደዱት አዳማዎች በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግን አምስት ግቦች አስመዝግበዋል። በነገው ጨዋታም ይህንን ጠንካራ ጎን ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል። ሆኖም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍላቸው ተጋጣሚው ግቦችን ለማስቆጠር የማይቸገር የመድን አጥቂ ክፍል ስለ ሆነ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክሮ መቅረብ ይኖርበታል።
\"\"

በአርባ ዘጠኝ ነጥቦች በሦስተኛ ደረጃነት
የተቀመጡት መድኖች በሁለተኛ ደረጃ ከተቀመጡት ባህርዳሮች በአምስት ነጥቦች ርቀው ይገኛሉ። ከባለፉት አምስት ጨዋታዎችም በወልቂጤ ከተማ ብቻ ተሸንፈው ሁለት አቻ እና ሁለት ድል አስመዝግበዋል። በውድድር ዓመቱ ጥሩ የሚያጠቃ እና ግቦች ለማስቆጠር የማይቸገር ቡድን ያስመለከቱን መድኖች በተጠቀሱት አምስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦችን አስቆጥረዋል፤ የማጥቃት ክፍላቸውም የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው።

መድኖች ከሌላው የቡድናቸው ክፍል አንፃር ሲታይ ደካማ የተከላካይ ክፍል አላቸው። የተጠቀሰው ክፍል ምንም እንኳ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች መጠነኛ መሻሻሎች አሳይቶ አምስት ግቦች ብቻ ቢያስተናግድም አሁንም ጥገናዎችን ይሻል፤ ለዚህ እንደ ማጣቀሻ የሚነሳው ደግሞ ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ ነው ግብ ሳያስተናግድ የወጣው።

በአዳማ በኩል የኢዮብ ማትያስ መሰለፍ አጠራጣሪ ነው ፤ መድኖች በቅጣትም በጉዳትም የሚያጡት ተጫዋች የለም።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ፋሲል ከነማ

መውረዱን ያረጋገጠው ኤሌክትሪክ እና ከድል መንገድ የራቀው ፋሲል ከነማ የሚያደርጉት ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!

እንደሚታወቀው ኤሌክትሪኮች ቀድመው መውረዳቸውን አረጋግጠዋል። ይህንን ጨዋታ አሸንፈውም ቢያንስ ከግርጌው ለመላቀቅ አልመው ይጫወታሉ ተብሎ ይገመታል። ዘንድሮ በርካታ አሰልጣኞች የቀያየረው ቡድኑ ባለፉት ሀያ አራት ሳምንታት ሦስት ነጥቦች ማግኘት አልቻለም። ለገጣፎን ሦስት ለባዶ ካሸነፈ በኋላ ከድል ጋር ተራርቋል። ለመጨረሻ ጊዜ ካደረጋቸው አስር ጨዋታዎችም በሦስቱ ብቻ ነው አቻ መለያየት የቻለው። ይህ የሚያሳየው ቡድኑ ምን ያህን በውጤት ቀውስ እንደሚገኝ ነው። በነገው ጨዋታም ብያንስ ይህንን መጥፎ ክብረ ወሰን ለመቀየር ይገባል ተብሎ ይታመናል።
\"\"
ወደ ሊጉ ካደጉበት ዓመት ጀምሮ ካሉት የውድድር ዓመታት ዘንድሮ ደካማ የሚባል የውድድር ዓመት በማሳለፍ ላይ የሚገኙት አፄዎቹ ለገጣፎን ካሸነፉበት ጨዋታ በኋላ ባደረጓቸው አራት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻሉም። እሱም ብቻ ሳይሆን በአራቱ ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ነው ማስቆጠር የቻሉት። ለመጨረሻ ጊዜ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ባዶ ለባዶ አቻ የተለያዩ ሲሆን ከዛም በፊትም በሲዳማ እና በድሬዳዋ ከተማ በተከታታይ ሽንፈት አስተናግደዋል።

በነገው ጨዋታም ምንም እንኳ ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል ተብሎ ባይታሰብም ቢያንስ በደካማው የውድድር ዓመት ላይ የተሻለ ደረጃ ይዘው ለማጠናቀቅ እና ያ በተከታታይ ከድል የራቁበት መጥፎ ክብረወሰን ለመቀየር ጠንክረው ወደ ሜዳ መግባት ይጠቅባቸዋል። በተለይም ግቦች ማስቆጠር የተሳነው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ለውጦች ማድረግ ግድ ይላቸዋል።

ዐፄዎቹ የበዛብህ መለዮ እና የሽመክት ጉግሳ ግልጋሎት አያገኙም።